የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ በጣለው የቪዛ መጠየቂያ ገደብ ዙሪያ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደቀጠሉ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።
ይህን ያስታወቁት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
የአውሮፓ ህብረት በቅርቡ ኢትዮጵያን በሚመለከት ባወጣው የቪዛ ገደብ ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መሆኑን፣ የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የማጣራቱ ስራ እና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ውይይቶች እንደቀጠሉ መሆኑንም አምባሳደር ነብዩ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
እሳቸው ዝርዝር ባይገልጹም በአውሮፓ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማቆያ ቆይተው ለጊዜው ወደ ካምፕ የተመለሱ እንዳሉት አብዛኞቹ ጥገኝንተ በጠየቁበት አገር “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚል ህጋዊ የማንነት ማረጋገጫ አልሰጡም።
አገራቱ በራሳቸው ማጣራት ” ኢትዮጵያዊ” ይበሏቸው እንጂ በሰነድ የተደገፈ መረጃ ባለመኖሩ መንግስት ሊቀበል እንደማይችል በማስታወቁ ነው የቪዛ ገደብ የተጣለው። መንግስት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በሰነድ ላልተረጋገጠ ዜጎች ጊዜያዊ የጉዞ ሰነድ “ኢትዮጵያዊ ናቸው” ብሎ እንዲሰጥ ጫና ያሳደረው የአውሮፓ ህብረት ከውሳኔ የደረሰበት አግባብ በህግ የሚደገፍ እንዳልሆነ ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
በሌላ ዜና “አዲሱ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ ህግ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዲያስፖራዎችን ይጎዳል?”ረቂቅ ህግ በተለይም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ላይ ስጋት መደቀኑን፣ ኢትዮጵያ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊጎዳ አይችልም? ዲያስፖራዎችን ዒላማ ያደረገ ይመስላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር ነብዩ፣ “ህጉ ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ ነው፣ እንደ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እኛም ገና አላየነውም፣ ረቂቅ ህጉ ከዲያስፖራዎች ጋር በተመለከት ጉዳት ካለው አስተያየት የምንሰጥበት ይሆናል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አዲሱ ረቂቅ ህግ ወደኋላ አስር ዓመት ወደ ሁዋላ ተመልሶ እንዲሰራ ያዛል። አንድ ሰው ከሚታወቀው አቅሙ በላይ በተለየ ሁኔታ ንብረቱን ካፈራ ንብረቱን በህጋዊ መንገድ ስለማግኘቱ ለፍርድ ቤት እንዲያስረዳ የሚያስረዳ ነው።
እንዲሁም ንብረቱ በህጋዊ መንገድ ስለመፈራቱ የሚያስረዳ ህጋዊ ማስረጃ ካልተገኘ መንግሥት ንብረቱን የመውረስ መብት እንደሚሰጠው በረቂቅ ህጉ ሰፍሯል።
“ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል በተካሄዱት ሥብሠባዎች ስኬታማ ውይይቶችን አድርጋለች” በሚል አምባሳደር ነብዩ ተድላ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በሳምንቱ የተከናወኑ ዐበይት የዲፕሎማሲ ተግባራትን እና ቀጣይ ሥራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኀን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ በሩሲያ በተካሄደው ሦስተኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ሥብሠባ ላይ በብሔራዊ ባንክ ገዥ እና በብሪክስ የኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ የሚመራ ልዑክ በሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በሦስተኛው የብሪክስ አባል ሀገራት ተወካዮች ሥብሠባ ላይ በተለዋዋጭ እና ሊተነበይ በማይቻል የዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚክ ምህዳር ውስጥ የብሪክስ ሀገራትን እና ሃብቶችን በማሠባሠብ ዓለም አቀፍ ተግዳሮትን በአጋርነት መቅረፍ እንደሚገባ ነው ያስገነዘበችው።
የብሪክስ አባል ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እንዲሁም በሌሎች መስኮች የኢኮኖሚ ግንኙነትን በማሳደግ እና የልማት ፋይናንስን በመጨመር ዘላቂ ልማትን መደገፍ አስፈላጊ እንደኾነም መልዕክት መተላለፉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በብሪክስ ተሳትፎ የጎላ ሚና መወጣት እንደምትችል ገለጻ ተደርጓል። ዕውነተኛ ዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መኾኑም አጽንኦት ተሰጥቷል ነው ያሉት።
የታዳጊ ሀገራትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከ190 በላይ ሀገራት በተመድ መምከር የሚችሉበት ዕድል ስላለ ሀገራት በጎንዮሽ የሚያደርጉት መጓሻሸሞች አዋጭ እንዳልኾኑ በኢትዮጵያ በኩል ተነስቷል፤ ኢትዮጵያም ለባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ትኩረት ትሰጣለችም ብለዋል።
ከብሪክስ ሥብሠባ በተጓዳኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከስምንት አባል ሀገራት እና ተጋባዥ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ቀጣይነት ያለው ትብብርን ማጠናከር የሚያስችል ምክክር መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ኢትዮጵያ በስትራቴጂክ ትብብር የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል ስኬታማ ምክክር ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በውይይቶቹም ኢትዮጵያ የአዲሱ የብሪክስ ልማት ባንክ አባል እንድትኾን የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ድጋፍ የሚያደርጉ መኾኑን ማረጋገጫ እንደሰጡ አንስተዋል።
በሩሲያ በተካሄደው ሦስተኛው የብሪክስ የአባል ሀገራት ሥብሠባ ኢትዮጵያ የብሪክስ ማዕቀፍ ጥምረት ንቁ ተዋናይ እየኾኑ ከመጡ ሀገራት መካከል አንዷ መኾን ችላለች ብለዋል።
“የጋራ ሃብቶች ለጋራ እጣፈንታ እና ብልጽግና፣ የዓባይ ወንዝ ፍትሐሂ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ለትብብር እና ቀጣናዊ ውህደት” በሚል መሪ መልዕክት ሦስተኛው ዓመታዊ የቀጣናዊ ውህደት እና የዓባይ ወንዝ ምክንያታዊ አጠቃቀም መድረክ (አፍሪራን) በአዲስ አበባ መካሄዱን ገልጸዋል።
በሳምንቱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምሥጋኑ አረጋ ከተለያዩ ሀገራት የሥራ ኀላፊዎች፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ካደረጉ አምባሳደሮች ጋር ስኬታማ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ምክክር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዜናው ከማህበራዊ ሚዲያ፣ አሚኮና ከናትናኤል ተሰባስቦ የቀረበ ነው