የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታሪካዊ በሆነ የክስ ሂደት በቀረቡባቸው 34 ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ ተብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የፍርድ ውሳኔው ሲተላለፍ፤ የበርካቶች ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ፖለቲከኛ በምርጫ መሳተፍ ይችላል ወይ? የሚለው ነው።
በቀጣይ ዓመት ኅዳር 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ለተያዘለት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካንን ወክሎ ተፎካከሪ ሆኖ ለመቅረብ ዶናልድ ትራምፕ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
ጥፋተኛ የተባሉት ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይችላሉ?
መልሱ አዎ ነው።
የአሜሪካ ሕገ-መንግሥት ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደር ዕጩን በተመለከተ የሚጠይቀው ቅድመ ሁኔታ የላላ ነው።
ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመሆን በአሜሪካ የተወለደ እና በአሜሪካ ለ14 ዓመታት የኖረ እንዲሁም ዕድሜው 35 ዓመት እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት።
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ እና በእስር ላይ የሚገኝ ዕጩ ቢሆን እንኳን ለዋይት ሐውስ ከመወዳር አያግድም።
ይሁን እንጂ ዶናልድ ትራምፕ ተከሰው ጥፋተኛ መባላቸው ከፍተኛ የሆነ ድምጽ ሰጪ ቁጥር እንደሚያሳጣቸው ይገመታል።
ብሉምበርግ እና ሞርኒንግ ኮንሰልት የሕዝብ አስተያየት ሰብሰበው ባወጡት ሪፖርቶች ወሳኝ በሆኑ ግዛቶች የሚገኙ 53 በመቶ ድምጽ ሰጪዎች፣ ትራምፕ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ቢባሉ ለሪፐብሊካን ፓርቲ ድምጽ አንሰጥም ብለዋል ብሎ ነበር።
ኩዊኒፒያክ ዩኒቨርሲቲ የሠራው የሕዝብ አስተያየት ደግሞ 6 በመቶ የትራምፕ ደጋፊዎች ፖለቲከኛው ጥፋተኛ ከተባሉ ድምጽ አንሰጣቸውም ብለዋል።
በቀጣይ የትራምፕ ዕጣ ምንድን ነው?
ከንግድ መዝገቦች ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በቀረቡባቸው 34 ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ በተባሉት ትራምፕ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል።
ዳኛው ትራምፕ ላይ የቅጣት ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት የጥፋተኛውን ዕድሜ ጨምሮ በርካታ ነገሮችን ከግምት ያስገባሉ።
ትራምፕ ጥፋተኛ በተባሉባቸው ወንጀሎች የገንዘብ ቅጣት፣ የገደብ ቅጣት ወይም በሕግ አካል ክትትል ስር የመቆየት ግዴታ ወይም እስር ሊወሰንባቸው ይችላል።
ከሐምሌ 11 በፊት ግን ትራምፕ ጥፋተኛ መባላቸውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚሉ ይጠበቃል። የይግባኝ አቤቱታቸው ደግሞ ወራትን ከፍ ካለም ዓመታት ሊወስድ ይችላል።
ትራምፕ ጥፋተኛ በተባሉበት ወንጀል ዘብጠያ የመውረዳቸው ዕድል ጠባብ ቢሆንም፣ እስራ በዳኛው ጠረጴዛ ላይ ያለ የቅጣት አማራጭ ነው።
ትራምፕ ጥፋተኛ የተባሉባቸው ወንጀሎች በኒው ዮርክ ግዛት በ’ኢ’ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ይህ ማለት አነስተኛ ቅጣት የሚያሰጡ ናቸው። ይሁን እንጂ እያንዳንዶቹ ቅጣቶች እስከ 4 ዓመት እስር ሊያስፈርዱ ይችላሉ።
ዳኛው ግን የትራምፕን አዛውንት ዕድሜ፣ ከዚህ ቀደም በወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የማያውቁ መሆናቸውን እና ወንጀሎቹ ሲፈጸሙ ኃይል የተቀላቀለባቸው አለመሆናቸውን ከግምት በማስገባት አነስ ያለ ቅጣት ሊጥሉባቸው ይችላሉ።
ቢቢሲ አማርኛ