የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ አዋጅን ተዘጋጅቶ ለተወካዮች ምክር ቤት ተላከ። ውሳኔው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ላይ ምርጫ ቦርድ የጣለውን ዕግድ የሚነሳበትን አግባብ የሚያመቻች እንደሚሆን ተመልክቷል። አቶ ጌታቸው ረዳ እርምጃውን አድንቀዋል።
ም/ቤቱ ” ከህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ስርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም ” ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 10/2013 ዓ.ም የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ሕጋዊ ሰውነት እንደሰረዘ ማስታወቁ አይዘነጋም፤ ቦርዱ ለዚህ ውሳኔ የበቃው ትህነግ ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ላይ መሳተፉን በሌላ አነጋገር ትህነግ ጦርነት አንስቶ ፍላጎቱን በሃይል ህግ ከሚፈቅደው ውጭ በመንቀሳቀሱ ነበር። በዚሁ ውሳኔ መሰረት ትህነግ ያለው ንብረትም እግድም የውሳኔው አካል እንደሆነ አስታውቆ ነበር።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ትህነግ ከአመጻ ተግባሩ መታቀቡን ጠቅሶ ዕግዱ እንዲነሳለት ምርጫ ቦርድን ጠይቆ ነበር። ቦርዱም ትህነግ ኃይልን መሠረት ያደረገው የአመጻ ተግባር መታቀቡን ገልጾ፣ ያም ቢሆን ግን በምርጫ ቦርድ ህግ እንደገና የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1162/ 2011 እንዳልተገደደ በምላሹ አስታውቋል።
ቦርዱ የማሰናበቻ ህግ እንጂ ጥፋተኛ የነበረ ከጥፋቱ ሲመለስ ዕግድ እንዲነሳለት የሚያችል ባለመኖሩ ሳቢያ የትህነግን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። ዛሬ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የተሰማው አስተያየትም መነሻው ይህ የህግ ክፍተት እንደሆነ ተደምጧል።
” በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ረቂቅ የአዋጅ ማሸሻያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ” በሚል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ሌላው ደግሞ ምክር ቤቱ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አድርጎ ስለማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቀረበው አዋጅ ላይ መወያየቱን አሳውቋል።
” በወንጀል የተገኘን ንብረት ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የደህንነት ስጋት ከመሆኑ በተጨማሪ የፋይናንስ ስርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጸኝነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የሚያደርግ ነው ” ብሎታል።
ይህን ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን የገለጸው ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመልክቷል።
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ አንድ እርምጃ የተራመደ ውሳኔ በማለት አወድሰው በኤክስ ገጻቸው ለጥፈዋል።
ትህነግ ውስጣዊ ችግሩ በተባባሰበትና ገሃድ በወጣበት በዚህ ወቅት ህጋዊ ዕውቅና ጋር ተያይዞ በተከፋፈለው ቡድን መካከል ምን ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ መግለጽ ባይቻልም ጎራው ለይቶ ሁለት ቡድን እንደሚወጣ የሚያምኑ በርካታ ናቸው።
ትሕነግ ወደ ብልጽግና ለመግባት እየተደራደረ ነው የሚለው መረጃ ከወጣ ወዲህ ምንም እንኳን የትሕነግ ሰዎች ምንም ዓይነት ድርድር የለም ቢሉም በመሬት ላይ የሚታየው ግን የሚጠቁመው ሌላ ነው። በቅርቡ የብልጽግና ሁለተኛ ሰው አደም ፋራህ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተ ቡድን ይዘው ወደ መቀሌ በመጓዝ ከትሕነግ ሰዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
መቀሌ ላይ በአማርኛ በተደረገው ስብሰባ ከብልጽግና የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ፣ የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የአማራ ክልል የቀድሞ የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሰማ ጥሩነህ የተገኙ ሲሆን ከትሕነግ በኩል ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ጌታቸው ረዳ፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባል ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (በበረኻ ስሟ ሞንጆሪኖ)፣ አብርሃም ተከስተ እና አዲስ ዓለም ባሌማ ናቸው፡፡