በኦሮሚያ ክልል ሰላም ለማስፈን በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡንና የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
አቶ ሽመልስ ትናንት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር፣አባላትና ተወካዮች ጋር ትናንት በነበራቸው ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተሻለ ሰላም አለ።
ሰላሙ እንዲጠናከር የክልሉ ሕዝብና የሀገር ሽማግሌዎች ትልቅ ሚና ነበራቸው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በክልሉ ሰላም እንደሌለ ተደርጎ የሚነዛው ወሬ ሀሰት ሲሆን፤ ይህንን የሚያደርጉትም ሰላም እንዳይኖር የሚፈልጉ አካላት ናቸው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፤ ዛሬም ድረስ ጦርነትን እያወጁ የገቢ ምንጫቸው ያደረጉ አካላት አሉ። እነዚህ አካላት ከዚህ ሥራቸው ሊታቀቡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ችግሮችና ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ሙሉ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል።
ድርድሮች እንዳይሳኩ የሚታትሩ አካላት እንዳሉም ይታወቃል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በመንግሥት በኩል ግን የተጀመሩ ድርድሮችን ለመቀጠል ዛሬም ዝግጁ ነው ብለዋል። በመሆኑም ማንኛውም ሃሳብ ያለው አካል ወደ ሰላም ሊመጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሽመልስ እንዳመለከቱት፤ በአሁኑ ወቅት አንዱ በአንዱ ላይ መሣሪያ የሚያነሳበት ምክንያት አይኖርም። መንግሥት የጀመራቸው ሕግ የማስከበር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
«ካለ መስዋእትነት የሚመጣ ሰላም» የለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ብልጽግና ፓርቲ እኛ ካልነው ውጪ አይሆንም የሚል አቋም የለውም ብለዋል።
ሁሉም ነገር የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚለውን ተከትሎ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ለሰላም ሁሉም በትብብር ሊሠራ ይገባል። ፓርቲያችን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነው። የዲሞክራሲ ግንባታ ብዙ ሥራና ጊዜ ይጠይቃል በመሆኑም ሁሉም በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በክልሉ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን የመመለስ ሥራ አበረታች ውጤት የታየበት ነው። እስካሁን በተካሄዱት የመመለስ ሥራዎች በርካታ ቁጥር ያለው ከክልሉ ውጪና በክልሉ ውስጥ ይኖር የነበረ ተፈናቃይ መመለስ ተችሏል ብለዋል።
የተመለሱትንም ተፈናቃዮች የስድስት ወር ቀለብ በማቅረብ በየደረጃው እንዲቋቋሙ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል ሲሉ ጠቁመዋል። የማቋቋሙ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ አሁንም የሚታዩ ክፍተቶች አሉያሉት ኃላፊው፤ ለዚህም ችግሮችን የመለየት፤ አሠራሮችን የመፈተሽ፤ ተጠያቂነት የማስፈንና ሥራዎችን በቴክኖሎጂ የታገዙለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም ለሀገራዊ ምክክሩም ውጤታማነት የክልሉ መንግሥት አብሮ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነና አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም መግለጻቸውን አዲስ ዘመን ሪፖርት አድርጓል።