በጂግጂጋ ከተማ እና በተቀሩት ዞኖች ከ230 በላይ የአግሮ ፕሮሰሲንግ (የወተትና የመኖ ማቀናባበሪያዎች) የመጠጥ ውሃ ፣ የቆርቆሮ ማምረቻ፣ የመኪና መገጣጠሚያ፣ የአምነበረድ ፋብሪካ፣ የሮቶ ፣ የፍራሽና ሌሎች በርካታ ፋብሪካዎችም ተከፍተው ስራ ጀምረዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በክልሉ ለተሠማራው የጋዜጠኛ ቡድን እንደገለጹት ፤ ክልሉ ያገኘውን ሰላም ተከትሎ የኢንቨስተሮች ቁጥር እያደገ መጥቷል። ከለውጡ በኋላ ባሉት ስድስት ዓመታት ብቻ በክልሉ ከ230 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ፋብሪካዎች ተከፍተዋል።
ቀደም ሲል በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ይህ ነው የሚባል ሥራ እንዳልነበር የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ፤ ለዚህም ምክንያቶቹ፣ የሰላም እጦት ፣ የኢንቨስተሩ ዋስትና ማጣት እንዲሁም የነበረው መንግሥት ለኢንቨስትመንት ትኩረት አለመስጠቱ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት ከለውጡ በፊት በክልሉ አጠቃላይ የነበሩት ፋብሪካዎች ብዛት ከ85 የማይበልጥ እንደነበር ብለዋል።
ከለውጡ በኋላ በጂግጂጋ ከተማ እና በተቀሩት ዞኖች ከ230 በላይ የአግሮ ፕሮሰሲንግ (የወተትና የመኖ ማቀናባበሪያዎች) የመጠጥ ውሃ ፣ የቆርቆሮ ማምረቻ፣ የመኪና መገጣጠሚያ፣ የአምነበረድ ፋብሪካ፣ የሮቶ ፣ የፍራሽና ሌሎች በርካታ ፋብሪካዎችም መከፈታቸውን አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ከ 318 በላይ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አክለዋል።
የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ፣ ምርታማነትን በማሳደግና የሥራ እድል በመፍጠር ለክልሉ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛልም ብለዋል።
በቅርቡ በጂግጂጋ ከተማ ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው “Suweyas Motors Company” ክልሉ አሁንም በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን መነቃቃት የሚያሳይ መሆኑን እንደ አብነት ጠቅሰዋል።
የሲዌስ ሞተር ካምፓኒ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ኢብራሂም በበኩላቸው ፋብሪካውን ለመገንባት ብቻ 250 ሚሊዮን ብር እንደፈጀ ተናግረዋል። ሥራ ከጀመረ የሁለት ሳምንት ዕድሜ ያስቆጠረው ፋበሪካው በቀን አምስት መኪኖችን እየገጣጠመ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርብ መሆኑንም ገልጸዋል። እስከ አሁንም 40 JETOUR እና 12 SUZUKI DIZIRE መኪኖችን ገጣጥሞ ለገበያ እንዳዋለ ገልጸዋል።
ከፍተኛ የግዢ ፍላጎት እንዳለ የተናገሩት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ቅድመ ክፍያ ፈጽመው ለመግዛት ወረፋ የያዙ ሰዎች በርካታ ስለመሆናቸውም አንስቷል። ካምፓኒው የሀገር ውስጥ የመኪና አቅርቦት ፍላጎትን ማሟላት ብቻ ሳይሆን መኪኖችን ወደ ጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት የማድረግ ራዕይ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበትና ለሦስት መቶ ሰዎችም ቋሚ የሥራ እድል መፍጠሩን አስረድተዋል።
‹‹ሳሂድ ሜታል ኢንዱስትሪ ኢንጂነሪንግ›› ሌላው በጂግጂጋ ከተማ የተመለከትነው የከባድ መኪኖች ቦዲ ማምረቻ እና መገጣጠሚያ ካምፓኒ ነው። አቶ ነስር ያሲን የካምፓኒው ማርኬቲንግ ክፍል ሃላፊ እንደሚያስረዱት፤ ካምፓኒው በራሱ ቅርጽ ማውጫ ማሽኖች ተጠቅሞ የካባድ መኪኖችን ቦዲ፣ ቦቴና የነዳጅ ማደያ ታንከሮችን ይሠራል። ሞተር እና ገቢና ብቻ ይዘው ከውጭ የሚመጡ ከባድ መኪኖች የቀረው አካላቸው እዚሁ ተሰርቶና ተገጣጥሞ ሙሉ ሆነው ይወጣሉ ብለዋል። ካምፓኒው ለ270 ሰዎች የሥራ መፍጠሩንም ጠቅሰዋል። በካምፓኒው ውስጥ ከዜሮ ተነስተው ሥራ የጀመሩ ሠራተኞች ዛሬ ሙያ አካብተው ከፍተኛ ተከፋይ እስከ መሆን መብቃታቸውንም ገልጸዋል።