ሕጋዊነት (legalism) በክርስትና ውስጥ ሌላው የግብዝነት እና የኅይማኖታዊ ፈራጅነት መገለጫ:-
ክፍል አንድ ፦
ሰዎች በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት በማመን ክርስቲያን ከሆኑ በኋላ፣ እየኖሩት ባለው የክርስትና ሕይወት ውስጥ በኅይማኖታዊ የጠላትነት ስሜት፣ በፈራጅነት ፣ ሌሎችን ማህበራዊ ተቀባይነት እስከማይኖራቸው በማዋረድ ፣ በርኅራሄ ማጣት እና በይቅር አልባይነት ሕይወት እንዲመላለሱ ከሚያደርጋቸው ችግር ውስጥ አንዱ የሕጋዊነት (legalistic ) አስተሳሰብ እና ልምምድ ነው። አስተሳሰቡ ጽንፍ ሲረግጥ አደገኛ ነገሮችን ያስደርጋል። አለፍም ሲል በእውነት ላይ ያልቆመ የኅይማኖታዊ አክራሪነት ስሜት ውስጥ ሊከት ይችላል። ክርስቶስን እንዲሞት ለሮማውያን አሳልፈው የሰጡት ለሕጋቸው የቀኑ አይሁዳውያን እግዚአብሔርን ያገለገሉ ስለመሰላቸው ነበር።
ወንጌል እና በወንጌል አማካኝነት የሚገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ምንነት ካልገባን፣ አስተሳሰቡ ማንንም ሰው አይምርም ። የትኛውንም ክርስቲያን የተማረ ይሁን ፣ ያልተማረ፤ የሥነ- መለኮት ሊቅ ይሁን ፈላስፋ፤ አዲስ ክርስቲያን ይሁን ወይም ነባር የሚለው አሳሳቢ አይደለም ። የወንጌል እውነት ያልገባውና የእግዚአብሔርን ጸጋ ምንነት ያልተረዳ ሁሉ የአስተሳሰቡ ሰለባ ሊሆን ይችላል። ጌታ ካልረዳ የሕጋዊነት (legalistic ) ባህሪይ ማንንም ሰው በኅይማኖታዊ ቀናኒነት ግብዝ ፈራጅ ያደርጋል። ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያውያን የወንጌል አማኞች ዘንድም በስፋት ይስተዋላል።
በክርስትና እምነት ልምምድ ውስጥ ያለው ህጋዊነት (legalistic)አካሄድ ብዙ ጊዜ በብዙ ነገሮች ማለትም በስነ-ልቦና እና በስነ-መለኮት የሚመራ ነው ሲሉ ምሁራን ይናገራሉ:: በዛሬው ጹሁፌ ደግሞ ከሥነ-መለኮት እይታ አኳያ ስለ ህጋዊነት (legalistic) አስተሳሰብ አንዳንድ ቁልፍ ነጥቦችን ላነሳላችሁ ወደድሁ:: በትእግስት አብረን እንቀጥል::
የሕጋዊነት (legalistic ) ምንድነው?
ሥነ መለኮታዊ ትርጓሜ :-
በሥነ-መለኮት አውድ ውስጥ፣ ሕጋዊነት (legalism) በሕግ ወይም በሥነ ምግባር ደንቦች ላይ ከልክ በላይ ማጉላትን : መፅነፍ እንዲሁም ባልታወቀ ወይም በተሰወረ መንገድ የሕግን ባህሪይ እየተገበሩ በግብዝነትና በፈራጅነት ልብ ጸጋን እና ምሕረትን፣ መግፋት የሚል ትርጓሜን ይይዛል። ይህ ዓይነቱ የሕጋዊነት ልምምድ ሕጉን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት የሚመነጭ ነው (Misunderstanding of the Law) ።
የትኛውንም ኅይማኖታዊ አስተሳሰብ ወደ ትግበራ ከማምጣታችን በፊት ከሥነ-መለኮታዊ አተያይ ( Theological Perspective) አንጻር የኪዳናት ልዩነት መኖሩን መረዳት ያስፈልጋል። በአንድ ነገር ላይ ያለን ቅድሜ ግንዛቤ አተገባበራችን ላይ በቀጥታ ወይም በተዝዋዋሪ ይንጸባረቃል። በብሉይ ኪዳን ሕጉ በመልአክት መካከለኝነት በሙሴ በኩል ለእስራኤላውያን የተሰጠ ቃል ኪዳን ነበር (ዘጸ 19-20)። ነገር ግን፣ በአዲስ ኪዳን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት አዲስ የጸጋ ቃል ኪዳንን አምጥቷል (ዕብ. 8፡6-13)።
በእምነት መጽደቅ ወይም መዳን የተጅመረው አብርሃም ጋር ነው። እግዚአብሔር በእምነት መጽደቀን ወይም በእምነት አማካይነት በጸጋ መዳንን አብርሃም ዘመን አደረገና ሕጉን ከ430 ዓመት በኋላ በሙሴ ዘመን አደረገው። ሕግ በእምነት ከመጽደቅ በፊት ተሰጥቶ ቢሆን ወይም በጸጋ መዳን ከህግ በኃላ ቢሆን ኖሮ የሰው ልጅ ድነት በእምነት በጸጋ አማካይነት መሆኑ አስተማማኝ አይሆንም ነበር::
እግዚአብሄር በቀደመው ኪዳን ሕጉን ሰጥቶ የነበረበት ዓላማ ፣ ሰዎች ጠብቀውት እንዲድኑ ሳይሆን ፣ ይልቁንም በሕጉ አማካይነት ኅጢአተኞች ፣ ኩነኔ የወደቀባቸው የፍርድ እና የሞት ልጆች መሆናቸውን እየነገረ አዳኝ የሚያስፈልጋቸው መሆናችንን ይገነዘቡ ዘንድ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሕጉ አዳኝ እንደሚያስፈልገን እያሳየ ወደ ክርስቶስ የሚመራን ሞግዚት መሆኑን በገላ 3፡24-25 ባለው ክፍል ላይ ተናግሯል ።
የገላትያ አማኞች በክርስቶስ ጸጋ እነርሱን ከጠራቸው ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል ማለትም ክርስቶስ ሲደመር መገረዝ ይሆናል ጽድቅ ወይም መዳን ወደ ሚል አስተሳሰብ ዘወር እንዳሉ፣ እንዲሁ አንድ አማኝም በኢየሱስ ክርስቶስ ብቼኛ አዳኝነት በማመን ከዳነ በኃላ ፣ ወደ ሕጋዊነት ማለትም የሕግን ሥራ በማድረግ እግዚአብሔርን ላስደስትና ልቀደስ እችላለሁ ወደሚል አስተሳሰብና ተግባር ሊገባ ይችላል ። ሕጋዊነት መነሻው የሰው ልብ ነው: ጸጋ ግን ምንጩ እግዚአብሔር ነው:: አንድ አማኝ እንዴት የሕጋዊነት አስተሳሰብና ተግባር ሊንፀባረቅበት ይችላል? ለዚህ ከዚህ በታች የማነሳቸው ስምንት ነጥቦች እንደ ዋና ምክንያት ተጠቃሾች ናቸው።
- የማረጋገጫ ፍላጎት ( Desire for Assurance)፦
- በባህልና በኅይማኖታዊ ዳራ (Cultural or Religious Background) :
- በቅዱሳት መጽሃፍት የተሳሳተ ትርጓሜ(Misinterpretation of Scripture):
- የህጋዊ አስተምህሮዎች ተጽእኖ( Influence of Legalistic Teachings):
- ለመንፈሳዊ እድገት ባለ መሻት (Desire for Spiritual Growth):
- ለፍርድ ባለ ፍራቻ( Fear of Judgment):
- የእኩዮች ጫና እና የማህበረሰቡ ተስፋዎች( Peer Pressure and Community Expectation):
- የእግዚአብሔር ጸጋ ምንነት ካለመረዳት ችግር(Lack of Understanding of Grace) ::
የሕጋዊነት (legalism) አስተሳሰብ እና ሕይወት ያላቸው ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ፣ እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉት እግዚአብሔርን ለማስደሰት እና የጽድቅ ህይወት ለመኖር ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት የተነሳ ነው ። ይህ የራሳቸውን ጽድቅ ከሌላው በተሻለ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ሳያውቁት፣ የአንጻራዊነት ምልከታ ውስጥ ስለሚከታቸው ሕግ እና ኅይማኖታዊ ወግ ተስቷል ባሉበት ነገር ሁሉ ወደ ሌሎች ጨካኝ ፈራጅ ያደርጋቸዋል።
በሶሻል ሚድያ ላይ በጥቂቱ ተገልጠው የምንመለከተው ኅይማኖታዊ ጨካኝ ፈራጅነትና አረመኔነት የሞላበት አካሄድ ፣በአገራችን ያሉ የአንዳንድ ወንጌላዊያን አማኖችን ልብ ምን ዓይነት መሆኑን ማሳያ ናሙና ( Sample) ሊሆን ይችላል ። እንዲህ ዓይነት የአማኖች አካሄድ የመጨረሻ ትኩረታቸውን ከእግዚአብሔር ጸጋ እና መንፈስ ቅዱስን ወደ ሰው ጥረት እና አፈጻጸም ስለሚቀይረው፣ ሕይወታቸውን በመንፈስ ጅምሮ በሥጋ፤ በጸጋ ጅምሮ በሕግ የመደምደም ያደርገዋል ።
ለዛሬ አበቃሁ !!
ሰናይ ሰንበት
Via – ነቢዩ ነኝ