የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት፣መበተንና ወደ ማህበረሰቡ መልሶ የማዋሃድ የቅድመ ማስጀመሪያ ምክክር በትግራይ መጀመሩ በተሰማ ማግስት በብልፅግና ፓርቲና በሕወሃት መካከል የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ፓለቲካዊ ውይይት በመቐለ ከተማ መካሄዱ ተገለጸ። መንግስት ትህነግ ወደ ጦርነት ለመግባት የጀመረውን ዳርዳርታ ባስቸኳይ ካላቆመ እርምጃ እንደሚወስድ ለሚመለከታቸው የውጭ አገራትና ለራሱ ለትህነግ ከማስጠንቀቂያ ጋር ቀን ቆርጦ አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።
ዛሬ የመንግስት መገናኛዎች እንዳሉት በብልፅግና ፓርቲና በሕወሃት መካከል የተጀመረው የፓርቲ ለፓርቲ ፓለቲካዊ ውይይት ለሶስተኛ ግዜ በመቐለ ከተማ የተካሄደ ነው።
በውይይቱም ቀደም ሲል የተደረሰውን የፓርቲ ለፓርቲ የግንኙነት መርሆዎች በማስታወስና የተጀመረውን ዋና ዋና አጀንዳዎች የመለየት ሂደት በማጠናቀቅ በአጀንዳዎቹ ቅደም ተከተል ላይ ከመከሩ በኃላ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተመልክቷል።
ዜናው በትህነግና ጊዜያዊ አስተዳደሩ መካከል የስልጣን ሽሉቻው ጎራ ለይቶ ወደ እርስ በርስ መታኮስ ያመራል በተባለ ማግስት መሆኑ ለበርካቶች መነጋገሪያ ሆኗል። የትህነግን ዜና የሚከታተሉና አድምተው የሚሰሩ ሚዲያዎች በተመሳሳይ ለዜናው ጀርባቸውን መስጠታቸው ሌላው መወያያ አጀንዳ ሆኗል። በተቃራኒ የትህነግና የብልጽግና መስማማት ስጋት የሚሆንባቸው ዜናው አስደንግጧቸዋል።
እንደ መረጃው በመጀመርያ አጀንዳነት የተለየውን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ጋር ተያይዞ በዝርዝር ውይይት በማድረግ ሁለቱም ፓርቲዎች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማምተዋል። ተስማሙባቸው የተባሉባቸው ነጥቦች
1. በቅርቡ በራያ የተፈጠረውን የግጭት ክስተት በተመለከተ በዝርዝር ውይይት በማካሄድ፣ ክስተቱ መፈጠር ያልነበረበትና ከጀመርነው ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ሂደት ጋር የሚቃረን እንደሆነ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
2. ማናቸውንም ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድና በውይይት እየፈቱ ለመሄድ ሁለቱም አካላት የበኩላቸውን ፓለቲካዊ ድርሻ ለመወጣትና በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማምተዋል:: በተያያዘም የሚኖሩ የኮሙዩኒኬሽን ስራዎች የሰላም ሂደቱን የሚደግፉ እና ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ ንግግሮችና ይዘቶች የተቆጠቡ እንዲሆኑ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
3. ማናቸውንም ግጭት የሚፈጥሩ አዝማምያዎች በጋራ ለመከላከል እና ከተፈጠሩም በፍጥነት ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት ለመስራት ተስማምተዋል።
4. የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ወደ መሬት ለማውረድ እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ስኬት ምቹ ፓለቲካዊ ሁኔታ ለመፍጠር ሁለቱም ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መስማማት ላይ ደርሰዋል።
በቀጣይም በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት በመስማማት የእለቱን ውይይቱ መጠናቀቁ ተመልክቷል።