የሽግግር ፍትሕ በርካታ ሂደት፣ ቅርጽ እና አተገባበር ያለው ሲኾን ሀገራት እና ሕዝቦች ካሉበት ግጭት ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመሸጋገር የሚተገብሩት የፍትሕ ሂደት ፣ ሂደቱ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ስህተቶችን እና የመብት ጥሰቶችን የማረም ሥራም ይከናወንበታል። ይህ ትላቅ ተግባር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የውጭ ድጋፍ ስለሚያሻው በዚሁ ድጋፍ ሳቢያ ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዳያመጣ መጠንቀቅ እንደሚገባም ተመከለተ።
“የሽግግር ፍትሕ አንድ ዓይነት አሠራር ሊኖረው አይችልም” ያሉት ተመራማሪ እና አማካሪ ዶክተር ፊሊክስ ናሂንዳ በኔዘርላንድስ የሕግ ተመራማሪ እና አማካሪ ናቸው። እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2008 እስከ 2016 በኔዘርላንድስ ቲልበርግ ዩኒቨርሲቲ በቲልበርግ ሕግ ትምህርት ቤት ዓለም አቀፍ ወንጀል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር በመኾን አገልግለዋል።
በዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ያደረጉ ሲኾን በተለይ በሽግግር ፍትሕ ዘርፍ ሰፊ ዕውቀት እና ልምድ አላቸው። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ የኾነውን የሽግግር የፍትሕን በተመለከተ እንግዳ አድርጓቸው ነበር።
ዶክተር ፊሊክስ ናሂንዳ የሽግግር የፍትሕን በማብራራት ይጀምራሉ። እንደእሳቸው ገለጻ የሽግግር ፍትሕ ሰፊ ጽንሰ ሃሳብን የያዘ የፍትሕ ሂደት ነው። የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት ከ2004 ጀምሮ ያስቀመጠው ማብራሪያ በአብዛኛው ዓለም ተቀባይነት ያገኘ እና በብዙ ሀገራት ዘንድ ተግባራዊ የኾነ እንደኾነ ይገልጻሉ።
እንደ ድርጅቱ ገለጻ የሽግግር ፍትሕ በርካታ ሂደት፣ ቅርጽ እና አተገባበር ያለው ሲኾን ሀገራት እና ሕዝቦች ካሉበት ግጭት ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመሸጋገር የሚተገብሩት የፍትሕ ሂደት ነው። ሂደቱ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ስህተቶችን እና የመብት ጥሰቶችን የማረም ሥራም ይከናወንበታል።
የሽግግር ፍትሕ አንድ ዓይነት አሠራር ሊኖረው እንደማይችል የሚገልጹት ዶክተር ፊሊክስ ናሂንዳ ሀገራት ከራሳቸው ተጨባጭ ኹኔታ ጋር የተገናዘበ የሽግግር ፍትሕን ሊተገብሩ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
ፊሊክስ ናሂንዳ (ዶ.ር.) ከ1970 ጀምሮ በደቡብ አሜሪካ ሀገራት አርጀንቲና እና ቺሊ የተጀመረው የሽግግር ፍትሕ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን አግኝቶ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች በሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ኒውዝላንድ፣ ካናዳ እና ሌሎች ሀገራት ላይም ተተግብሮ ውጤት አስገኝቷል።
የሽግግር ፍትሕን ተግብረናል ብለው ነገር ግን ሰላም እና መረጋጋትን ያላረጋገጡ ሀገራት እንዳሉ የገለጹት ዶክተር ፊሊክስ ናሂንዳ የዚህ ምክንያቱ የአተገባበሩ ችግር እንደኾነ ያስረዳሉ።
የሽግግር ፍትሕ ሲተገበር በዚያ ሀገር ጦርነት ሊቆም ይገባል፣ መንግሥት እና የፖለቲካ ኃይሎች እውነተኛ ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው፣ ሂደቱ አሳታፊ እና ሃቀኛ መኾን አለበት።
እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር የውጭ የገንዘብ ድጋፍ ሊጠይቁ እንደሚችሉ የሚገልጹት ዶክተር ፊሊክስ ናሂንዳ የውጭ ድጋፉ ግን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እንዳያመጣ መጠንቀቅ ይገባል ይላሉ።
በተለይ በሽግግር ፍትሕ ምንድን ነው ሊሠራ የታሰበው? የሽግግር ፍትሕ እንዴት ቢፈጸም ይሻላል? እንዲኹም ሀገር ወዴት እንድትሄድ ነው የሚፈለገው? የሚለው ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ መተው አለበት ማለታቸውን ከአሚኮ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።