መንግስት በስድስት ቦታዎች የተፈጥሮ ጋዝ መገኘቱን አረጋገጠ፤ በቅርቡ ምርት ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል። በሶማሌ ክልል ኦጋዴን በተደረገ ዳሰሳ 21 ቢሊዮን 336 ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ እንዳለ መረጋገጡን የማዕድን ሚኒስቴር ገልጿል። በቅርቡ በዓመት ከስምንት ቢዮን ዶላር ገቢ የሚያስገኝ የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑንንመዘገባችን አይዘነጋም።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማትዮስ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን በተደረገ ዳሰሳ 21 ቢሊዮን 336 ሚሊዮን የተፈጥሮ ጋዝ እንዳለ ተረጋግጧል፡፡
አስቀድሞ በዘገብነው ዘገባ በኢትዮጵያ ኦጋዴን ሰርጥ ካሉብና ሂላል አከባቢ የሚገኘውን የነዳጅ ሃብትና የተፈጥሮ ጋዝ አውጥቼ ወደ ምርት እገባለሁ ያለው የቻይናው ነዳጅ አውጪ ካምንፓኒ Poly GCL ተመልሶ የነዳጅ ማውጣት ፍቃድ አግኝቶ ወደ ስራ መግባቱ ስናመለክት ከማዕድን ሚኒስቴር ምላሽ ማግኘት እንዳልቻልን ማስታወቃችን አይዘነጋም።
አሁን ላይ ሚኒስትር ዳኤታው እንዳሉት በአካባቢው 19 ጉድጓዶችን በመቆፈር በተደረገ ዳሰሳ 21 ቢሊዮን 336 ሚሊዮን የተፈጥሮ ጋዝ ተገኝቷል። ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በክልሉ ኦጋዴን አካባቢ ያለውን ሀብት በተገቢው መልኩ ለመጠቀም በስፋት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ከመግለጻቸው ባለፈ ማን እየሰራው እንደሆነና ስራው ምን ደረጃ እንዳለ አላስታወቁም።
በአካባቢው ትልቅ ሀብት እንዳለ መረጋገጡን ያነሱት አቶ ሚሊዮን ፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያ በስድስት ቦታዎች ላይ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ኦጋዴን፣ መቀሌ፣ መተማ፣ ደቡብ ኦሞ እንዲሁም ጋምቤላ አካባቢዎች በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል፡፡
ወደፊት ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠል ከቻለ አሁን ከተገኘው እጥፍ በላይ ማግኘት እንደሚቻል የሚጠቁሙ መረጃዎች እንዳሉም ነው አቶ ሚሊዮን ያመላከቱት፡፡
እንደ አቶ ሚሊዮን ገለጻ፤ በክልሉ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በቅርብ ዓመታት ወደ ምርት ለማስገባት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ሌሎች በፍለጋ ምዕራፍ ላይ ያሉትም በአጭር ጊዜ ውጤታማ የሚሆኑበትን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በተጨማሪም የተጀመረው ፍለጋ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የተጀመረውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የማዕድን ዘርፍ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግ ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው ዋና ዋና ዘርፎች መካከል እንዱ በመሆኑ በተገቢው መንገድ ኪኮኖሚውን እንዲደግፍ ትኩረት መደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡
እንደ አቶ ሚሊዮን ገለፃ፤ ለአንድ ሀገር ልማት የተለያየ የኃይል አማራጭ ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ማዕድናት በተገቢው መልኩ ማልማት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ልማትን ከማጎልበት ጎን ለጎን በጂኦ-ተርማል ዘርፍ ያላትን ከፍተኛ አቅም ለኃይል አማራጭ ለማዋል እየሠራች እንደምትገኝ አያይዘው የገለጹት አቶ ሚሊዮን፤ ከክልሎችና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በተለይ ጂኦ-ተርማልና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ዘርፎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ከመደገፋቸው በተጨማሪ ለወደፊት ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡