በመንግስት ተቋማት ላይ በተካሄደ የኦዲት ምርመራ ከህግና መመሪያ ውጭ ክፍያ የፈጸሙ፣ በተቋማቸው ለማይገኙና ለተሰናበቱ ሰራተኞች ደመወዝ የሚከፍሉ፣ ከበጀታቸው በላይ እላፊ የተጠቀሙ፣ ያለ አማካሪ መሃንዲስ ማረጋገጫ ክፍያ የፈጸሙ፣ ለማን እንደሚከፍሉ የማያውቁ፣ እላፊ የከፈሉና የመሳሰሉትን ዝርዝር ጉዳዮች ያካተተ ሪፖርት ቀረበ፣ ተመላሽ እንዲሆን የተባለ ገንዘብ አስራ አንድ በመቶ ብቻ መመለሱ ተመልክቷል። የሪፖርቱ አቅራቢዎችና ምክር ቤቱ ጥፋት በፈጸሙት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ጥያቄ አቅርበዋል።
በዘጠና ሁለት መስሪያ ቤቶች ላይ በተደረገ የኦዲት ግኝት መሰረት ተመላሽ እንዲያደርጉ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት 443 ሚሊየን 23 ሺህ 846 ብር ከ91 ሣንቲም፣ እንዲሁም 23 ሺህ 55 ዶላር ውስጥ የተመለሰው 48 ሚሊየን 217 ሺህ 965 ብር ከ67 ሣንቲም ብቻ መሆኑ ጠቅሰው የፌደራል ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት አድርገዋል።

ዋና ኦዲተር በተቋማቸው የተከናወኑ ሥራዎችን ሪፖርት ሲያቀርቡ እንዳሉት የተመለሰው ገንዘብ ሊመለስ ከሚገባው ውስጥ አስራ አንድ በመቶ ብቻ ነው። ይህም ከሚጠበቀው አንጻር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ተመልክቷል።
በሪፖርቱ በባለበጀት መስሪያ ቤቶች በኩል ርምጃ እስከመውሰድ የሚደርስ መሻሻሎች መኖራቸውን ቢገለጽም ነገር ግን ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት ግኝት እና ብር ተመላሽ ያላደረጉ መስሪያ ቤቶች ላይ ምክር ቤቱ ርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ ቀርቧል።
በዚሁ መሰረት ምክር በ2014 በጀት ዓመት በዋና ኦዲተር በኦዲት ግኝት መሰረት ብር ተመላሽ እንዲያደርጉ አስተያየት የተሰጠባቸውና ተመላሽ ያላደረጉ ተቋማት ላይ ተጠያቂነትን እንዲሰፍን ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
የበጀት አጠቃቀምን አስመልክቶ በሪፖርቱ እላፊ በጀት የበሉ
ተቋሙ ኦዲት ካደረጋቸው መስሪያ ቤቶች መካከል የተፈቀደላቸውን በጀት በስራ ላይ ያዋሉት ሂሳብ ሲነጻጸር ከበጀት በላይ ወጪ የተደረገበት ሆኖ ተገኝቷ። በርካታ ደግሞ ስራ ያልተሰራበት በጀት ተመዝግቦባቸዋል።
በ20 መ/ቤቶች በልዩ ልዩ የሂሳብ መደቦች በደንቡ መሰረት ሳያስፈቅዱ ለእያንዳንዱ የበጀት ኮድ ከተደለደለው በላይ ወጪ የሆነ ሂሳብ ከመደበኛው በጀት ብር 524. 7 ሚሊዮን ፣ ከውስጥ ገቢ 288.9 ሚሊዮን ፣ ከካፒታል በጀት 489.4 ሚሊዮን በድምሩ 1.3 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል።
በኮድ ከተደለደለው በጀት በላይ ውጭ ያደረጉ ዋና ዋና መ/ቤቶችን ሪፖርቱ ዘርዝሮ አቅርቧል። በዚሁ ዝርዝር አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች እላፊ ሃብት መጠቀማቸው ተገልጿል
- ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 322.5 ሚሊዮን
- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ተጠሪ ተቋማቱ 267.9 ሚሊዮን
- ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 173.2 ሚሊዮን
- ወለጋ ዩኒቨርሲቲ 125.1 ሚሊዮን
- የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት 109.5 ሚሊዮን
- ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 91.3 ሚሊዮን
- አምቦ ዩኒቨርሲቲ 83.3 ሚሊዮን
- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 75.1 ሚሊዮን ሲሆኑ ሁለት መስሪያ ቤቶች ደግሞ 9.7 ሚሊዮን ብር በጀት ስለመኖሩ ሳይረጋገጥና ሳይፈቀድ ክፍያ መፈጸማቸው ተመልክቷል።
ከደንብ ውጭ የተከፈለ ክፍያን በተመለከተ
ከደንብ እና መመሪያ ውጭ የተከፈለ ሃብትን አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርት በ30 መ/ቤቶች ብር 16 ሚሊዮን 470 ሺህ ከደንብና መመሪያ ውጭ አላግባብ ክፍያ መፈጸሙ ይፋ ሆኗል። በዚሁ መሰረት ዋና ዋናዎቹ ተብለው የተጠቀሱት
- ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 3 ሚሊዮን
- የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት 2 ሚሊዮን 889 ሺህ
- ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ 2 ሚሊዮን 42 ሺህ
- መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ 1 ሚሊዮን 156 ሺህ
በተቀጠሩበት መስሪያ ቤት የሌሉና ከስራ ገበታ ለተሰናበቱ ሰራተኞች የተከፈለ ደመወዝ
የኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ይፋ ባደረገው ሌላ መረጃ ደግሞ በአስራ ስድስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያገኛቸው ግኝቶች ናቸው። ስማቸውን ዘርዝሮ ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው 485 ሺህ 183 ከ56 ሳንቲም ገንዘብ ባክኗል። የባከነውም መስሪያ ቤቶች በመስሪያ ቤት ለሌሉና ከስራ ለተሰናበቱ ሰራተኞች ያለማቋረጥ ደመወዝ ይከፍሉ እንደነበር በተገኘ ማስረጃ ነው።
በበልጫ አላግባብ የተከፈለ የመንግስት ሃብትን በተመለከተ
በ32 መ/ቤቶች እና በ9 ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች በተለያዩ የግንባታና ግዥዎች 4.9 ሚሊዮንና ለውሎ አበልና ሌሎች ክፍያዎች 57.6 ሚሊዮን በድምር 62.6 በብልጫ የተመዘገበ የኦዲት ግኝት መኖሩን ተቋሙ አመልክቷል።
የግዥ አዋጅ ደንብና መመሪያ ያልተከተሉ ግዥዎችን አስመልክቶ
በሰባ ሶስት መ/ቤቶች እና በ15 ቅ/ጽቤቶች ብር 2 ቢሊዮን 199 ሚሊዮን የመንግስት ግዥ አዋጅ ደንብ እና መመሪያን ሳይከተል ግዥ ተፈጽሟል። ይህ የተለመደና ሊታረም ያልቻለ አሰራር
- በጨረታ መግዛት ሲገባው ያለጨረታ በቀጥታ የተፈጸመ ግዥ 1.8 ቢሊዮን ብር
- መስፈርት ሳይሟላ በውስን ጨረታ የተገዛ 104.3 ሚሊዮን ብር
- ግልጽ ጨረታ መውጣት ሲገባው በዋጋ ማወዳደሪያ የተፈጸመ 96.1 ሚሊዮን ብር
- የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ በቀጥታ የተፈጸመ ግዥ 13.8 ሚሊዮን ብር
- ሌሎች የግዥ ሂደት ያልተከተሉ 134.6 ሚሊዮን ዋና ዋና ናቸው።
ዋና ዋና መስሪያ ቤቶች (ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ ግዥ የፈጸሙ)
- ገቢዎች ሚኒስቴር በዋናው መ/ቤትና በቅርንጫፍ ፅ/ቤት 1.4 ቢሊዮን
- የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት 91 ሚሊዮን
- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 65.5 ሚሊዮን
- የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 62.9 ሚሊዮን
- የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ 57.1 ሚሊዮን
- ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 37.4 ሚሊዮን
- የጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መ/ቤት እና በድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት 34 ሚሊዮን
በአማካሪ መሃንዲሳ ሳይረጋገጥ የተከፈለ ክፍያ
የግንባታ ክፍያ በአማካሪ መሃንዲስ ተረጋግጠው መከፈላቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በ2 መ/ቤቶች 170 ሚሊዮን 394 ሺህ በአማካሪ መሃንዲስ የክፍያ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሳይቀርብ ክፍያ ተፈጽሞ ተገኝቷል። ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 169.7 ሚሊዮን ብር በአማካሪ መሃንዲስ ሳይረጋገጥ ክፍያ ፈጽሞ ተገኝቷል።
የተከፋይ ሂሳብ ፦
በአስራ አራት መ/ቤቶች 1.7 ቢሊዮን ብር በተከፋይ ሂሳብ ተይዞ ተገኝቷል። ይህ ገንዘብ ለማን እንደሚከፈል እንኳን ተለይቶ እንደማይታወቅ ሪፖርቱ ግኝቱን አስቀምጧል። የተከፋይ ሂሳብ ለባለመብት መለየት ካልቻሉ መስሪያ ቤቶች ፦
- የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር 1.5 ቢሊዮን
- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 131.8 ሚሊዮን
- ማዕድን ሚኒስቴር 29.9 ሚሊዮን ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ሪፖርቱ ከፋና አዲስ ዘመንና ቲክቫህ የተሰባሰበ ነው