የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ፍርድ ቤት በነጻ ቢያሰናብታቸውም ከእስር ባልተለቀቁት የኦነግ አመራሮች ዙሪያ ያደረኩት ክትትል ፍሬ ማፍራት ባለመቻሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ ጥረት እንዲያደርግልኝ ሲል በደብዳቤ ጠየቀ።
ኦነግ በእስር ላይ የሚገኙት ሰባት አመራሮቹ ህይወት የሚያሰጋው መሆኑን በመግለጽ ሚያዚያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ደብዳቤ እንደጻፈለት ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዲሞክራሲ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያትተው አመራሮቹም በፍ/ቤት ነጻ የተለቀቁ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ከእስር አለመፈታታቸውን፣ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ከአገሪቱ ህጎች በተጻረረ መልኩ በቁጥጥር ስር እንዲቆዩ ማድረጉን በመጥቀስ ቦርዱ የአመራሮቹን እስር ሁኔታ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ኦነግ ማመልከቱን ጠቅሷል።
ኦነግ አመራሮቹ አቶ አብዲ ረጋሳ፣ አቶ ሚካኤል ቦራን፣ አቶ ኬነሳ አያና፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ ዶ/ር ገዳ ገቢሳ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ገዳ ኦልጂራ እና አቶ ግርማ ጥሩነህ የተባሉት የፓርቲው አመራሮች አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ በደብዳቤው ማሳወቁንም አካቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው በተደጋጋሚ በቀረቡት ቅሬታዎች መሰረት በጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥር 1162/11/14579 ለቋሚ ኮሚቴው በተጻፈ ደብዳቤ ከላይ በስም የተጠቀሱት ሰባቱ የኦነግ ፓርቲ አመራሮች እስር ቤት እንደሚቀያየርባቸው፤ የታሰሩበት ቦታ በግልጽ እንደማይታወቅ፤ ፍ/ቤት እንዳልቀረቡ እና የአያያዝ ሁኔታቸውም አሳሳቢ እንደሆነ በፓርቲው በተደጋጋሚ አቤቱታዎች እየቀረቡ በመሆኑ እና ቦርዱ ያደረገው ክትትል በሙሉ ፍሬ ማፍራት ሳይችል መቅረቱን በመግለጽ ለቋሚ ኮሚቴው ማሳወቁን አውስቷል።
ይሁንና በፓርቲው በተደጋጋሚ እየቀረበ ባለው አቤቱታ ላይ የተደረገ ማጣራት መኖሩን ቦርዱ መልስ ያላገኘ በመሆኑ በፓርቲው ቅሬታ ላይ የተደረገ ማንኛውም ማጣራት ካለ ቋሚ ኮሚቴው እንዲያሳውቀው ግንቦት 19 ቀን 2016 በጻፈው ደብዳቤ ቦርዱ ጠይቋል።