ክሱ የተመሰረተባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን÷ ተከሳሾቹም 1ኛ ቄስ በላይ መኮንን፣ 2ኛ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማራው ኢያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ 3ኛ በኮሚሽን ሥራ የተሰማራው በረከት ሙላቱ ጃፋር፣ 4ኛ ዓለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና 5ኛ የኒሞና ንግድ ሥራ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ ናቸው።
4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸው እና ሌሎቹ ግን በችሎቱ መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግም በተከሳሾቹ ላይ ሁለት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
በአንደኛው ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ ቁጥር 32 ንዑስ ቁጥር 1(ሀ) እና የሙስና ወንጀሎች ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 2 እና ንዑስ ቁጥር 3 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ነው።
በዚሁ የክስ ዝርዝር ላይም ተከሳሾች በጋራ በመሆን ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚያደርግ ምንም ዓይነት የሥራ ግንኙነት ሳይኖራቸው፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚገኘው የኅብረቱ የባንክ ሒሳብ ላይ ገንዘብ በዶላር ተቀንሶ ለተከሳሾች ክፍያ እንዲፈፀም የተሰጠ ምንም ዓይነት የክፍያ ትዕዛዝ በሌለበት ሁኔታ ትዕዛዝ እንዳለ አስመስለው በተጭበረበረ መንገድ ከ6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የማይገባቸውን ብልፅግና ለራሳቸው ለማግኘትና ለሌሎች ሰዎች ለማስገኘት በማሰብ የሚል ተጠቅሷል።
2ኛ ተከሳሽ ለአፍሪካ ኅብረት ድርጅት የግንባታ ቁሳቁስ እንዳቀረበ በማስመሰል የካቲት/2016 ዓ.ም በማቅረብ ወደ ተከሳሹ ሒሳብ ቁጥር 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ከአፍሪካ ኅብረት ሒሳብ ተዘዋውሮ ገቢ እንዲሆንለት ያዘዘ መሆኑን የሚያሳይ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነድ በስሙ እንዲዘጋጅ ማድረጉ በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡
3ኛ ተከሳሽ በረከት ሙላቱ ጃፋር ለአፍሪካ ኅብረት ጥልቅ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለመሥራት የተስማማ በመሆኑ ከአፍሪካ ኅብረት ሒሳብ ወደ ራሱ የሂሳብ ቁጥር 2 ሚሊየን 525 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንዲደረግ ማዘዙን የሚያሳይ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነድ በስሙ እንዲዘጋጅ ማድረጉ በክሱ ተገልጿል፡፡
4ኛ ተከሳሽ ዓለምገና ሳሙኤል ዲንሳ ለአፍሪካ ኅብረት የጥልቅ ጉድጓድ የውኃ ቁፋሮ ሥራ የሠሩ በመሆኑ ኅብረቱ ወደ ግለሰቡ የሒሳብ ቁጥር 1 ሚሊየን 315 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገቢ እንዲደረግ የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ማዘዙን የሚያሳይ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነድ በስሙ እንዲዘጋጅ አድርጓል ተብሏል በክሱ ዝርዝር ላይ፡፡
5ኛ ተከሳሽ አበራ መርጋ ተስፋዬ ለአፍሪካ ኅብረት ከማኅበሩ የግንባታ ቁሳቁስ እንዳቀረበ እና ከኅብረቱ ሒሳብ በክፍያ እንዲፈጸምለት ወደ ራሱ በሆነው የድርጀቱ ሒሳብ 1 ሚሊየን 210 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ክፍያ እንዲፈፀም ማዘዙን የሚሳይ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶች በስሙ እንዲዘጋጅ ማስደረጉና ገንዘቡን ወጪ ለማድረግ ሰነዶቹን በውል ባልታወቀ ጊዜ እና ቦታ ለ1ኛ ተከሳሽ መስጠታቸው በክሱ ተጠቅሷል።
እንዲሁም በሁለተኛው የክስ መዝገብ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ቁጥር 382 ንዑስ ቁጥር 1 ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅምን ወይም መሻሻልን ለማግኘት በማሰብ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8 ሠዓት ተኩል ላይ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ በመቅረብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚገኘው ኅብረቱ ሒሳብ ላይ ገንዘብ በአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጎ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለተጠቀሱት ተከሳሾች እንዲከፈል የሚያዙ ሐሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን ጠቅላላ ድምሩ 6 ሚሊየን 50 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም በወቅቱ የምንዛሪ ተመን 346 ሚሊየን 843 ሺህ 475 ብር ለማስተላለፍ ሐሰተኛ ሰነዶቹን ለባንክ እንዲቀርብ በማድረግ እና በማቅረብ በፈጸሙት የክፍያ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት ወደ ሐሰት መለወጥ ወይም ሐሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ተከሰዋል የሚል ዝርዝር አቅርቦባቸዋል።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ማንነታቸውንና አድራሻቸውን ካስመዘገቡ በኋላ የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
3ኛ ተከሳሽ ጠበቃ የለኝም ማለታቸውን ተከትሎ ከጠበቃ ጋር ተማክረው እንዲቀርቡና ክሱንም በንባብ ለማሰማት ለፊታችን ሰኞ ተቀጥሯል።
ፍርድ ቤቱ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርባቸው በቀጣይ ቀጠሮ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።
በታሪክ አዱኛ fana