የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመንግሥት ባንኮች እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደ “ተዛማጅ ወገኖች” እንደሚቆጠሩ ወስኗል። የባንኩ መመሪያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተቋማቱ የሚሰጠውን የብድር መጠን እንዲገድብ የሚያስገድድ ነው። እስከ ጎርጎሮሳዊው 2022/23 ብቻ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 777.8 ቢሊዮን ብር የንግድ ባንክ ዕዳ አለባቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሣምንት “የባንክ ሥራን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አምስት መመሪያዎችን” እንዳሻሻለ አስታውቋል። መመሪዎቹ የተሻሻሉት በብሔራዊው ባንክ መግለጫ መሠረት “በሥራ ላይ ያለውን የባንክ ዘርፍ የቁጥጥር ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መርሆዎች እና ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲሁም የባንክ ዘርፍ ከደረሰበት ዕድገት ጋር የተጣጣመ” ለማድረግ ነው።
የመጀመሪያው ከፍተኛ የብድር ተጋላጭነት ገደብ መመሪያ “አንድ ተበዳሪ ከባንኩ ጋር በገባው ውል መሠረት ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ ምክንያት በባንኩ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ለመቀነስ እና የባንኮች የተጋላጭነት መጠንን በወቅቱ ለመቆጣጠር” ያለመ ነው።
በመመሪያው መሠረት “ማንኛውም ባንክ ለአንድ ወይም ተያያዥነት ላላቸው ደንበኞች” የሚሰጠው ብድር “ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከ25 በመቶ እንዳይበልጥ” ተገድቧል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ “ተያያዥነት ያላቸው አካላት እንደ አንድ የባንክ ተበዳሪ” እንደሚቆጠሩ አስረድተዋል። “አንድ ተበዳሪ ወይም single counter party ሲባል አንድ ተበዳሪ ብቻ ሳይሆን ተበዳሪዎች እርስ በርሳቸው የቁጥጥር ወይም ደግሞ የኤኮኖሚ ግንኙነት ካላቸው እንደ አንድ ተበዳሪ ተቆጥረው ይኸው ከፍተኛ የብድር ጣሪያ ወይም ደግሞ 25 በመቶ ተግባራዊ ይደረጋል” ሲሉ አቶ ፍሬዘር ብሔራዊ ባንክ በቪዲዮ ባሰራጨው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
ባንኮች ባለቤትነት እና የሥራ ግንኙነትን ጨምሮ በተለያየ ሁኔታ ከሚዛመዷቸው አካላት ጋር የሚኖራቸው “የቢዝነስ ግንኙነት የተገደበ” እንዲሁም “ከጥቅም ግጭት ነጻ እንዲሆን” ሁለተኛው መመሪያ ሥራ ላይ እንደዋለ አቶ ፍሬዘር ተናግረዋል። ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት የሚሰጥ የብድር ተጋላጭነት ገደብ መመሪያ ባንኮች ተዛማጅነት ላላቸው አካላት “ብድር አግባብነት በሌለው መንገድ” እንዳይሰጡ ለመቆጣጠር ጭምር የታቀደ ነው።
“አንድ ባንክ ለአንድ ተዛማጅነት ላለው አካል ሊሰጠው የሚችለው ከፍተኛ የብድር መጠን የካፒታሉን 15 በመቶ ብቻ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል” ያሉት አቶ ፍሬዘር “ለተለያዩ ተዛማጅ አካላት ሊሰጥ የሚችል የብድር መጠን በአጠቃላይ ከባንኩ ካፒታል ከ35 በመቶ መብለጥ እንደሌለበት መመሪያው ይደነግጋል” ሲሉ አስረድተዋል።
ሁለተኛው መመመሪያ “አንድ ባንክ ተዛማጅ ከሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ከማናቸውም ተዛማጅ ካልሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ተግባራዊ በሚደረግ ሁኔታዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ እንዲሆን እና ከዚህ በተለየ ሁኔታ እንዳይፈጸም ይደነግጋል።” በመመሪያው መሠረት ከዚህ በኋላ የመንግሥት ባንኮች እና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደ ተዛማጅ ወገኖች ይቆጠራሉ።
በመንግሥት ባንኮች እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል “ከዚህ በፊት ምንም ድንበሩ አይታወቅም ነበር” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “ብዙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የብድር አሰጣጥ ከግል ተበዳሪ የተለየ” ሆኖ መቆየቱን ያስረዳሉ።
“አሁን ግን ያ ነገር ቀርቶ ልክ እንደ ማንኛውም እንደ ግል ተበዳሪ ተዛማጅ ወገን ስለሆነ ያ መመሪያ ተግባራዊ ይደረግባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “ከአሁን በኋላ በአንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት እና በንግድ ባንክ መካከል የሚኖረው አጠቃላይ የብድርም ይሁን ሌሎች ግንኙነቶች በገበያ የሚመራ” እንዲሆን መወሰኑም “ለወደፊት ጥሩ ነው” የሚል ዕምነት አላቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሦስተኛ መመሪያ የንብረት ምደባ እና ለተዛማጅ ስጋቶች ስለሚያዝ መጠባበቂያን የተመለከተ ነው። መመሪያው ከአንድ ባንክ ካፒታል “ከአምስት በመቶ በላይ የሆኑትን እና የውል ማሻሻያ የተደረገባቸውን ብድሮች አጠቃላይ መረጃ በየጊዜው ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንዲደረግ ያስገድዳል።”
“አንድ ወቅቱን ጠብቆ መከፈል ያልቻለ እና ለተበላሸ ብድር የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላ ብድር ለብድሩ መያዣነት የቀረበው ዋስትና ምንም ይሁን ምን እንደ ተበላሸ ብድር ተወስዶ ወለድ የማይከፈልበት ምድብ ውስጥ መካተት” እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግለጫ ይጠቁማል።
“አንድ ተበዳሪ ከአንድ ባንክ የተለያዩ ብድሮችን የወሰደ ከሆነ እና ከብድሮቹ አንዱ የተበላሸ ከሆነ ይህ የተበላሸው ብድር ባንኩ ለደንበኛው ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ወይም ተጋላጭነት 20 በመቶ እና ከዛ በላይ ከሆነ ሁሉም ብድሮች ወዲያውኑ በተበላሸ ብድር መደብ ውስጥ ይካተታሉ።”
ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሚያዝያ ይፋ ባደረገው የፋይናንስ ዘርፉን የተመለከተ ሪፖርት የሀገሪቱን ባንኮች በሦስት ጎራ ከፍሏቸዋል። እስከ ሰኔ 2015 ድረስ ከባንኮች ጠቅላላ ንብረት 49.5 በመቶ ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ግዙፍ” ተብሎ በብሔራዊ ባንክ የተመደበ ብቸኛ ባንክ ነው። ንግድ ባንክ በገበያው በጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 48.7 በመቶ ድርሻ አለው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት ባንኮች የሰጡት ብድር “በጥቂት ትላልቅ ተበዳሪዎች እጅ እንደተከማቸ” ይፋ አድርጓል። እስከ ሰኔ 2015 ባንኮች ከሰጡት አጠቃላይ ብድር 23.5 በመቶው ለአስር ተበዳሪዎች ብቻ የተሰጠ ነው። መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ያለው ከፍተኛ ድርሻ እና የብድር ክምችት ብሔራዊ ባንክ አሁን ሥራ ላይ ላዋላቸው መመሪያዎች ዋና ገፊ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ዶክተር አብዱልመናን ይናገራሉ።
ይሁንና “ንግድ ባንክ ለተወሰኑ የልማት ድርጅቶች የባንኩን እጥፍ፣ እጥፍ፣ እጥፍ ካፒታል የሚያህል ብድር ሰጥቷል” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “እሱን ምንም ሊያደርገው አይችልም። የሆነ መፍትሔ ካልተፈለገለት በስተቀር” ሲሉ መመሪያዎቹ ወደ ኋላ ተመልሰው የተፈጠረውን ችግር ሊቀይሩ እንደማይችሉ አስረድተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽንን አቋቁሞ ስድስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ በነሐሴ 2013 አስረክቦት ነበር። ኮርፖሬሽኑ የተሸከመውን ብድር ከመንግሥት የልማት ድጅቶች ሽያጭ ለመክፈል ቢታቀድም የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እንዳሉት “በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት” ባለመሳካቱ “ንግድ ባንክ ላይ ጫና አምጥቷል።”
በመንግሥት ውሳኔ ወደ ዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ብድራቸው በቀዳሚነት የተዘዋወረላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የኬሚካል ኢንዱስትሪ ነበሩ።
ተቋሙ በመጀመሪያው ዙር 398.7 ቢሊዮን ብር የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ብድር ተረክቧል። እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር ሠነድ መሠረት በሰኔ 2015 ወደ የዕዳ እና ሀብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የተዘዋወረው አጠቃላይ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብድር 540 ቢሊዮን ብር ነው።
እስከ ጎርጎሮሳዊው 2022/23 ብቻ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 777.8 ቢሊዮን ብር የንግድ ባንክ ዕዳ እንዳለባቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ሰነድ ያሳያል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን የመሳሰሉ ተቋማት በመንግሥት ዋስትና ከውጪ ጭምር በመበደራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አጠቃላይ ብድር ወደ 900 ቢሊዮን ብር ገደማ አሻቅቧል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አበዳሪ በዋናነት የመንግሥት ንብረት የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ከፌድራል መንግሥት አጠቃላይ ብድር 48 በመቶ ድርሻ አለው።
ዶክተር አብዱልመናን “ይኸ ሁሉ ዕዳ ሳይጠራቀም ይኸ መመሪያ ወጥቶ በተግባር ውሎ ቢሆን ኖሮ” አሁን የተፈጠረውን ችግር መቆጣጠር ይቻል እንደነበር ያምናሉ። “አሁን ችግሮች በጣም ገዝፈው ከወጡ በኋላ ጥሩ ነው ነገር ግን የሚፈታው ያለፈ ችግር አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በግል ባንኮች ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር እና ክትትል ጥብቅ ቢሆንም በንግድ ባንክ ረገድ “ዳተኛ ነው” ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን ይተቻሉ። በባንኩ “መካከለኛ” እና “ትንሽ” በሚሉ ሁለት ምድቦች የሚገኙት የግል ባንኮች በአጠቃላይ ሀብት፣ በተቀማጭ እና በካፒታል ከንግድ ባንክ ጋር የሚወዳደሩ አይደሉም።
ለምሳሌ ያክል በብሔራዊ ባንክ “መካከለኛ” በሚለው ጎራ የተመደቡ አምስት ባንኮች በጋራ ካፒታል ከገበያው ያላቸው ድርሻ 31 በመቶ ነው። የባንኮቹ ተቀማጭ 29.4 በመቶ ሲሆን ጠቅላላ ሀብታቸው ደግሞ 28 በመቶ ነው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት የግል ባንኮች “ሊያደርሱት የሚችሉትም ሆነ እስካሁን ያደረሱት ጉዳት በጣም ትንሽ ነው።”
ዶክተር አብዱልመናን ብሔራዊ ባንክ “የመንግሥትንም ባንክ የግልንም ባንክ በዕኩል ሁኔታ እንዲቆጣጠር እና እንዲከታተል ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ ባንክ ያስፈልጋል” ሲሉ ይሞግታሉ። “የብሔራዊ ባንክ ነጻ አለመሆኑ ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን እንዲያደርግ” መንገድ እንደከፈተ የሚናገሩት ዶክተር አብዱልመናን መንግሥት ዋስትና የገባላቸው ብድሮች የብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች የማይመለከታቸው እንዲሆኑ የተደረገው ብሔራዊው ባንክ እያወቀ፤ ፈቅዶ መሆኑ አጥብቀው የሚተቹት ነው።
ይህ አሰራር “የተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከንግድ ባንክ ካፒታል በላይ በጣም ትልቅ ገንዘብ [በብድር] ወስደው” ሀገሪቱን ችግር ውስጥ ከጣሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለመሆን መብቃታቸውን የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ባንኮች “ብቁ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለቤቶች፣ ዳይሬክተሮች እና ሥራ አስፈፃሚዎች” እንዲኖሯቸው የሚደነግግ በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ላላቸው ሰዎች የሚውሉ መስፈርቶች መመሪያ ሥራ ላይ አውሏል። “ገለልተኛ የሆኑ ግለሰቦች በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት የሚካተቱበትን አስገዳጅ ሁኔታ” የሚደነግገው የኩባንያ አስተዳደር መመሪያ አምስተኛው ነው። በአዲሱ መመሪያ ባንኮች “ቢያንስ ሁለት ሴቶች በቦርድ አባልነት” ማካተት አለባቸው።
Source DW amharic