ኤርትራ ” ቅኝ ገዝታኛለች” ስትል ከምትወንጅላት ኢትዮጵያ የተለየችበትንና አገር የሆነችበትን 33ኛ ዓመት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ባስገነቡት ስታዲየም አክብራለች። ግንቦት አስራስድስት ቀን በተከበረው በዓል ላይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸው አዲስ ያነሱት ጉዳይ ቢኖር ስጋታቸውን ብቻ ነው። “ቀጣዩ” ያሉትን ጦርነት ” የአደባባይ ሚስጢር ነው” ብለውታል። ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ “እነኳን ለነጻነት ቀን አደረሳችሁ” ሲሉ የደስታ መግለጫ ልከዋል።
” የነሳነቱ ፍሬዎች ከወዴት ናቸው” የሚሉ በርካታ የኤርትራ ተወላጆች ጎራ ለይተው በሚከታከቱበት፣ አንዳንዴም ነፍስ በሚጠፋበት “የነጻነት ቀን” ላይ ኢሳያስ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ ወይም ለሚነሳባቸው ትችት መልስ ሰጥተው አያውቁም። ይልቁኑም አሜሪካና አውሮፓን በቃላት መከስከስ፣ ማብጠልጠልና ማውገዝ የየዓመቱ ተጠባቂ ንግግራቸው ሆኗል። ዘንድሮም ያደረጉት ይህንኑ ነው።
በዘንድሮው ንግግራቸው አዲስ የሆነው “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ላይ የቀረበ ተጽዕኖና ጫና የሚያሳድሩ፤ በጎረቤቶቻችን እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችና አዝማሚያዎች፤ በእርግጥም በርካታ ናቸው” ሲሉ የተናገሩትና ነው።
አገራቸው ይህን ጉዳይ ጠንቃቃ እንደምትከታተለው ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ እሳቸውን ስለሚተካ መሪ፣ ስለ ህገመንግስት፣ ስለምርጫ፣ ስለ ነጻ ሚዲያ፣ ስለ መድበለ ፓርቲ ወዘተ ለሰላሳ ሶስተኛ ጊዜ ባደረጉት የግንቦት አስራስድስት ንግግራቸውም ዘለውታል። በተግባር ባያደርጉት እንኳን ለወሬ ያህል እንኳን እነዚህን ጉዳዮች የሚፈሩት ኢሳያስ ኤርትራን እንዳጨለሟት የሚገልጹ በርክተዋል።
ዓለም እንደ ተራ ሸቀጥ ካሻው መደብር፣ ወይም ድርጅት እንዳሻው የሚሸምተው ኢንተርኔት በርቅ የሆነባት፣ አምራች ዜጎቿን ከስራ ባዶ እንደሆነች የሚነገርላት፣ ከአዳዲስ ነገሮች ጋር ብዙም የማትተዋወቀው ኤርትራ ትውልዷን ቢያንስ ለሰላሳ ዓመታት ወደሁዋላ እንደጎተተች የሚናገሩ “ይህ የትውልድ ክፍተት ወደፊት ዕዳው ከባድ ነው” በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግን ይህ ጉዳይ አያሳስባቸውም። ይልቁኑም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ውል ያስጨንቃቸዋል። ከዚህም በላይ የህወሃትና የመንግስት የሰላም ስምምነት ያበሳጫቸዋል። አሁን አሁን ደግሞ እረፍት ነስታኡቸዋል የሚሉም አሉ።
ኢሳያስ በንግግራቸው “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ላይ የቀረበ ተጽዕኖ እና ጫና የሚያሳድሩ፤ በጎረቤቶቻችን እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና አዝማሚያዎች፤ በእርግጥም በርካታ ናቸው” ሲሉ የገለጹት ኢትዮጵያን እንደሆነ ፍንትው ብሎ የሚታይ ሃቅ እንደሆነ በበርካታ ማሳያዎች እየተብራራ እየቀረበ ነው።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ “ጠቅላይ እና ሁሉን ልቆጣጠር ባይ ኃይሎች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ ሀገራቸው በምትገኝበት ቀጠና “ሌላ የጦርነት ዑደት ለመቀስቀስ እያሴሩ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። ኢሳያስ ወንጅለው አላቆሙም ኤርትራ ለሚያጋጥሟት ማናቸውም ጦርነቶች ራሷን በብቃት ያዘጋጀች አገር መሆኗን ገልጸዋል። “ዝግጁ ነን” ሲሉ።
የፕሬዚዳንቱን “ዝግጁ ነን” ንግግር፣ በቅርቡ ቀይ ለባሽ መኮንኖችን ሲያስመርቁ ” በቀጣናውም ሆነ በአገር ውስጥ የሚያሰጋን ሃይል የለም፤ ሰፊና ዘመናዊ ጦር ተገንብቷል” ላሉት የአገር መከላከያ ሰራዊት ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ምላሽ የሚመስል ንግግር አድረገው የወሰዱም አሉ።
በብቻኛው የአገራቸው ቴሌቪዥን ቀርበው ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ለሰዓታት ስለ ዓለም ፖለቲካስ፣ የሃይል አሰላለፍ፣ ስለ አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም አስተሳሰብ ወዘተ ለኤርትራ ህዝብ ማብራሪያ የሚሰጡት ኢሳያስ፣ አሁንም እንደቀድሞው አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ሩሲያ፣ቻይና፣ ታይዋን ፣ሆንግ ኮንግ፣ ፍልስጤም፣ምኑንም ሳይዘሉ አንስተዋል። ስለ አውሮፓ ህብረት፣ ኔቶና ከቀይ ባህር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ምልህቋን ለመታል እየሰራች ስላለችበር ኤደን ባህረ ሰላጤ ዳሰሳ ድርገዋል።
ዳሰሳቸውን የቋጩት ግን “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ላይ የቀረበ ተጽዕኖ እና ጫና የሚያሳድሩ፤ በጎረቤቶቻችን እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና አዝማሚያዎች፤ በእርግጥም በርካታ ናቸው” በሚለው ሃርግ ነው።
ዘወትር ችግሮችን ወደ ውጭ አካላት ላይ የሚገፉት ኢሳያስ እሳቸው ፐሬዚዳንት ሆነው መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ኤርትራ ለደረሰችበት ደረጃና የተወሳሰቡ ችግሮች እና ውድመቶች “ጠቅላይ እና ሁሉን ልቆጣጠር ባይ” ያሏቸውን ኃይሎች ተጠያቂ አድርገዋል።
እነዚህ ኃይሎች “ክፍፍል እንዲኖር የማነሳሳት፣ ቀውሶችን የመፍጠር እና የማባባስ” ከዚያም አልፎ ወረራ እና ጦርነት እንዲቀሰቅስ አጀንዳዎችን የማስረጽ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ኢሳያስ በንግግራቸው አትተዋል።
እነዚህ ኃይሎች ያቀዷቸው በርካታ ግጭቶች አለመሳካት “ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ” ውስጥ እንደከተታቸው የጠቀሱት የኤርትራው ፕሬዝዳንት፤ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት “ሌላ የጦርነት ዑደት ለመቀስቀስ እያሴሩ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል። ፕሬዝዳንቱ የሌላ ዙር ጦርነት ጉዳይን “የአደባባይ ሚስጥር ነው” ሲሉ በንግግራቸው ቢገልጹም ዝርዝሩን ከመግለጽ ተቆጠበዋል። የዚህ ጉዳይ ዝርዝር “በትክክለኛው ጊዜ” የሚገለጽ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጥቆማ ከሰጡ በሁዋላ በመጨረሻ ኤርትራ ሊያጋጥማት ለሚችሉ ሁሉም አይነት ጦርነቶች የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ዝግጁነት አሁንም ብቁ መሆኑን አስታውቀዋል። የኤርትራ ህዝብም በዚህ ጉዳይ ሊጨነቅ እንደማይገባውም ማስተማመኛ ሰጥተዋል።
አክለውም ኤርትራ ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን ከመጠበቅ ባሻገር፤ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን “ወዳጅነት፣ ትብብር ና ተመጋጋቢነት” ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን አሁንም በብርቱ ማከናወኗን እንደምትቀጥል ጨምረው ገልጸዋል
ኤርትራ ጉርብትናዋ ከሱዳን፣ ከኢትዮጵያና ከጅቡቲ ጋር ነው። ከጅቡቲም ሆነ ከሱዳን ጋር አሁን ላይ የሚጋጭ ወይም ሊያዋጋ የሚችል አጀንዳ የለም። አንዱና ትልቁ እሳቸውም እንዳሉት የአደባባይ ሚስጢር የሆነው ጉዳይ ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለው የህልውና ጥያቄና ለህልውና ሲባል የሚወሰደው ማናቸውም ዓይነት እርምጃዎች ናቸው።
በተደጋጋሚ እንደተደመጠው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አልደገፉም። እንደውም የሰላም ንግግሩ አካል አለመሆናቸው አበሳጭቷቸዋል። ከሻዕቢያ ቀለብ ይቆረጥላቸዋል የሚባሉ የዩቲዩብ አራጋቢዎች ይህዚን ሁለት ቀን “መንግስት ከትግራይ ሃይሎች ጋር በመሆን ኤርትራን ሊወጋ ነው” ማውገዝ ጀምረዋል። ለምን ቀድሞ መጮህ እንደተፍለገ ግልጽ ባይሆንም ጉዳዩ የማይቀር እንደሆነና ኢሳያስ እንዳሉት ጊዜው ሲደርስ ይፋ የሚሆን ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ።
የባህር በር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ኢሳያስ ዘመናቸውን ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ ተቅዋሚና ታጣቂ በማደራጀት ያሳለፉ፣ አሁንም በዚያው አቋማቸው የጸኑና ብረት አንጋቾችን እያስለጠኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚነዱና ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት የሚለውን ዓላማቸውን ለአፍታ የማይስቱ ናቸው።
ትህነግ የአገር መከላከያን ሲወጋ በተፈጠረው ክፍተት ተንደርድሮ ትግራይን ያጥለቀለቀው የሻዕቢያ ሃይል፣ በበርካታ ዝርፊያ፣ የጅምላ ግድያና፣ ውድመት የሚጠየቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ለመከላከያ በወቅቱ ለሰጠው ድጋፍ ምስጋና እንደተቸረው የሚታወስ ነው። መንግስትም ይህንኑ እንደሚያከብር በይፋ በመግለጫ አስታውቆ ነበር።
ከሰላም ስምምነቱ በፉት ጀምሮ ለመጠባበቂያ ሲዘጋጅ የነበረው ሻዕቢያ በአማራ በኩል ለተነሳው ጦርነት ግንባር ቀደም ተዋናይ እንደሆነ በርካታ መረጃዎች መውጣት ጀመሩ። የሻዕቢያ ደጋፊና ወዳጅ ወይም ተቀጣሪ የሆኑ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ሳዋ የሰለጠኑ ሰልጣኞች ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን ተናገሩ። ይህ ሳይበቃ ለሶማሌ ሰፊ ቁጥር ያለው ወታደር በተደጋጋሚ በማስለጠን ወደ ምስራቅም ሃይል ማከፋፈሉን ተያያዙት።
ከሶማሌና ከግብጽ ጋር በገሃድ በመወገን ኢሳያስ ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ ያሴሩ ጀመሩ። የሴራው አካል የሆነውና ከሸኔ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን ያነዳል የተባለው በአማራ ክልል የተነሳው ጦርነት በታሰበው መልኩ ውጤት ሊያመጣ አለመቻሉና ትህነግ በተገመተው ደረጃ ዳግም ወደ ጦርነት አለመግባቱ ኢሳያስን ስጋት ውስጥ እንደከተተ መረጃዎች ይወጡ ሰንብተዋል።
ኢትዮጵያ ላቀረበችው አሰብን የመጠቀም ጥያቄ ያለ በቂ ምክንያት ጀርባቸውን የሰጡት ኢሳያስ አፉወርቂ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ “እምቢ” አሉ።፡ኢትዮጵያም ወእን ፟ህልውናዬ ነው”፡በሚል በገሃድ አነሳች። መሪዋ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ታሪክ ጠቅሰው ኢትዮጵያ ከአንድም ሁለት የባህር በር እንደነበራትና በሴራ እንደተነጠቀች አስታወቁ። ይህ ትውልድ በወደብ ጉዳይ ሃፍረቱን እንዲያነሳና ህልውናውን እንዲያስከብር ጥሪ አቀረቡ። ምሁራንና አዋቂዎች፣ እንዲሁም ዜጎች በነጻነት በጉዳዩ እንዲመክሩ ተጣሩ፤ ኢሳያስን ይህም አላስደሰታቸውም።
በተለይም ለአራተኛ ዙር ውጊያ ያደርጋሉ የተባሉት የትግራይ ታጣቂዎች ከዛ ይልቅ ወደ መከላከያ የመቀላቀላቸው ዜና፣ የተረፉትም በሰላም እንደሚሸኙና ተፈናቃዮች በሰላማዊ መንገ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ኢሳያስ ስጋታቸው እጅግ እንደጨመረ አክቲቪስቶቻቸው ከሚያቀርቡት መረጃ ለመረዳት ይቻላል።
በግልጽ ባይነገርም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ወሳኝ የፖለቲካ ኤሊቶችና በዕርጋታ ለሚመረምሩ “ኢሳያስ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያ ስለሟና ጥቅሟ ሊከበር አይችልም” የሚለው ድምዳሜ ያስማማቸውል። ለጊዜው ይፋ ባይሆንም የትህነግና የመንግስት አመራሮች በዚህ እሳቤ ወደመተማመኑ ደርሰዋል። እናም ኢሳያስ ” የአደባባይ ሃቅ ነው” ያሉት ቀጣዩ የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይና የህልውና መከበር ትንቅንቅ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የአለም ፖለቲካ የሚቀያየር ከመሆኑ አንጻር፣ ባለበት የሚጸና ጉዳይ የለም። በዚሁ የዓለም ፖለቲካ ተለዋዋጭነት ባህሪ የተነሳ የሚፈጠረው ባይታወቅም፣ ኢትዮጵያ ሃብቷንም አፍሰሳም ሆነ በሌላ መንገድ ህልውናዋን ለማስጠበቅ መንገዷን መቀጠሏ የሚቆም አይሆንም። ጥያቄው የመንግስት ሳይሆን የህዝብ ነው። ማንም መንግስት ቢመጣ ይህ ጥያቄ አይቆምም። ማንም መንግስት ቢመጣ ካሁን በሁዋላ ቡና ሳይተክሉ ቡና ኤክስፖርት ማድረግን አይፈቅድም።
“በትክክለኛው ጊዜ” ብለው ሁሉንም ገሃድ እንደሚያደርጉት ያስታወቁት ኢሳያስ የህወሃትና የመንግስ መስማማት እምነት እያዳበረ ከሄደ ሊከብዳቸው እንደሚችል በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሰራዊት ዝግጅትን አስመልክቶ ብርጋዲየር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ” እኛ ዝግጅታችን ለአገር ውስጥ አይደለም” ሲሉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ጦርነት በንም መልኩ እንደማያዋጣ ስምምነት አለ። ጦርነት እጅግ አውዳሚና ዘላቂ መፍትሄ የማያመጣ በመሆኑ በሰለማዊ መንገድ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊቀጥል ሁሉም ጉዳይ እንዲቋጭ አብዛኞች ይፈልጋሉ። ኢሳያስ በመጨረሻው መልዕክታቸው እንዳሉት መልካም ጉርብትና አዋጪነቱ ለጥያቄ አይቀርብም።
ኤርትራ ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን ከመጠበቅ ባሻገር፤ ከቅርብ ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ወዳጅነት፣ ትብብር እና ተመጋጋቢነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን አሁንም በብርቱ ማከናወኗን እንደምትቀጥል በንግግራቸው ማሳረጊያ ኢሳያስ አንስተዋል። እግረ መንገዳቸውንም በሌሎች አገሮችም ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ ማስታወቅ እንደሚገባቸው ባይዘነጉ ደግ እንደነበር ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት ወቅት የሻዕቢያ ጦር በባለሙያ በተደገፈና በዘመቻ በትግራይ ያካሄደውን ዝርፊያ፣ እንዲሁም ከባድ የጦር መሳሪያዎች እንዲመልስ መጠየቁን ገልጸን ዜና ማቅረባችን አይዘነጋም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስየንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ልከዋል። በመልዕክታቸው ኢትዮጵያና ኤርትራ ትብብራቸውን አጠናክረው አብረው እንደሚጓዙ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም በተመሳሳይ የንኳን አደረሳችሁ መልዕክት መላካቸውን አመልክቷል።