የጋራዥ ባለቤቶች እንድሰራ የሚፈቅዱልኝ ማፀዳዳት፣ የጋዝ ታንከር መሙላት ፣ጐማ መቀየር ወይንም ማጠብ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግን የመካኒክነት ሙያ አለኝ፡፡ በሙያዬም ስለ አውቶሞቲቭ ሳይንስ ስነግራቸው እርስ በእርስ ተያይተው ይስቁብኛል፡፡ ምንም ነገር የማልችል አድርገውም ይቆጥሩኛል
በየሺ ወልዴ
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአልደፈርም ባይነት ጐልቶ ይታያል፡፡ እጄን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም ብለው እራሳቸውን ከሰውት አጼ ቴዎድሮስ እስከ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ መሳሪያ እስከታጠቁት ድረስ በርካታ ታሪኮች ተፈፅመዋል፡፡ እነዚህንም በርካታ ምሁራንና ፀሀፍት እንዲሁም ፖለቲከኞች ሲያወድሷቸውና ሲዘክሯቸው ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ እኛም በኢትዮጵያ የበረራ ታሪክ ውስጥ ስሙን የተከለውና የጥቁሮች የበታችነት እንደ እግር እሳት የሚያንገበግበው ፖለቲከኛና ጥቁር አሜሪካዊ አውሮፕላን አብራሪ ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ጥቂት ለማለት ወደድን፡፡
አፍሪካ አሜሪካዊው ጆን ቻርልስ ሮቢንሰን ተወልዶ ያደገው በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ ነው፡፡ የልጅነት እድሜውን ከእናቱና ከእንጀራ አባቱ እንዲሁም በአራት ዓመት ከምትበልጠው እህቱ ጋር በመሆን በሚሲሲፒ ባህረ ሰላጤዋ ወደብ አሳልፏል፡፡
ትንሹ ሮቢንሰን እንደ አእዋፋት በሰማይ የመብረር ፍላጐት ያደረበት ገና በህፃንነቱ ነበር፡፡ የሰባት ዓመት አዳጊ በነበረበት ወቅትም አውሮፕላን መሰል ተንሳፋፊ በማዘጋጀት ወደ ሚሲሲፒ የባህር ወደብ አምርቶ እንደነበር መዛግብት ያወሳሉ፡፡
ተማሪው ሮቢንስን
ሮቢንስን የቀለም ትምህርቱን በ1919 በአውሮፓውያኖቹ የቀን ቀመር በባህረ ሰላጤ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ በዚህ ጊዜም የስነ እንቅስቃሴ ሀይልንና የመኪና እቃዎችን ምንነት የማወቅ ፍላጐቱ እጅግ የናረበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አፍሪካ አሜሪካውያን ከ1ዐኛ ክፍል አልፎ የመማር እድል ስላልነበራቸው ሮቢንሰን በባህረ ሰላጤው ውስጥ ሆኖ ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም፡፡
በመሆኑም ሮቢንሰን ወደ ደቡብ ምዕራባዊው የአሜሪካ ክፍል አልባማ ከተማ ለማምራት ተገደደ፡፡ መስከረም 1921 የአውቶሞቲቭ ማሽን ሳይንስ ለማጥናት ቸስኪጊ ወደተሰኘ ተቋም አመራ፡፡ ከሦስት አመት የትምህርት ዘመን በዓለም ተመርቆ የወጣው ሮበን የአውቶሞቢል፣ የአፈታሪክ፣ ስነፅሁፍ፣ የድርሰትና የታሪክ ትምህርትንም በተጨማሪነት ተከታትሏል፡፡ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እራሱን የማሳተፍ ፍላጐትና የበረራ ፍቅር በውስጡ የሚንተገተግበት ሮቢን ቺካጐ ለሚገኘው የበረራ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በተደጋጋሚ ቢያመልክትም ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ሁኔታዎች እስኪመቻቹለት ድረስም በፅዳትና ተላላኪነት በበረራ ማሰልጠኛም መስራት ጀመረ፡፡ በአንድ አሰልጣኝ አማካኝነት ስልጠናው ከተመቻቸለት በኋላ ሮቢን የመጀመሪያው ጥቁር የበረራ ተማሪ በመሆን ከነጮቹ ጋር እኩል ወንበር ላይ ተሰየመ፡፡ በጥቁርነቱ በትምህርት ቤቱ ታሪክ የመጀመሪያም ሆነ፡፡
የሮቢንሰን የስራ ተሞክሮ
ሮቢንሰን ወደ በረራ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ከመግባቱ አስቀድሞ በጫማ ማስዋብ ወይንም እንደ ሀገራችን ‘’ ሊስትሮ ’’ ስራ ላይ ተሰማርቶ ነበር፡፡ እትብቱ በተቀበረባት በባህረ ሰላጤ ወደቧ ምንም አይነት ስራ ለማግኘት አልታደለም፡፡ በነጮች የሚመራ ጋራዥ ውስጥ የመስራት አጋጣሚውን ቢያገኝም የሚደርስበት መገለል ሰላም ነሳው፡፡ በአንድ ወቅት ለአባቱ ‘’ የጋራዥ ባለቤቶች እንድሰራ የሚፈቅዱልኝ ማፀዳዳት፣ የጋዝ ታንከር መሙላት ፣ጐማ መቀየር ወይንም ማጠብ ብቻ ነው፡፡ እኔ ግን የመካኒክነት ሙያ አለኝ፡፡ በሙያዬም ስለ አውቶሞቲቭ ሳይንስ ስነግራቸው እርስ በእርስ ተያይተው ይስቁብኛል፡፡ ምንም ነገር የማልችል አድርገውም ይቆጥሩኛል” በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ ሮቢን በመቀጠል ወደ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ መቀመጫ ከተማ ወደሆነችው ዲትሪዮት ነበር ያመራው፡፡ እዚህም ቢሆን የስራውን መስመር ለማግኘት እጅግ ተቸግሯል፡፡ የቀድሞውን ተሞክሮ በመጠቀም በፅዳትና ተላላኪነት ተቀጠረ፡፡ ቀስ በቀስም ወደ ረዳት መካኒክነት ተዘዋወረ፡፡ አሁንም ግን በነጮች የስራ ባልደረቦቹ መገለል ይደርስበት ነበር፡፡ ይህንንም በመልካም ጐኑ ለቀረባቸው ነጭ የስራ አጋሮቹ ያጫውታቸዋል፡፡ ልምዱንም ያካፍላቸዋል፡፡ በዚህም ችሎታውን እያስተዋወቀ በመምጣቱ ከረዳትነት ወደ ዋና መካኒክነት እንዲሁም የከፍተኛ ተካፋይነት እድሉን አገኘ፡፡
የሮቢንሰን የበረራ ህይወት
በመካኒክነት ሙያው ስኬትን እያጣጣመ የመጣው ሮቢንሰን በአየር ላይ ለመንሳፈፍ የሚያስችለውን አጋጣሚ ማማተር ጀመረ፡፡ ለመስክ ስራ በሚወጣበት አጋጣሚ ከፓይለት ሮበርት ዊልያም እና ፐርሲ ጋር ይገናኛል፡፡ ለዋኮ 9 (WACO 9 ) የመጀመሪያ ክፍያውን በመፈፀም በረራ አካሄደ፡፡ በኋላም ወደ አየር ላይ ምልልስ አምሮቱ ይቀሰቀሳል፡፡ ወደ ችካጐ በመመለስም ጋራዥ ከከፈተ በኋላ ወደ ከርቲስ ራይት የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ማመልከቻ ያስገባል፡፡ እንደተለመደውም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በዘር የመሄድ ልማድ ያለው ሮቢን አሁንም በጠራጊነት ማሰልጠኛውን ተቀላቀለ፡፡
ሮቢንሰን በአንድ ምሽት የበረራ አሰልጣኙ ለተማሪዎቻቸው በሚያስረዱት ወቅት በደንብ አደመጠ፡፡ ያዳመጠውንም በተግባር ለመስራት ሞከረ፡፡ የራሱ አውሮፕላንም ሰራ፡፡
በዚያች ምሽት ሙከራ አደረገባት፡፡ ሮቢንሰን ወደሚያፀዳው ክፍል የገቡት አቶ ኢንደርሰን እጅግ ይደነቁና ከበረራ አሰልጣኙ ሚስተራ ሲንዲራ ጋር ያገናኙታል፡፡ ፍቃድ ያለው አብራሪ ያደርጉታል፡፡ አልፈውም በማሰልጠኛው ውስጥ ካሉ ሰልጣኞች ጋር ተቀምጦ ትምህርት እንዲከታተል እድሉን አመቻቹለት፡፡ የፓይለት /የአብራሪነት/ ማዕረግም ተጐናፀፈ፡፡ በመቀጠልም ብርኔሊየስ ኮፊ ከሚባል ጓደኛው ጋር በመሆን የማብረር ፍላጐት እያላቸው ግን ያልቻሉትን የአፍሪካ አሜሪካዊ ችግር መፍታት የሚችል የፓይለቶች ማህበርን መሰረቱ፡፡
ለጥቁር አብራሪዎች መስፋፋት የሮቢንሰን ሚና
የበረራ ማሰልጠኛዎች ለአፍሪካ አሜሪካውያን በራቸውን መዝጋት እንደሌለባቸው የወሰኑት ሮቢንስንና ጓደኛው ኮርኔሊየስ ኮፊ ሮቢንስ አሊኖስ የተሰኘውን የአውሮፕላን ጣቢያ ከፈቱ፡፡ የጥቁር ፓይለቶችን ይበልጥ ለማበረታታት ሮቢንሰንም የቀድሞውን ቱስኪን ተቋሙን ወደ በረራ ማሰልጠኛነት አሳደገው፡፡ በርካቶችንም መታደግ ቻለ፡፡
ሮቢንሰን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ
እንደ ጐርጐሮሳዊያኑ የቀን ቀመር በ1935 ሮቢንሰን ኢትዮጵያን መረዳት እንደሚፈልግ አሳወቀ፡፡ የነጮች በጥቁሮች ላይ የበላይ መሆን ሰላም የማይሰጠው ሮቢንሰን ኢትዮጵያ ላይ ኢጣሊያ ባንዣበበችበት ወቅት በኔግሮ ፕሬስ ስፖንሰር አድራጊነት ጥቁር የቢዝነስ ባለቤቶች እና የማህበረሰብ መሪዎች ምክክር መድረክ ላይ በመገኘት ነበር ኢትዮጵያን ለመርዳት ያለውን ፍላጐት ያሳየው፡፡ በዚህ ጊዜም የቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ የአክስት ልጅ ዶክተር ሁላኩ በየነ ጋር መገናኘትና መነጋገር ችለዋል፡፡ ዶክተሩም ጥያቄውንም ለአፄ ሀይለ ስላሴ አቅርበውላቸዋል፡፡ ንጉሱም የሮቢንሰንን ጥያቄ ስለመቀበላቸው በቴሌግራፍ አሳወቁት፡፡
የኮሚሽኑ አባል እንዲሆን የተመረጠበት በርካታ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛውና ዋነኛው የሮቢንሰንና የስራ ባልደረቦቹ በፖለቲካውና በውትድርናው ዓለም ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸውና ኢትዮጵያ ላይ በፋሽስቱ የኢጣሊያ ጦር ወራሪ ሀይል ለመመከት በፍላጐቱ መነሳቱ፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያም በቅኝ ግዛተ ስር ሳትወድቅ የቆየች ሀገር በመሆኗ፤ ይህንንም አልደፈር ባይነቷን ለመደገፍ ባደረበት ፅኑ ፍላጐት መነሳሳትን ፈጥሮለታል፡፡
ሌላኛው አጋጣሚ ደግሞ በአሜሪካ የአየር ጦር ሀይል ውስጥ የጥቁሮች መብት ውስን በመሆኑ ለሮቢንሰንና መሰል ጓደኞቹ መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል፡፡
በኢትዮ ኢጣሊያ ጦርነት ጊዜ የንጉሱን ጦር ከፊት ሆኖ በመምራት ከአዲስ አበባ ወደ አድዋ ዘመተ፡፡ በጋዝ የተሞሉ ቦንቦችን የተሸከሙ የኢጣሊያ ጦር መሳሪያዎች በንፁሀን ኢትዮጵያውያኖች ላይ ስለሚነጣጠሩ እውነተኛ ምስክር ነው፡፡
ምንም የጦር መሳሪያ ያልተጠቁ ነገር ግን ሙሉ ወኔ ያነገቡ የኢትዮጵያ ወዶ ዘማቾችን ሲያይ የጣሊያን ጦር ወደ ኋላ ባፈገፈገበት ወቅት የፍራቻ በተተኮሰ ሮቢንሰን ተጐዳ፡፡
ሆኖም ግን ለመተኮስ ሙከራ አላደረገም፡፡ የጣሊያን ጦር እንደገና በማንሰራራት በአዲስ አበባ የጥፋት ዘመቻውን ከፈተ፡፡ ሮቢንሰንም የኢጣሊያን ጦር መመከት የሚያስችል ጉልበት አዳብሮ በመመለስ ዳግም ጦርነት ገጥሟል፡፡
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የኢጣሊያን ጦር ከኢትዮጵያ በወጣበት በ941 ዓ.ም ሮቢንሰን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡
ኮሎኔል ሮቢንሰን ከሌሎች አፍሪካ አሜሪካውያንና ከወቅቱ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስቴር ይልማ ዴሬሳ ጋር በመሆን የንጉሰ ነገስቱን አየር ሀይል ግንባታን አከናወነ፡፡
ኮሎኔል ሮቢንሰን ከልዑል መኮንን ጋር በመሆን የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈተ፡፡ በዚህም የሲቪል ንግድ ዘርፉን ተቀላቀለ፡፡ ብሎም በሀገሪቷ በርካታ ከበረራ ጋር በተያያዘ የሚውሉ ክስተቶች መታየት ጀመሩ፡፡ በምስራቅ አፍሪካም በኮሎኔል ሮቢንሰን አማካኝነት የተከፈተው አቪየሽን ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም አድርጓታል፡፡
ለበርካታ አስርት አመታት የኢትዮጵያን አየር መንገድ ሲያገለግል የቆየው ኮሎኔል ጅሀን ሮቢንሰን ህልፈቱም በዚችው በደከመላት ሀገር በደረሰበት የአውሮፕላን አደጋ ነው፡፡ በጉለሌ መካነ መቃብር የቀብር ስነስርዓቱ የተከናወነበት የኢትዮጵያ ባለውለታ ሮቢንሰንን ማስታወስ የሚያስችል ሀውልት አፅሙ ባረፈበት ስፍራ እንኳን አልተቀመጠለትም ነበር፡፡
እርግጥ ነው የተለያዩ ባለሥልጣናት በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡ አጼ ኃይለስላሴ የሮቢንሰንን አስከሬን በተኛበት ተመልክተውታል፡፡ ለኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበውለታል፡፡ በርካታ ሀያሲያን፣ ፀሀፊያን፣ የሲቪል አቪየሽን የቦርድ ዳይሬክተሮች እና ጀነራሎች የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ልዑል መኮንን እና የአሜሪካ አምባሳደርን ጨምሮ በርካታ የበረራ ባለሙያዎች በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘት ስንብት አድርገውለታል፡፡
ለዚህ ብዙ ለሚነገርለት የኢትዮጵያ ባለውለታ ጥቁር አሜሪካዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሀገሪቱ የበረራ ታሪክ ላበረከተው አስተዋጽኦ በምስሉ የተቀረፁ ሀውልትን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ አማካኝ ስፍራ ላይ አሰርቶለታል፡፡ ይሄም ለኢትዮጵያ የጦር ጀግንነቱና ለአፍሪካ አሜሪካ አቪየሽን መስራችነቱ ክብር ሲባል የተሰራለት ስለመሆኑ ኦል አፍሪካ ዶት ኮም በመረጃ መረቡ አስነብቧል፡፡