ስፔን እስራኤልን በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመክሰስ ደቡብ አፍሪካ የጀመረችውን እንቅስቃሴ ለመቀላቀል የወሰነች የመጀመሪያዋ አውሮፓዊት ሀገር ሆናለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ስፔን ከእውነት ጎን መቆሟን እንደምትቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ዘመቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል እና ከፍተኛ ውድመት ማስከተሏን ጠቅሳ ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት አቅርባ ነበር።
ፍርድ ቤቱም እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ራፋ ከተማ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ጥቃት እንድታቆም ቢያዝም ጦርነቱ በጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ትእዛዝ ከመስጠት ተቆጦቦ ነበር።
ይሁን እንጂ እስራኤል ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ የመፈጸምም ሆነ ከፍርድ ቤቱ ጋር የመተባበር ምንም ምልክት አላሳየችም፡፡
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው የመንግሥታቸውን አቋም ማስታወቃቸውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ “ስፔን ከእውነት ጎን መቆሟን እንደምትቀጥል ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል።
ሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ ኒካራጓ፣ ሊቢያ እና ፍልስጤም ደቡብ አፍሪካን ለመቀላቀል ለጠየቁት ጥያቄ በኔዘርላንድ ሔግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ምላሽ እንዲሰጣቸው እየተጠባበቁ የሚገኙ ሀገራት መሆናቸውን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡