በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር የክልሉ መንግሥት ባካሄደው ውይይት ላይ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እንዳልተጋበዙ ጠቅሰው ቅሬታ አሰሙ። ኦነግና ኦፌኮ የመመጻደቅ ፖለቲካ ውስጥ እንደሆኑ የሚጠቅሱ ራሳቸውን እንዲመረመሩ መክረዋል፤ “ኦነግና ኦፌኮ በኦሮሚያ ሰላም ማስፈን ይችላሉ? ከቻሉ ከታጣቂዎቹ ጋር አብረው እየሰሩ ነው ማለት ይሆናል”
የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በዋትስ አፕ፣ በማህበራዊ ገጹና በዌብ ሳይት ጥሪ ማቅረቡን ለአቤቱታው ምላሽ ቢሰጥም ፓርቲዎቹ ለቪኦኤ “አልተጋበዝንም” ብለዋል።” ውይይት መደረጉን የሰማነው በሚዲያ ነው ” ሲል ኦፌኮ ሲገልጽ፣ የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ፓርቲያቸው በውይይቱ በውይይቱ አለመሳተፉን ነው ያስታወቁት። ነገር ግን “አልተጋበዝንም” አላሉም።
የኦፌኮ ዋና ፀሀፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ” ውይይቱ መደረጉን የሰማነው ከብዙሃን መገናኛ ነው። እንደ ግለሰብ ይሁን እንደ ተቋም የደረሰን ጥሪ የለም የኮሚኒኬሽን ክፍተቱ ከማን በኩል እንደሆነ አላውቅም ” ሲሉ ለቪኦ ኤ ተናግረዋል።
ኦፌኮ የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ቢሆንም ባለው ቅሬታ ሙሉ ተሳትፎ እያደረገ እንዳልሆነ አቶ ጥሩነህ አስታውቀዋል። አያይዘውም ለውይይት በምክር ቤት ይሁን በመንግስት ጥሪ አልደረሰንም ብለዋል።
የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በበኩላቸው ፤ ፓርቲያቸው በውይይቱ እንዳልተሳተፈ በተመሳሳይ ለቪኦ ኤ ተናግረዋል። ምክንያት ያሉትም ” ለውይይቱ ጥሪ ሊደረግ ይችላል እኛ ግን የምንፈልገው በአንድ አካል አቅራቢነት የሚደረገውን ውይይት ሳይሆን ሁሉም በእኩልነት የሚሳተፍበትን ውይይት ነው”
“የምንፈልገው አንድ ሀገርን የሚያስተዳደር መንግሥት በሚሰጠው ቦታ ተወስኖ መወያየት ሳይሆን እራሳችንን የመፍትሄ አካል ነን ብለን የምናይ አካላት በአንድ ላይ ሆነን በተመሳሳይ ድምጽ ተወያይተን ዘላቂ መፍትሄ የምናስቀምጥበት ካልሆነ ኦነግ በአንድ አካል ጥሪ የሚሳተፍበት መድረክ አይኖርም ” ሲሉ ተናግረዋል።
“የኦሮሞን ችግር የሚፈታው በእውነታ ላይ በተሰመሰረተ አካታች ውይይት እንደሆነ የገለጹት አቶ ለሚ ፤ ውይይት ሂደቱን ጠብቆ አካታች በሆነ መልኩ መከናወን አለበት አሁን ያለው አካሄድ ሂደቱን ያልጠበቀ ቅንነት የሌለው በአንድ አካል ብቻ ተጎትቶ እየሄደ ያለ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ ኦነግ እና ኦፌኮ በወይይቱ አለመሳተፋቸውን ገልጸው፣ ጥሪው ግን መተላለፉን አስታውቀዋል። ” በድረገጻችን ላይ ለጥፈናል፣ በዋትስአፕ ላይ ጥሪው ተላልፏል። ምክር ቤቱ በውይይቱ እንዲሳተፍ ኮሚቴው ሲወስን ጥሪው ይፋ ሆኗል” ሲሉ ክሱን ባስተናገደው ቪኦኤ ላይ ምላሽ አቅርበዋል።
አቶ ሰለሞን “በአካል ሳይቀር አነጋግሬያቸዋለሁ” ብለዋል። “ኦሮሚያ የኢትዮጵያ እምብርት ናት እናተ ስለሚመለከታችሁ ለምን አብረን አንሄድም?” በማለት በውይይቱ እንዲሳተፉ ማበራታታቸውንም አስታውቀዋል።
አንድ ሆኖ ተመስርቶ ስድስት ቦታ የተከፋፈለው ኦነግና ኦፌኮ ራሳቸውን ከመመጻደቅ በሽታ ሊላቀቁና ራሳቸውን ሊመለከቱ እንደሚገባ ዜናውን የሰሙ የቀድሞ የኦነግ አመራር ለኢትዮሪቪው ተናግረዋል።
ነዋሪነታቸው በአውሮፓ የሆነው እኚህ የቀድሞ የኦነግ አመራር ” ዛሬ ላይ ኦፌኮና ኦነግ ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላቸው የገባቸው አልመስለኝም። በመመጻደቅ ፖለቲካ ውስጥ ናቸው። ሁለት ጥያቄዎችን አንስቼ ሞግቻቸው ነበር መልስ አልነበራቸውም። አሁንም ህዝብ የሚጠይቃቸው ይህንኑ ነው” ብለዋል።
በኦሮሚያ ህዝብ በታጠቁ ሃይሎች ዝርፊያ፣ ግድያ፣ እገታና መፈናቀል መሰላቸቱን ያስታወቁት አስተያየት ሰጪ ” መጀመሪያ ኦነግና ኦፌኮ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቅ አውርደው ወደ ሰላም እንዲመለሱ የማድረግ አቅም ካላቸው፣ በገሃድ መሃል ከተማ ተቀምጠው ታጣቂዎችን የሚመሩ እንደሆነ ይፋ ያድርጉ፣ በኦሮሚያ እየተፈጸመ ያለውን እገታ ማስቆም፣ ዝርፊያውን መታደግ እንደሚችሉ ምን ማረጋገጫ አላቸው በሚሉ ጉዳዮች ሞግቺያቸው ምላሽ የላቸውም” ያሉት አስተያየት ሰንዘረዋል።
“ዝም ብሎ መመጻደቅ፣ የችግሩ አካል ሆነው ሳለ ራሳቸውን የኦሮሞ ህዝብ ብቸኛ መፍትሄ አድርገው መመለከት ምንም ያህል አያራምድም” ያሉት የቀድሞ የኦነግ አመራር፣ ” በርካታ የኦነግ ሰዎች በሰላም እየታገሉና ህዝባቸውን እያገለገሉ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። እነሱ በውይይት ከመሳትፍና መፍትሄ ለመፍለግ ለሌሎች የሰላም አስተዋጾ እውቅና ሰጥተው የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ፣ እነዚህ ወገኖች ሁሉ የየራሳቸው ደጋፊ እንዳላቸው ኦነግም ሆነ ኦፌኮ ዘንግተውታል” የሚል ትችትም ሰንዝረዋል።
የኦሮሞ ህዝብ ረብሻ እንደሰለቸው በቅርቡ በወለጋ አደባባይ የወጣው ህዝብ ምልክት እንደሆነ ገልጸዋል። አያይዘውም ኦፌኮም ሆነ ኦነግ በፖለቲካ መጃጃት ውስጥ እንደሆኑ አዲሱ ትውልድ ዝምታውን ሰብሮ ሊነግራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።