ኢራናውናያ ለፕሬዚዳንታቸውና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዲሁም አብረው ላሉ እንዲጸልዩ ታዟል። ፕሬዚዳንት ራይሲ ዛሬ በምሥራቃዊ አዘርባጃን ግዛት ተገኝተው የቂዝ ቃላሲ ግድብን መርቀው በመመለስ ላይ ሳሉ የተሳፈሩበት ሄሊኮፕተር መከስከሱ ነው የተሰማው።
ዜናውን እንዳራባው ቴህራን ታይምስ ዘገባ ከሆነ በበረራ ላይ የነበሩት ሦስት ሄሊኮፕተሮች ነበሩ። ሁለቱ በሰላም ወደ መጡበት ተመልሰው ሲያርፉ አንደኛው ተከስክሷል።
አንዳንዶች “ተሰወረ” በሚል እየዘገቡት ያለው ይህ የመከስከስ አደጋ ሲደርስ አየሩ አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል። IRNA የተሰኘው የአገሪቱ ሚዲያ እንዳለው ፕሬዚዳንቱና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተሰወረው ወይም ተከሰከሰ በተባለው ሄሊኮፕተር ውስጥ ነበሩ። ዜናው ከተሰማ ጀምሮ ፍለጋው አልተቋረጠም። ይሁን እንጂ አየሩ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ይህ እስክለተጻፈ ድረስ ቁርጥ ያለ መረጃ አልተሰማም።
ሩሲያ ለማፈላለግ ድጋፍ እንደምትሰጥ መንስኤውን ለመመርመር ዝግጁ መሆኗን በውጭ ጉዳይ ቃለ አቀባይዋ በኩል ማስታወቋን አልጀዚራ ዜናውን በየደቂቃው በሚያዳብረበት ገጹ ላይ አስፍሯል። የአውሮፓ ህብረትም “ተሰወረ” የተባለውን ሄሊኮፕተር ለማፈላለግ የድርጅቱን የሳተላይት ማፈላለጊያ ለመጠቀም ፈቃደኝነቱን አስታውቋል። አዘርባጃንም በተመሳሳይ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።፡
“የኢራኑን ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይስን ጨምሮ ከፍተኛ የሀገሪቱን ባለስልጣናት አሳፍሯል” የተባለ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር በምሥራቅ አዘርባጃን መከስከሱን ከዘገቡት መካከል አንዱ የሆነው ቢቢሲ በትነተና መልክ ባሰፈረው ጽሁፍ ከወዲሁ በኤራን ምን ሊሆን እንደሚችል ፈራ ተባ እያለ ትንቢቱን አኑሯል።
አርባ የሚደርሱ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአነፍናፊ ውሾችና በድሮን ተደግፈው ፈለጋ ላይ መሆናቸውን የኢራን ባለስልጣናት ህዝቡ እንዲረጋጋ በሚሰጡት መረጃ ላይ ደጋግመው እየገለጹ ነው።
የአነጋጋሪው ፕሬዚዳንት ራይሲ የመቸረሻ ዜና ሁሉን በጉጉት እየጠበቁት ነው። የኢራን መንግስት ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን ከማስታወቁ በቀር ያለው ነገር የለም።