ለሴቶች የዘጠኝ ወር እርግዝና ቀላል አይደለም።
በተለይም ለአንዳንዶች፤ ወራቶቹን በሙሉ በህመም ነው የሚያሳልፉት።
ተደጋጋሚ ማጥወልወል፣ ማቅለሽለሸ፣ ማስታወክ እንዲሁ ሌላም. . . ።
እስካሁን ድረስ ሳይንቲስቶች ለእነዚህ ነፍሰጡሮች ፈውስን ማግኘት ሳይሆን ምክንያቱንም በጥልቀት እንዲሁም በቅጡ አልተረዱትም ነበር።
በቅርቡ ግን ይህ የሚቀይር ሁኔታ ተፈጥሯል።
ሳይንቲስቶች አንዳንድ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ለምን በከፋ ህመም እንደሚሰቃዩ ምክንያቱን ደርሰውበታል።
ይህም ግኝት አንድ እርምጃ ፈውሱን ወደ ማግኘት ያስጠጋ ነው ተብሏል።
ጥናቱ እንደሚያሳየው ጽንሱ ሃይፐርሜሲስ ግራቪዳረም (ኤችጂ) የተሰኘውን በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ከፍተኛ ማጥወልወል እና ማስመለስ እናቶች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሆርሞኖችን እንደሚያመነጭ ነው።
ስለዚህ ተመራማሪዎቹ ለሴቶች ከእርግዝናቸው በፊት እነዚህን ህመሞች ሊያስከትል የሚችለውን ጂዲኤፍ 15 የተሰኘውን ሆርሞን ማጋለጥ መፍትሔ ሊሆን ይችላል እያሉ ነው።
“ነፍሰጡር ሴት ለዚህ ሆርሞን የበለጠ ተጋላጭ ከሆነች ትታመማለች” ሲሉም የካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሰር ስቴፈን ኦ ራሂሊ ተናግረዋል።
አክለውም “መንስዔውን ማወቃችን ይህ በእርግዝና ወቅት እንዳይከሰት እንዴት መከላከል እንደምንችል ፍንጭ ይሰጠናል” ይላሉ።
በርካታ ነፍሰ ጡሮችን የሚያሰቃየው ይህ ህመም ከ10ሩ ውስጥ በስምንቱ ላይ የሚከሰት ነው።
ይህ ህመም የጽንሱንም ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ሲሆን፣ በርካታ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ከፍተኛ ድርቀት ለመከላከልም በደም ስር የሚሰጠው ግሉኮስ ያስፈልጋቸዋል።
አንዳንድ እናቶች በእርግዝና ወቅት በቀን እስከ 50 ጊዜ ይታመሙ እንደነበር ይናገራሉ።
በዝላይ ስፖርት የኦሊምፒክስ ተወዳዳሪ የሆነው እንግሊዛዊው ግሬግ ራዘርፎርድ ባለቤት የ35 ዓመቷ ሱዚ ቨርሪል በእርግዝናዋ ወቅት በከፋ ሁኔታ በመታመሟ ምክንያት ጽንሱን ለማቋረጥ አስባ እንደነበር ታስረዳለች።

የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ሱዚ ከሦስቱ እርግዝናዎቿ መካከል በሁለቱ ወቅት የከፋ ህመም እና ስቃይ አጋጥሟት እንደነበረ ተናግራለች።
“ቤተሰቦቼ አጠገብ መሆን አልችልም ነበር። በጣም አስከፊ በመሆኑም ጽንሶቹን ለማቋረጥ አስቤም ነበር” ስትልም ለቢቢሲ ታስረዳለች።
“ሳላስመልስ መተንፈስ አልችልም ነበር። በሁለቱም እርግዝናዎች ወቅት ለአምስት ወራት ያህልም ከመኝታ ቤቴ መውጣት አልቻልኩም። ዓለም በጣም ትጠባለች። ባለቤቴ ግሬግ ተንከባካቢዬ ሆነ” ብላለች።
“ሁሉንም የሕይወታችሁን አካል ይነካል እናም ሕጻናቱ ከመወለዳቸው በፊት ያሉትን ቀናት በመከራ ተሞልቶ ለማለፍ መሞከር ነው” ስትልም ታስረዳለች።
የዌልስ ልዕልትም በሦስቱም እርግዝናዋ ወቅት ኤችጂ በተሰኘው ህመም ትሰቃይ ነበር። በተለይም በመጀመሪያዋ እርግዝናዋ ወቅት ህመሟ ጠንቶ ሆስፒታል ገብታለች።
ቀደም ሲል የተደረጉ ጥናቶች የእርግዝና ህመም ጂዲኤፍ ከተሰኘው ሆርሞን ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ቢጠቁሙም ነገር ግን ተመራማሪዎች በግንዛቤው ላይ የጎደለ ነገር አለ ይሉ ነበር።
አዲሱ ጥናት የኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ሳይንቲስቶች፣ የስኮትላንድ፣ የአሜሪካ፣ እና የሲሪላንካ ተመራማሪዎችን አሳትፏል።
ኔቸር በተሰኘው ጆርናል የታተመው ይህ ግኝት የህመሙ ሁኔታ የሚወሰነው በማህጸን ውስጥ ከሚመረተው የሆርሞን መጠን፣ እንዲሁም አስቀድሞ ከነበረ ተጋላጭነት ጋር የተያያዘ መሆኑንም አረጋግጧል።
ተመራማሪዎቹ በኬምብሪጅ በሚገኘው የእናቶች ሆስፒታል በሚከተታሉ ሴቶች ላይ ነው ጥናታቸውን ያካሄዱት። በተፈጥሯቸው (በዘረመል መዋቅራቸው) ምክንያት ለኤችጂ ተጋላጭ የሆኑ ነፍሰጡር እናቶች በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የጂዲኤፍ 15 ሆርሞን አናሳ መሆኑን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
ነገር ግን ቤታ ታላስሚያ የተሰኘው (የደም መዛባት) ችግር ያለባቸው ከእርግዝና በፊትም በሰውነታቸው ውስጥ ከፍተኛ ጂዲኤፍ 15 እንዲኖር የሚያደርግ ሲሆን፣ የማቅለሽለሽም ሆነ የማስመለስ ህመሙ አነስተኛ ይሆናል።
“ይህ ሆርሞን በእናቷ አዕምሮ ውስጥ ያለውን ልዩ ተቀባይ እንዳይደርስ መከልከል ይህንን ለማከም ውጤታማ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድ ነው” ሲሉም ፕሮፌሰር ስቴፈን ያስረዳሉ።

ቤድፎርድ ውስጥ የምትኖረውን እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ቪቪን ኩመር በእርግዝናዋ ወቅት በሰዓት አስር ጊዜ ትታመም እንደነበር ታስታውሳለች። የማታስታውክበት ሰዓትም እንቅልፍ ሲወስዳት ብቻ ነበር።
“በዚህ ህመም ውስጥ ካለፋችሁ በጭራሽ ማገገም ከባድ ነው። ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ስሜት አለው” ትላለች።
አክላም “ከዓለም ጋር እንደተቆራረጥኩ ተሰማኝ። መጨረሻው አልገባኝም። ከቤትም መውጣት ፈታኝ ነበር” ስትልም ያለፈችበን ስሜት ታስረዳለች።
“የባለቤቴን እና የእናቴን ድጋፍ በማግኘቴ በጣም ዕድለኛ ነበርኩ። ያለ እነርሱ በእርግዝናው መቀጠል ጥንካሬው ላይኖረኝ ይችላል” ትላለች።
በሦስተኛ እርግዝናዋ ወቅት ህመሟ ጠንቶ ሆስፒታል የገባች ሲሆን፣ በቆየችባቸው ስምንት ቀናት ጽንሱን አጣች።
“የተለያዩ መድኃኒቶች እየወሰድኩ ነበር። ሁሉም ሊፈውሱኝ አልቻሉም። በሚያሳዝን ሁኔታ ሕጻኑ ይህንን ሊቋቋም ስላልቻለ ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም” ትላለች።
በእርግዝና ወቅት በከፍተኛ ህመም የሚሰቃዩ ሴቶችን የሚደግፈው የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሻርለት ሐውደን ይህ የጤና ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ችላ መባሉን ይናገራሉ።
“ተመራማሪዎቹ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመሰግናለሁ። ምክንያቱም የዌልስ ልዕልት በዚህ ህመም መሰቃየቷ እስኪታወቅ ድረስ ዜና እንኳን መሆን አልቻለም ነበር” ይላሉ።
አክለውም “ሰዎች የሚሳቡበት የምርምር መስክ አልነበረም። የሴቶች የእርግዝና ህመም ነው ፤ ታዲያ ለምን ያስጨንቀናል? የሚል ዕሳቤም አለ” ሲሉም ያስረዳሉ።
ምስጋና ለቢቢሲ