አቶ አረጋ ከበደ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፤ ”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በአልሚ ባለሃብቶችና በመንግስት ተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ውጤት እንዲመዘገብ እያስቻለ ነው።
በዚህም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነ ቅንጅታዊ አሰራር የ312 ባለሀብት ኢንዱስትሪዎች በስራ ሂደት አጋጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን መፍታት መቻሉን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎቹን ችግር በመፍታትም ወደ ማምረት ማሸጋገር የተቻለ ሲሆን፤ በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ማምረት የተሸጋገሩት ከመሬት፣ ከብድርና ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ጥያቄዎች ”በኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በተወሰደው ቆራጥ እርምጃ መፍታት በመቻሉ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ወደ ማምረት የተሸጋገሩት ኢንዱስትሪዎችም ከ82 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ስራ እጥ ወገኖች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር ያስቻሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
”የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ክልሉ ካጋጠመው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ከፈጠረው ጉዳት ፈጥኖ በማገገም የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያገዘ ውጤት እንዲመዘገብ እንዳስቻለም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
በክልሉ እየተገኘ ያለውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠልም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የሚተገበር የመካከለኛ ጊዜ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን አስታወቀዋል።
በተጨማሪም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየትና በመፍታት ከሌላው የመደበኛ ስራ በተለየ መልኩ ለመምራት አደረጃጀት በመፍጠርና የሰው ሃይል በመመደብ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
አጠቃላይ ክልሉ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እምቅ ፀጋ አለው ያሉት አቶ አረጋ፤ ፀጋዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማፋጠንና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ ፀጋዎችን በመለየት፣ የምርት አይነቶችን በመወሰንና አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ በማስገባት በክልሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተቀርጾ እየተተገበረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በ28 የኢንዱስትሪ መንደሮች ከ3ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በመለየትና መሰረተ ልማት በማሟላት የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በኢንዱስትሪ መንደሮች መሰረተ ልማት እያሟላ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ባለሃብቶች ሼድ በመገንባትና ማሽን ተክለው ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።
(ኢ ፕ ድ)
ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓም