በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) በተለያዩ ዘርፎች የሕይወት ዘመን ሽልማቶች በመስጠት ተጠናቋል

በሕይወት ዘመን አበርክቶ ሽልማት ምድብ በየዘርፉ ለሀገራቸው ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘመን ሽልማቶች ተሰጥቷል። ተሸላሚ ከነበሩት ግለሰቦች መካከልም፡- ዛሬ ታሪካቸውን በአጭሩ የምናቀርበው እና በዚህ መድረክ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ኢንጂነር አያና ብሩ ናቸው።
ኢንጂነር አያና ብሩ የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር የሠሩ በመሆናቸው “የኢትዮጵያ ታይፖግራፊ አባት” በሚል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕይወት ዘመን ሽልማት ሰጥቷቸዋል። ለመሆኑ ኢንጂነር አያና ብሩ ማን ናቸው?
ኢንጅነር አያና ብሩ ትውልድ እና እድገታቸው በወለጋ ነው። በወቅቱ በእንግሊዝ ኤምባሲ ሲሠሩ የነበሩት ታላቅ ወንድማቸው አቶ ዳባ ብሩ አያናን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ዳግማዊ ምንልክ ትምህርት ቤት አስገቧቸው። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በብቃት ያጠናቀቁት አያና ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ግብፅ ተላኩ።
ከዚያም ወደ እንግሊዝ ሀገር በማቅናት ከለንደን ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ተመርቀዋል። እንግሊዝ ሀገር እያሉም ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራ ሲያልሙ የነበሩት ኢንጂነር አያና “ኦሊቬቲ” ከተባለ የጣሊያን ካምፓኒ ጋር ባደረጉት ምርምር የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር ማሽን ዲዛይን አዘጋጁ።
ይህን ዲዛይን ወደ ተግባር ለመቀየር አንግሊዝ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ለማስተዋወቅ ቢሞክሩም “የአማርኛ ፊደል(ቋንቋ) የሚያገለግለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በመሆኑና ገበያ ስለማያስገኝ አያዋጣንም” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው።
በምላሹ ተስፋ ያልቆረጡት ወጣቱ መሐንዲስ ዲዛይኑን ይዘው ወደ አሜሪካኖች ሲሄዱ አሜሪካኖቹ እንደሚሠሩላቸው ግን የአሜሪካ አርማ እንደሚታተምበት ነገሯቸው፤ ኢንጂነር አያናም በሥራቸው ላይ የኢትዮጵያ አርማ እንዲታተም ፍላጎት ቢኖራቸውም አማራጭ ስላልነበራቸው ፈቅደው ሁለት ታይፕራይተሮችን አሠርተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።ማሽኑን ለንጉሡ በመስጠትም አገልግሎት ላይ እንዲውል አድርገዋል። EBC