በብቅርቡ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም አቅርቦ በደካማ አፈጻጸም ሪፖርት የተገመገመውና አስደንጋጭ የአሃዝ መረጃ ይፋ የተደረገበት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ ድጋሚ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ተገለጸ፡፡ ሹመቱ ” የዜሮ ግምገማ ው ውጤትስ” የሚል ጥያቄ አስነስቷል፣
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በአንዳንድ ፕሮጀክቶች ላይ ከክልሎች ጋር የሚፈጠር መደራረብና የጸጥታ ጉዳዮች ለስራው እንቅፋት እንደሆኑበት ቢያስታውቅም፣ በኮሚቴው ዘንዳ ብዙም ተቀባይነት አላገኘሞ፡፡ ግምገማው የዜሮ ብዜት ሆኖ ተመዝግቧል፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ምንም ሳይሰሩ ገንዘብ የተቀበሉ ተቋራጮችም በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ሲጠበቅ የተሰማው ሹመት ከግመገማው በላይ አስደንጋጭ ሆኗል.
ከዚሁ እጅግ ደካማና ብክነት ከሚያሳየው ግምገማ በመነሳት ይሁን በሌላ ምክንያት፣ በግልጽ ባይጠቀስም ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ ቀደም ሲል ” ብቸኛ ሴቴ” ተብለው ተሽመው ወደነበረበት የአገር መከላከያ ሚኒስትርነት ስልታስን ተመልሰዋል፣ ይህንህ ዜና ተከትሎ “ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ያሳየው እጅግ ደካማና አገሪቱ ከፍተኛ እመርታ እያሳየች ከምትገኝበት የእርሻ እንቅሳቃሴ ጋር አብሮ የማይጓዝ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ብርህኑ ሌንጂሶ በሃላፊነታቸው ስለመቆየታቸው ወይም ወደ መከላከያ ሚኒስትር በመክትለነት ስለመዛወራቸው ለጊዜው የተባለ ነገር የለም” የሚል አስተያየት በአሽሙር መልክ ተሰምቷል፣
ሚኒስቴሩ የ2015 አፈጻጸሙን የተመለከተ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ ፤ መስኖ ፤ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቦ የተሰጠው ምላሽና በአሃዝ የተደገፈ ግምገማ ሚኒስትሮቹንና በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎችን ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚገባ ዜናውን ተከትሎ አስተያየት መሰጠቱ ይታወሳል፣
ኢንጂነር አይሻ አይሻን ብዙም ከብልሹ አሰራር ጋር የማያሙዋቸው፣ ምንም ሆነ ምን ዙሪያቸውና አብረዋቸው የሚሰሩ ረዳቶቻቸው ሊፈተሹ እንደሚገባ ደጋግመው ሲወተውቱ ነበር፣ የመንግስት ቀጣይ እርምጃ በግልጽ ባይታወቅም ዶክተር አብርሃም በላይ ይህንኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት እንዲያቀኑ መሾማቸው ይፋ ሆኗል፣
የመስኖና ቆላ ሚኒስቴር አስደንጋጭ የግምገማ ሪፖርት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ዜናውን ያሰራጩ ሚዲያዎች ኢንጂነር አይሻ አይሻ ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት ሲዛወሩ ሹመታቸውን ዜና ከማድረግ ባለፈ ቀደም ብለው እሳቸው ስለሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የስራና የአፈጻጸም የዜሮ ብዜት ያሉት ነገር የለም፣ ሪፖርተር የቋሚ ኮሚቴውን ሪፖርት ጠቅሶ ክስር ያለውን ዘግቦ ነበር፣
- ከ27 ፕሮጀክቶች ውስጥ የአሥሩ አፈጻጸም ዜሮ ነው ተብሏል
- የበጀት አጠቃቀሙ ለሙስና የተጋለጠ መሆኑን ፓርላማው ተናግሯል
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ከተያዘለት በጀት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 5.4 ቢሊዮን ብር ቢጠቀምም ከ27 ፕሮጀክቶች አሥሮቹ አፈጻጸማቸው ዜሮ ሆኖ መመዝገቡና ያጠናቀቀው አንድም ፕሮጀክት አለመኖሩ ተገለጸ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡ የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ባቀረበው ጥያቄ፣ ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱ ሲጀመር ተይዞለት ከነበረው 7.8 ቢሊዮን ብር በዘጠኝ ወራት ውስጥ 5.4 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ሥራ ላይ ማዋሉን ገልጾ፣ ካከናወናቸው 27 ፕሮጀክቶች ጥራትና ዲዛይን ሥራ የመከታተልና ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአሥር ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዜሮ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ከተጠናቀቁ ሦስት ፕሮጀክቶች ውጭ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አንድም ፕሮጀክት በዕቅዱ መሠረት ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ አለመኖሩን ገልጿል፡፡ በዚህም ከሁሉም ፕሮጀክቶች 29 ሥራዎች አፈጻጸማቸው ዜሮ በመቶ፣ 17 ሥራዎች ደግሞ ከ50 በመቶ በታች ሆነው እያለ 5.4 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙ በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በክልሎች መካከል ያለው የአፈጻጸም ግምገማ ሰፊ ልዩነት ማሳየቱ የሚኒስቴሩን ድጋፍና ክትትል መላላት የሚያሳይ ነው ሲል የገለጸ ሲሆን፣ በደቡብ ክልል ውስጥ ሲከናወኑ የነበሩ ፕሮጀክቶች በክልሉ እንደ አዲስ መደራጀት ምክንያት ፕሮጀክቶቹ ተጓተዋል በሚል በምክንያትነት የተቀመጠው ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ የሚኒስቴሩ ድጋፍና ክትትልን መላላት የሚያሳይ ነው በማለት አስቀምጧል፡፡
የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ አሥራ ሰባት ፕሮጀክቶች የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ አማካይ አፈጻጸም ከ80 እስከ 85 በመቶ መሆኑንና በፀጥታ ችግሮች ምክንያት በዕቅዱ ያልተሠሩ ወይም ሙሉ በሙሉ የቆሙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡
ሚኒስትሯ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በዚህም የፕሮጀክቶች ጥራትና ዲዛይን አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆኖ ለመመዝገቡና ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት የተለያየ ምክንያት ቢኖርም፣ የፀጥታ ችግሩ ግን ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በየደረጃው ያሉ የማስፈጸም አቅም ውስንነት፣ የወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲሁም የዋጋ መናር እንደ ችግር አስቀምጠዋል፡፡
ሚኒስቴሩ አንድም ያጠናቀቀው ፕሮጀክት ሳይኖር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከተያዘለት በጀት 99.7 በመቶውን መጠቀሙን አስመልክቶ ላልተሠሩ ሥራዎችም ክፍያዎችን ፈጽሟል በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አይሻ (ኢንጂነር)፣ ሚኒስቴሩ ላልተሠሩ ሥራዎች ምንም ዓይነት ክፍያ አለመፈጸሙን አብራርተው ‹‹ከፕሮጀክት አፈጻጸሙ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት ያለው ሁኔታ አይፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡
መሬት ላይ የሚሠራው ሥራና በጀቱ እኩል እየሄደ ያልሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም ‹‹ሚኒስቴሩ እየከፈለ ያለው ክፍያ ዓምና ለተሠሩ ፕሮጀክቶች ጭምር መሆኑ፣ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ በመሄዱ በሚደረግ የዋጋ ማስተካከያ እንዲሁም በእጃችን ያለው የ100 ቢሊዮን ብር ኮንትራት ሆኖ፣ የሚሰጠው ከአሥር ቢሊዮን ያነሰ በጀት ሲሆን፣ የተሠራው ሥራና የሚከፈለው ክፍያ እኩል አይሆንም›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ካስፈለገም የወጪዎቹን ሰነዶች ድጋሚ መመልከት ይቻላል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የውኃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ፈትያ አህመድ፣ ሚኒስቴሩ በቋሚ ኮሚቴው የሚሰጡ አስተያየቶችን እየተቀበለ አለመሆኑን ገልጸው፣ የበጀት አጠቃቀሙ ለሙስና ተጋላጭ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ዕቅድና ሪፖርቱ መሬት ላይ ካለው ሁኔታ አንፃር አለመናበብ መኖሩን ጠቁመው፣ የተሰጡ አስተያየቶችን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡