የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተበራክተው መቀጠላቸውን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ መንግሥት በሁለቱ ክልሎች ከሚንቀሳቃሱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚያደርገው ውጊያ መካከል እንዲሁም ከውጊያ አውድ ውጪ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በዜጎች ላይ ሞት እና ከፍተኛ የመብት ጥሰት እየደረሰ ነው ብሏል።
ኢሰመኮ ዛሬ ግንቦት 20/2016 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ እጅግ አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ የዘፈቀደ እስር፣ ዘረፋ፣ እገታ እና መፈናቀል ዜጎችን እየገጠመ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ ባጠው ሪፖርቶች ላይ በምርመራ ያረጋገጣቸውን የተመረጡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ አድርጓል።
በመንግሥት ኃይሎች የተፈጸሙ ግድያዎች እና ጥሰቶች
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከሕግ ውጪ ግድያ፣ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ መፈጸማቸውን አመልክቷል።
ከየካቲት 15 እስከ 28/2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል የተካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት፣ አካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት መድረሱን ገልጿል።
የካቲት 20/2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን የአብነት ተማሪዎች ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ማደሪያ ጎጇቸው ከገቡ በኋላ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት ተኩስ ከፍተው 11 ተማሪዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን አስታውቋል።
መጋቢት ወር ላይ ኢሰመኮ በስም የጠቀሳቸው ሦስት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል በመንግሥት ኃይሎች ከተወሰዱ ከቀናት በኋላ የፊጥኝ እንደታሰሩ በጥይት ተገድለው መገኘታቸውን ገልጿል።
ሚያዚያ 9/2016 ዓ.ም. ደግሞ የመንግሥት ኃይሎች በፋኖ የተፈጸመባቸውን የደፈጣ ጥቃት ተከትሎ ጥቃቱ ወደ ተፈጸመበት ቀበሌ በመግባት 7 ሲቪል ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ ፈጽመዋል ብሏል።
ግንቦት 4/2016 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 2 ሰዎች መገደላቸውን ኮሚሽኑ አትቷል።
ኮሚሽኑ በዛሬው ሪፖርቱ በቅርብ ወራት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ ውጤቱን ይፋ አድርጓል።
ታኅሣሥ 15/2016 ዓ.ም. በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ኮሚሽኑ በስም የጠቀሳቸው 8 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።
በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተፈጸሙ ግድያዎች
በተመሳሳይ መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ከኅዳር ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች በሲቪል ሰዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች 15 ሰዎች ተገድለዋል።
በተጨማሪም ቁጥራቸው ለጊዜው በትክክል ያልታወቀ በርካታ ነዋሪዎችን ታጣቂዎቹ አግተው ወስደዋል፤ በርካታ የቀንድ ከብቶችን ዘርፈዋል እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችን አቃጥለዋል ብሏል ሪፖርቱ።
መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ስልካምባ ከተማ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ሁለት የወረዳ ነዋሪዎችን ገድለዋል።
የካቲት 29/2016 ዓ.ም. ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ወንጂ ከተማ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት 5 የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን ከሥራ ገበታቸው ካገቱ በኋላ አጋቾች የጠየቁትን የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመክፈል የሞከሩ የቤተሰብ አባላት “ከወንጀለኛ ጋር በመተባበር” በሚል በመታሰራቸው ታጣቂዎች ያገቷቸውን አምስት ሰዎች ገድለው አስክሬናቸውን ጥለዋል።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥር አጋማሽ ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ሁለት ግለሰቦችን ለመንግሥት ኃይሎች የሎጂስቲክ ታቀርባላችሁ በሚል መግደሉን አመለክቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በየካቲት እና ሚያዝያ ወራት በፈጸማቸው ተከታታይ ጥቃቶች በ44 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽሟል።
በሰዎች ላይ ከተፈጸመው ግድያ በተጨማሪ በበርካቶች ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አስፍሯል።
በፋኖ ታጣቂዎች የተፈጸሙ ግድያዎች
ከየካቲት 28/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በተከታታይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች 25 ሲቪል ሰዎችን ገድለው ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሲቪል ሰዎችን አግተው መውዳቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት ጠቅሷል።
በአካባቢው የፋኖ ታጣቂዎች በርካታ መኖሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውን እና ንብረት መዝረፋቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።
የካቲት 11/2016 ዓ.ም. በአማራ ክልል፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን የምትገኘው የሰሜን አቸፈር ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ባልደረቦች በወረዳዋ ትምህርት ለማስጀመር ለመስክ ሥራ ወጥተው ሳለ በፋኖ ተይዘው ለሦስት ቀን ታግተው እንደነበር ተጠቅሷል።
ሠራተኞቹ በእንግልት ከቆዩ በኋላ “የብልጽግናን ዓላማ ለማራመድ ሁለተኛ እንዳትመጡ” በሚል ማስፈራሪያ መለቀቃቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።
የካቲት 20/2016 ዓ.ም. ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለጉልበት ሥራ ወደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲጓዙ የነበሩ ከ274 በላይ ሰዎችን አግተው ለረዥም ጊዜ ካቆዩ በኋላ ክፍያ ጠይቀው መልቀቃቸውን ኮሚሽኑ አስታውሷል።
ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች የተፈጸሙ ግድያዎች
በመንግሥት ኃይሎች እንዲሁም ከፋኖ እና ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በተጨማሪ ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ማንነታቸው እስካሁን ባልተለዩ ኃይሎች ተገድለዋል።
መጋቢት 2/2016 ዓ.ም. ከአማራ ክልል፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የተነሱ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን እና ንብረት መዘረፉን ኢሰመኮ ተረድቷል።
መጋቢት አጋማሽ ማንነታቸው በውል ያልታወቁ የታጠቁ ቡድኖች በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ 7 ሰዎች፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ቀን በዶዶላ ወረዳ 4 ነዋሪዎች እንዲሁ ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
መጋቢት ወር ማብቂያ ላይ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ 5 ሰዎች የሶላት ስግደት አከናውነው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ሳሉ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተገድለዋል።
ከአስተዳደር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በነዋሪዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል በተፈጠሩ ግጭቶች በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል እንዲሁ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞት እና ጉዳት ደርሷል።
ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የኮማንድ ፖስቱ ማቆያ ስፍራዎች እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በርካቶች ለተራዘመ እና የዘፈቀደ እስር ተዳርገው እንደሚገኙ ጨምሮ ገልጿል።
ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ቤት ለቤት የተደረጉ ፍተሻዎችን ተከትሎ አርማ የሌለው ባንዲራ በቤታችሁ ተገኝቷል በሚል በቂ ባልሆነ የሕግ ምክንያት ሰዎች በዘፈቀደ በቁጥጥር ሥር በማዋል አላስፈላጊ እንግልትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ደርሷል ብሏል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ከተለያዩ ክሰተቶች ጋር በተያያዘ ተገቢ የሆኑ የሕግ ሂደቶችን ያልተከተሉ የተስፋፉ እስሮች መፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።
እንደማሳያም ከጥቅምት 25/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃ በማስተላለፍ እና የጥላቻ ንግግር በማሠራጨት በሚል የተጠረጠሩ ቢያንስ 244 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ኮሚሽኑ አክሎም በርካታ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች ከተያዙ በኋላ እስካሁን የት እንደሚገኙ ማወቅ አለመቻሉን ገልጿል።
መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በመካሄድ ላይ በሚገኘው የትጥቅ ግጭት፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ እና ያስፈጸሙ ኃላፊዎችን እና አባላትን እንዲሁም የታጣቂ ቡድኖች አባላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተዓማኒት ያለው ምርመራ እንዲጀመር፤ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው ካሳ እንዲያገኙ እና መልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ አለበት ማለቱን ቢቢሲ የኮሚሽኑንን ሪፖርት ጨምቆ ባወጣው ዘገባው አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገን ሪፖርት ተከትሎ ከመንግስትም ሆነ ስማቸው ከተጠቀሰው ታጣቂ ቡድኖች ለጊዜው የተሰጠ ምላሽ ይህ እስከተጻፈ ድረስ የለም። ኮሚሽኑ መንግስትን ቢወቅስም፣ መንግስት በበኩሉ በተደጋጋሚ የገለልተናነት ጥያቄ ያነሳበታል። በተለይም መከላከያ ሰራዊትን ለማጥቃት የሚመጡ ሃይሎችን ኤዝም በሉ፣ ሲገድሏችሁ ዝም ብላቹህ ሙቱ፣ አገርና መንግስትን ሲያፈርሱ ምንም እርምጃ አትወሰዱኤ የሚል ይዘት ያለው ሪፖርት እንደሚያወጣ በመጥቀስ ሲወቅሱ ይሰማል። ሰላማዊ ነዋሪ እየመሰለኡና የሰላማዊ ነዋሪዎች ዓይነት አለባበስ በመልበስ መከላከያ ሰራዊት ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ስለመፈጸሙ ምስክሮች ቢናገሩም ኮሚሽኑ ለዚህ ያለው ድርጊት ምንም ዓይነት አስተያየት ሲሰጥ አለመሰማቱ ለብዙዎች ግርታን እንደሚፈጥርም በአስተያየት ሲነሳ ቆይቷል።