“ዜናው የኢትዮጵያ ሰበር ዜና መህን ነበረበት” ሲሉ መረጃውን አያይዘው የላኩልን አቶ ሰለሞን ጉዲሳ፣ እንዲህ ያለው ዜና በሌላ አገር ይፋ ቢሆን በምን ያህል ደረጃ መነጋገሪያ ሊሆን እንደሚችል ጤናማ አዕምሮ ላላቸው ዜጎች ስውር እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የተተበተበችበት የዘር ፖለቲካና፣ የዘር ፖለቲካን ንግድ ያደረጉ አካሎች የሚፈጥሩት ሴራ ለእንዲህ ያለ የፈጠራ ስራ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ንፉግ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ገልጸው ዜናውን የላኩት አቶ ሰለሞን፣ የፈጠራ ባለቤቱን አሞግሰውታል።
ለጊዜው ስራቸውንና ሃላፊነታቸውን በማቆየት አስተያየታቸውን አክለው መረውጃውን ከመንግስት ሚዲያ ወስደው የላኩት ኢትዮጵያዊ፣ የመገናኛ አውታሮች እንዲህ ላሉ ድንቅ የፈጠራ ሰዎች እውቅና ሊሰጡ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሰሩትን ማበረታታት አዳዲስ ወጣቶች ወደ ፈጠራ እንዲገቡ ማነቃቂያ እንደሆነም አስታውቀዋል።
” ፋዴሳ ዛሬ ብቸኛ የመብራት ተጠቃሚ ነው። ነዳጅ ኖረ አልኖረ ግድ የለውም። በሚሊዮኖች በጨለማ በሚኖሩባት ኢትዮጵያ አንዴ ቻርጅ ተደርጎ አንድ ዓመት የሚቆይ ድምጽ አላባ ጄነሬተር መስራት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ከሰበር ዜናም በላይ ነው” ሲሉ ዜናውን ለመላክ ያነሳሳቸውን ምክንያት ገልጸዋል።
ፈዴሳ ሹማ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በቄለም ወለጋ ሲሆን በከተማው ውስጥ በኤሌክትሪክ ጥገና ሙያውም ብዙዎች ያውቁታል፡፡ ሥራው ጥገና እንደመሆኑ የመብራት መጥፋትና መቆራረጥ ሥራውን ብዙ ጊዜ ያስተጓጉልበታል።
ችግር ብልሃትን ይወልዳል እንዲሉ ወጣቱ መላ በመዘየድ ከብዙ ጥረት በኋላ አንድ ግዜ ቻርጅ ተደርጎ እስከ አንድ ዓመት ድረስ አገልግሎት መስጠት የሚችል ቴክኖሎጂ እውን አደረገ። ቴክኖሎጂውንም ይበልጥ አዘምኖ መስራት ችሏል።
ቴክኖሎጂው የመብራት አገልግሎት ከመስጠቱ ባለፈ ሞባይል፣ ለቴሌቭዥን፣ ፍሪጅና የትኛውንም አይነት የኤሌክትሮኒክስ መጠቀሚያዎችን ቻርጅ የሚያደርግ፣ የሚያንቀሳቅስና በገመድና ገመድ አልባ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዲቻል ተደርጎ የተሰራ ነው።
አንዴ የያዘውን ሀይል ሪሳይክል እያደረገ ራሱን ቻርጅ ከማድረግ አልፎ ለረዥም ጊዜ ሀይል ማመንጨት የሚችለው ይህ ቴክኖሎጂ በሀገራችን የሀይል አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
ከ300 ዋት ጀምሮ እንደ ተጠቃሚው አቅምና ፍላጎት የሚዘጋጀው ይህ ድምፅ አልባ ጄኔሬተር አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ነው ወጣቱ የገለፀው።
በዚህም ወጣቱ ፌዴሳ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን በቤቱ መብራት የማይጠፋበት ብቸኛው ሰው ነው ተብሏል። ወጣቱ ቴክኖሎጂው በስፋት ተመርቶ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ እየሰራ ሲሆን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እገዛ እየተደረገለት እንደሆነም ተነግሯል።