ትህነግ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ ትግራይን የወረረው የኤርትራ ጦር ዘርፎ ያጋዘውን ከባድ መሳሪያና የፋብሪካ ማሽነሪዎች እንዲመስል በድጋሚ መጠየቁ ተሰማ። የተዘረፉት ንብረቶችን አስመልክቶ ሙሉ መረጃ በመዘጋጀቱም ተሰምቷል።
ወቅቱ መከላከያ ሰራዊት ላይ ትህነግ “ቅጽበታዊ” ያለውን ጥቃት ሲፈጽም ድንበሩ ክፍት በመሆኑ ሻዕቢያ ሃይሉን ሙሉ በሙሉ በማሰለፍ ትግራይን ወሮ ከቤት ቁሳቁስ ጀምሮ በተደራጀ አኳኋን በትግራይ ያሉ ፋብሪካዎችን ማሽነሪያቸውን ነቅሎ መውሰዱ በወቅቱ ቢገለጽም ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም ነበር።
ሁለተኛው ጦርነት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ የነበረው ትህነግ ቅድሚያ ወራሪውን የሻዕቢያ ሰራዊት ለማባረር ያደረገው ጥረት አልነበረም። ትህነግ ይህን ባያደርግም ወደ መሃል አገር እየገሰገሰ “ሻዕቢያ ወረረን፣ ዘረፈን” በሚል ዕለት ዕለት ክስ ያቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው። ምስልና ቪዲዮ በማሰራጨት ለማጋለጥ የሚመኦክሩም ነበሩ።
የህልውና ጦርነት ላይ የነበረው መንግስትም የሚገሰግሰውን የትህነግ ጦር ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ውጪ ሻዕቢያን ” አትዝረፍ፤ እረፍ” ሊል የሚችልበት አቅም አልነበረውም።
አሁን ላይ የመከላከያ አቅሙን በዘመናዊ ደረጃ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም መልኩ እንዳደረጃ የሚናገረው መንግስት፣ በጦርነቱ ወቅት ሻዕቢያ የዘረፋቸውን ከባድ መሳሪያዎችና ማሽኖች እንዲመለስ ጥያቄ ማቅረቡን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የኤርትራ ተወላጆች ከኢትዮሪቪው ተናግረዋል። ይህም ሻዕቢያን አናዷል። በተመሳሳይ የትህነግ ሰዎች መንግስት ላይ ያላቸው እምነት እንዲጨምር አድርጓል።
ጥያቄው በውይይት ላይ በተደጋጋሚ የተነሳ ሲሆን፣ በኦፊሳል ደብዳቤ ሲቀርብ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ የዜናው ሰዎች ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በሻዕቢያ በኩል ምንም የተባለ ነገር የለም።
ሻእቢያ ያጋዛቸው መሳሪያዎች እያንዳንዳቸው ስለሚታወቁና ግምታቸውም ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት ቀደም ሲል ከአሰብ ወደብ እንደተዘረፈው የግለሰቦችና የመንግስት ንብረት ዝም እንደማይል በደብዳቤው ማስታወቁን ምንጮቹ ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህ ከፍተኛ ዋጋ የፈሰሰበትና በሻዕቢያ ወታደሮች ወደ ኤርትራ የተጓጓዘው ንብረት ምን አልባትም የግጭት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ዜናውን ያጋሩ ክፍሎች አመልክተዋል። ከኢትዮጵያ የባህር በር ፋላጎት ጋር ተዳምሮ ስጋቱን ከፍ እንደሚያደርገውም ተመልክቷል።
ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ እያደራጃ የሚኖር፣ በከፍተኛ ደረጃ በአዲስ አበባ የገንዘብ አጠባ ላይ የተሰማሩ ሃይሎች ያሉት፣ ኮንትሮባንድ ላይ በስፋት የሚንቀሳቀስና ኢትዮጵያን የመዝረፍ ዕቅድ ይዞ ሲሰራ የኖረ ድርጅት መሆኑ በተደጋጋሚ በከፍተኛ ሃላፊዎች ዘንዳ መነገሩ ይታወሳል። አሁንም ይህ እሳቤ እንደቀጠለ የሚናገሩ ወገኖች በተደጋጋሚ ” ሻዕቢያ መላ ካልተፈለገለት ኢትዮጵያ እርፍት አታገኝም” ሲሉ ማብራሪያ ሲሰጡ ቆይተዋል። አሁንም ይህንኑ የሚሉ አሉ።
ኢትዮጵያ ሰፊ ሃይል መግንባቷና ከትህነግ ጋር የነበረው ጦርነት በሰላም መቋጨቱ ሻዕቢያን እንደሚያሳስበው በተደጋጋሚ መገለጹ አይዘነጋም። ኢሳያስ አፉወርቂ የፕሪቶሪያው ስምምነት አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው መቃወማቸውና ይህንኑ ተከትሎ ግንኙነቱ መልሶ መሻከሩን መረጃው ያላቸው ሲያስታውቁ ከርመዋል።