እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጥያቄ አለኝ። ስላለፈው አንስቼ መሟገት አልፈልግም። በእኔ ዘመን በማቀው ጉዳይ መነጋገር ያስደስተኛል። እናም ኢትዮጵያዊያን በህዝብ ደረጃ ምን በድለናል? ምንስ አድርገናል? እውን ኢትዮጵያዊያን ለኤርትራ ተወላጆች ክፉ ህዝብ ነበርን? አሁንም ክፉ ነን? ልዩነት ፈጥረን ገፋናችሁ? ቤት አናከራይም፣ ምግብ አንሸጥም፣ በትራንስፖርት አናሳፍርም፣ በዶላር ካልከፈላችሁ ወዘተ አልን? ትምህርትቤት ከለከልን? ጎዳና ለየን? ምን በደልን እስኪ ንገርሩኝ!! በምን ምክንያት ነው ኢትዮጵያ ላይ ጠላት የማደራጀት መርህ በማራመድ መከራችንን የምናየው? መቼም የተሰወረ አይደለምና ለመርመር ሞክራችኋል? ወይስ ….? እስከመቼ ነው መከራችንን እንድናይ የሚደረገው? እና ” በቃ” ልንል እንደምንችል እኛን ሆናችሁ አስባችሁታል? ኤርትራዊያን ይህ ጉዳይ ቸል ያላችሁት ጉዳይ ነው?
አንድ ማንም የማይክደው ሃቅ አለ። ይህን ሃቅ ኢሳያስ አፉወርቂም አይክዱትም። እሳቸው ቢሮ የተገኙት “ኢትዮጵያዊ” የግንቦት ሰባት ካድሬዎችም አያስተባብሉትም። ዳውድ ኢብሳም ሆኑ ዳውድ ኢብሳ አምስት ያደረጉት የኦነግ አመራሮችም መከራከሪያ ያላቸውም። ትህነግ አንዱ የሸዕቢያ የዘር ሽንቱ ስለሆነ ያወቀዋል። ይህ ሃቅ “ምንድ ነው” ከተባለ ሻዕቢያ በምንም መስፈርት እሱ እንዳሻው የማይጋልባትና የማይዘርፋት፣ የተረጋጋች ኢትዮጵያን አይፈልግም። ለዚህም ነው ሲወለድ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ኢትዮጵያ ላይ ታጣቂ የሚያደራጀው። የሌሎችን አጀንዳ ተሸክሞ የኢትዮጵያ አበሳ ሆኖ የኖረው።
ሻዕቢያ ኢትዮጵያን መዝረፍ ዓላማው ነው። “ሲጋንፖርን እንሆናለን” ብሎ የተነሳው ኢትዮጵያን በትህነግ አማካይነት እየዘረፈ በኢንደስትሪ የበለጸገች ኤርትራን ለመገንባት ነበር። ከኢትዮጵያ ቡና በማጋዝ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቡና ላኪ ለመሆንና አንድ እግር የቡና ዛፍ ሳይኖራቸው ቡና በመላክ ታሪክ ግንባር ቀደም ሆኖ የተመዘገቡት በዚሁ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የመጋለብ ዕቅዳቸው ሳቢያ ነው። ትህነግን ለዚህ ታማኝነቱ እናመሰግነዋለን። የሚመራውን አገር ማጅራት ሲያስመታ የኖረው ሞራል አልባ ድርጅትና በመሆኑ።
እዚህ ላይ አንድ ምስክርነት እሰጣለሁ። ከትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር /ትህነግ አመራሮች ውስጥ ገና በበረሃው ትግል ዘመን “ሻዕቢያ እስትራቴጂካል ጠላታችን ነው” የሚሉ ነበሩ። እነዚህ አካላት “ደርግን መጣል የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ አስቀድመን ሻዕቢያን መዋጋት አለብን” የሚል አቋም ያራምዱ እንደንበር በበቂ ማስረጃ አረጋግጫለሁ። ስንቶቹን በዚሁ እምነታቸው ሳቢያ እነ መለስ እስከወዲያኛው እንዳሰናበቷቸው ዝርዝር ባልሰማም ግን የተወገዱ ነበሩ።
ይኽው ከበረሃ ጀምሮ ሻዕቢያ ላይ ያለው የአመለካከት ልዩነት ትህነግ ኢትዮጵያን እያስጋለበ ሲመራ በመካረሩ ህንፍሽፍሽ / መሰነጣጠቅ ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። በዚያው ወቅት የብር ለውጥን ተከትሎ ሻዕቢያ የዘረፈውና ያከማቸው ገንዘብ ወረቀት ሲሆንበት ወረራ መፈጸሙን እዚህ ላይ ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል።
ኢሳያስ የሚመሩትና ኢትዮጵያን እንዳሻው ማኘክ ካልቻለ ሊበትናት ሌት ተቀን እያደባ፣ ሴራ እያመረተና የሴራው አስፈጻሚዎቹን እያደራጀ ያለው ሻዕቢያ ከባድመ ጦርነት በሁዋላ መለስ ከምስራቅ አፍሪቃ፣ ከአፍሪቃ፣ ብሎም ከዓለም መድረክ እንዲገለል አደረጉት። ከሶማሌ አክራሪ ሃይሎች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ በማሰልጠን፣ በማስታጠቅና በማዝመት ሰፊ ተሳትፎ ስለነበረው በሽብር ተፈርጆ ተቆለፈበት። በሚከተለው ሌብነትን መሰረት ያደረገ፣ ከአቅም በላይ ምኞትን የተንተራሰ የቅዠት መንገድ በውጤቱም እመራዋለው የሚለውን ህዝብ በዘመናዊው ዓለም የሚኖር ሁዋላ ቀር አደረገው። የሲንጋፖርነት ቅዠቱ ቀርቶ የኤርትራ ህዝብ በየሱቁ የሚቸረቸር ኢንተርኔት ብርቅ የሆነበት ህዝብ ሆነ። ሁሉም ነገር ለክ እንደ ድንጋይ ዳቦ ዘመን የሆነባቸው ኤርትራን ባገኙት በር ሁሉ ጥለው ወጡ። በርካቶችም አዲስ አበባንመረጡ። አዲስ አበባ ሲመጡ አፋቸውን በጃቸው ላይ ጭነው “አይ ኢትዮጵያያ” በሚል የሚደነቁ ሆኑ። በጥቅሉ ኤርትራን ሰላሳ ዓመት ወደሁዋላ ጎትተዋት አረፉ። እንኳንስ ሲንጋፖር ሊኮን ምርጫ፣ ህግ፣ ሚዲያ፣ የተፈጥሮ መብት፣ የአሞልኮ ነጻነቱ የተገደበ ህዝብ ሆነ። ሻዕቢያ በምግባሩ ተቆልፎበት ላዩ ላይ ድር ያደራበት ድርጅት ሆነ። ከቶውንም ተረሳ። አቡዋራ የወረረው ድርጅትና አመራር ሆኖ ዕድሜውን ገፋ። አልተማረም አሁንም ይህ አባዜው የሚቆም አልሆነም።
አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ አመዱንና ያደራበትን ድር፣ የወረረውን አዋራ ጠርገው ወደ ምስራቅ አፍሪቃ፣ አፍሪቃና ዓለም የመለሱት የኢሳያስ የግል ፒኤልሲ የሆነው ሻዕቢያ፣ ትህነግ በኢትዮጵያ መከላከያ ላይ የፈጸመውን ክህደት የተሞላው ተግባር ተከትሎ ትግራይን ተቆጣጠራት። ቂም አቂሞ ነበርና ተበቀለ። ኢትዮጵያዊያን በሚወዱትና በማይደራደሩበት መከላከያቸው ላይ ትህነግ በፈጸመው ግፍና ክህደት ሳቢያ አኩርፈው ጀርባቸውን ስለሰጡ ሻዕቢያ የትግራይን ህዝብ በግላጭ ረሸነ። ያላደረገው ነገር የለም። ለጊዜ እንተወዋለን። አጋጣሚውን ተጠቅሞ በኢትዮጵያ የተያዩ የጸጥታ መዋቅር ውስጥም ለመዋኘት ዕድል ተመቻቸለት።
መከላከያና ደህነት ውስጥ ገብቶ ተሳተፈ። ትህነግ በራሱ ላይ ተክሎት የነበረውን የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይል መዋቅርና አሰራር እንዲሁም ሰነድ ይዞ ስለጠፋ ኢትዮጵያ ባዶ ቤት ነበረች። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ በጦርነቱ ወቅት ህዝብ እጅግ ተበሳጭቶ ስለነበር መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስና አጠቃላይ የጸጥታ ሃይሉ በፍጥነት ተቀላቀለ። እያደር ስሩን ሰዶ ፕሮፌሽናል ሆነ። ስማቸውን መጠቅስ ባያስፈልግም የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አገራት ወደፊት ታሪክ የሚመሰክርላቸው ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች ጋር ተጣምረው ሃያ አራት ሰዓት ሰርተው ድህነቱን ዘመናዊ፣ ዲጂታልና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም አድርገው ሰሩት።
እንግዲህ የሻዕቢያ ኩርፊያና መቆናጠር የተጀመረው ይህኔ ነው። ብዙዎች የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለመለያየቱ ምክንያት ቢያደርጉም ዋናው ግን አብይ አህመድ ደህንነቱንና መከላከያውን ባስቸኳይ አዋቅረው “ላደረጋችሁልን እናመሰግናለን” በሚል የሻእቢያን ሰዎች በጊዜ ሳያስቡት በድንገት ማሰናበታቸው ነው። ወደ ኤርትራ አልመለስም ብሎ አሁን አዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ (ብዙ ናቸው) እንደነገረኝ ከሆነ ኢሳያስ በዚህ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ውሳኔ እጅግ ተበሳጭተዋል። ብዙ ብዙ ብለዋል። እንደሰማሁት ከሆነ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የሆነና መረጃዎች በቴክኖሎጂ የተሰወሩ በመሆናቸው ኢሳያስ ሰዎቻቸው እዚያ ቢሆኑም መረጃ አልባ መሆናቸውም ጭራ አስበቅሏቸዋል።
የሻዕቢያ ጀነራሎች ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወር በፊት ኢንሳንና ኒስን በጎበኙበት ወቅት ያዩትን ማመን አቅቷቸው “ይህ ኢትዮጵያ ነው” እስከማለት መድረሳቸውን አንዱ አስጎብኚ ወዳጄ አጫውቶኛል። እሱ የነገረኝ ብዙ ቢሆንም ከሚናገሩትና ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ አንጻር ስለሚነገራቸው ቴክኖሎጂ ምንም መረጃ ያላቸው አይመስልም። እንደውም ግራ በመጋባት ስሜት ጉብኝቱን ጀምረው እንደጨረሱ ነው የሰማሁት።
ስለፕሪቶሪያው ስምምነት ብስጭት የተሰማው ምክንያት መረጃ ወደፊት ዝርዝሩን ባቀርብም አንድ ነገር ጠቆም ለማድረግ እወዳለሁ። ኢሳያስ ያኮረፉት አብይ አህመድ የፕሪቶሪያው ስምምነት አካል ስላላደረጓቸው ነው። ከመንግስት ወገን የተያዘው አቋም ሻዕቢያ በውስጥ ጉዳይ መግባት አያስፈልገውም ከሚል እንጂ ከሌላ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ግን ሻዕቢያ በተመሰረተው አዲስና ዓለምን ያስደመመ ግንኙነት ኢትዮጵያ ማእቀብ እንዲነሳላቸው፣ ወደ አፍሪካና ምስራቅ አፍሪቃ እንዲሁም ወደ የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ኢሳያስን ያገዘች ቢሆንም በአሰብ ወደብ ጉዳይ የቀረበውን የሰጥቶ መቀበል ዕቅድ አፍነው መያዛቸው አብይ አህመድን አላስደሰተም። እንደ አገር ኢትዮጵያን ዳግም አመድ አፋሽ ይህ እውነት ነው። እንደውም ቀደም ሲል ሲባል እንደነበረው ” ሻዕቢያ እያለ ኢትዮጵያ ሰላም ልታገኝ አትችልም” የሚለውን ድምዳሜ ከፍ አድርጎ ያሳየ ሆኗል። ወዳጆቼ እኔ እስማማለሁ!! ሻዕቢያን ማጥፋት እስካልተቻለ ድረስ የረጋ አንጠጣም። እንዲሁ አሳራችንን እንዳየን ነው የምንቀጥለው። ይህ መላምት ሳይሆን ያለፍንበት፣ በእድሜያችን ያየነው ሃህቅ ነው።
ሻዕቢያ በፕሪቶሪያው የሰላም አማራጭ ንግግር ላይ ቢገኝ የሚጠይቀው በአልጀርስ ስምምነቱ መሰረት ራሱ ትህነግ በመሪው አማካይነት የፈረመበት ስምምነት ይተገበርልኝ ከሚል አይዘልም። እሱ ደግሞ ከለውጡ በፊት ኢህአዴግ በግልጽ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኖ ለተግባራዊነቱ “ወደፊት” ያለበት ጉዳይ በመሆኑ የኩርፊያው ጉዳይ ሌላ ስለምሆኑ ማሳያ ነው ብል አልዋሸሁም።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ አያያዝ ያላማረው ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት፣ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ፣ በቅርቡ ደግሞ የቀይ ባህር ጉሮሮ በሆነው የኤደን ባህረ ሰላጤ ጥልቅ ቦታ ላይ መልህቅ ለመጣል መዘጋጀቷ ስጋት ፈጥሮበታል። ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የገነባችውና እየገነባች ያለው ሰራዊት እንቅልፍ ነስቶታል። የኢትዮጵያ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችም “ዝግጅታችን ለመንደር ሽፍታ ሳይሆን ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ነው” በሚል በተደጋጋሚ መናገራቸው የባህር በር አልባ እንዲሆን በግፍ ለተፈረደበት 120 ሚሊዮን ህዝብ ትርጉሙ ብዙ ነው። በተቃራኒው እንዴት አድርገው ኢትዮጵያን ባህር አልባ እንዳደረጉ ለሚገባቸው አቶ ኢሳያስ ንግግሩ ግልጽ ነው። እናም አስቀድመው ኢትዮጵያን ማተራመስ አለባቸው።
በዚህ መነሻ ነው አስቀድሞ ገና በአዲሱ የፍቅር ግንኙነት ሙቀትና የጫጉላ ጀልባ ላይ ሆነው ኢሳያስ አማራ ክልል ላይ ኮምፓሳቸውን ጥለው ሴራቸውን ያደሩት። አብይ ድሩን ሲያነሱላቸው እሳቸው አዲስ ድር እያደሩ ኢትዮጵያ ላይ ክፉ ሰንኮፍ ዘሩ። ዕድሜ ለትህነግ ባዶ ቤት ስላደረገን ኢሳያስ የሚያደርጉት ቢታወቅም ” ቀኑ ሲደርስ እንነጋገራለን” በሚል ታለፉ። የኤርትራ ኤምባሲ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ባህር ዳር ቅርንጫፍ የከፍተ እስከኢመስል ድረስ አማራ ክልል አስተዳር ውስጥ ገብቶ ሲያቦካና መፈንቅለ መንግስት ሲያደራጅ እንደነበር የማይውቁት ምስኪን የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ሌሎቹ ወገኖች አይደሉም። የዋሁ ህዝብ ባህር አልባ መደረጉን ረስቶ፣ ሰላም ወርዷል ጠብመንጃ ወደ መሬት መባሉን ተከትሎ ትጥቅ የፈቱ የኢትዮጵያ ወታደሮች በግፍ በጅምላ መረሻናቸውን ረስቶ፣ ከጥርሳቸው ወርቅ ሳይቀር እየተነቀለ መዘረፋቸውን ንቆ “ኢሱ” ብሎ ሲዘፍንና ሲያቆላምጣቸው፣ እሳቸው ከኦነግ ቀጥሎ ሁለተኛ የትርምስ አጀንዳቸውን በአማራ በኩል ለማስጀመር እየሰሩ ነበር። እድሜ ለኢሳት የቀድሞ ተዋናዮች!! ታሪክ ይፈርደዋል።
የብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ሚሽት ነኝ የምትለው ባለ ብዙ ስም መነን ” በኤርትራ አስራ አምስት ሺህ ፋኖ ሰልጥነዋል፤ ይቀጥላል” ስትል መመስከሯ፣ ከዙህ ጋር ተያያዞ አስመራ ኢሳያስ ቢሮ የነበሩ ቃል አቀባዮች በቅጽበት ከ “ኢትዮጵያዊነት” ወደ “ኢሳያሳዊነትና ሻዕቢያዊነት” ብርሃን ፍጥነት የተለወጡበት ሚስጢር ኢሳያስ ለምስኪኑ ህዝቧና ለኢትዮጵያ ያዘጋጁትን አዲሱ የትርምስ አጀንዳ ምን ያህል በቅንብር መሰራቱን የሚያሳይ ነው። ይህም ወደፊት ወደ ህሊናቸው የሚመልሱ የሚናዘዙበትና ይቅርታ የሚጠይቁበት አበይት የክህደት ታሪካቸው ነው።
በነገራችን ላይ ባንዳና ከሃጂ በሚል በርካታ ባለሙያዎች ይወቀሳሉ። በውጭ አገራት ሚዲያዎች፣ በራሳቸውና በተቀጠሩበት የዜና ማሰራጫ ላይ ለቀጠራቸው አገር፣ ወይም ድርጅት ወይም ግለሰብ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ መረጃ የሚረጩ ሁሉ ለምንድን ነው ” ባንዳ” የማይባሉት? ኢትዮጵያን ለማፍረስ በአገሪቱ የተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ የሚያሰራጩ የኢትዮጵያ ልጆች፣ በሚያሰራጩት መረጃ መሰረት ስለምንድን ነው ተፈርጀው በትክክለኛ ስያሜ ” ባንዳ” የማይባሉት? ይባስ ተብሎ ወያኔና ሻዕቢያ ከሚያግዙዋቸው ጋር ሆነው በጋራ ኢትዮጵያን ሲያፈራርሱ ጦሩን በፕሮፓጋንዳ ሲነዱ ከነበሩት የቪኦኤ ጋዜጠኞች መካከል ጡረታ ሲወጡ አዲስ አበባ መጥተው ካባ የተደፋባቸው እንዳሉ እዚህ ላይ ወረፍ አድርጎ ማለፍ አግባብ ነው። ሌሎችም ጉዳዩን በጥለቅት እንዲያዩት ማሳሰቢያም ነው።
ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ ኢሳያስ አማራ ክልል የፈለፈሉትን ሃይል ይዘው፣ ትህነግን በመጨመር ልክ እንደ 1983 እሳቸው መሪ ሆነ አዲስ አበባ መንግስት ለመገልበጥ ቋምጠዋል። ከትህነግ ወገን ፍላጎት ያላቸው አሉ። በተቃራኒው ” መንግስት ያግዘንና ኢሳያስን እንበቀል” የሚሉም የትህነግ ሰዎችም አሉ። በአማራ በኩል እዛም እዚህም የተጀመረው ንቅናቄ መሬት የያዘና የበሰለ ፖለቲካ የሚራምድ፣ ሃላፊነት የተሞላበት አደረጃጀት የሌለው በመሆኑ እንደታሰበው አልሆነምና ሻዕቢያ ለኢትዮጵያና የዋሁ ህዝቧ የወጠነው ውጤት አየር ላይ ተንሳፏል። እንደቀድሞ ተንደርድሮ አዲስ አበባ ለመምጣት እንዳኮበኮቡ ክንፋቸው ተመቷል።
ሃያ ሁለት ዓመት የትግራይን ህዝብ ከሻዕቢያ ትንኮሳና ወረራ ሲጠብቅ በኖረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ትህነግ ክህደት ከፈጸመ በሁዋላ ያለ አንዳች ከልካይ ትግራይን በቡድን፣ በግል፣ በድርጅት የዘረፈው፣ እጅግ አስከፊ ወንጀልና አሰቃቂ ግድያ የፈጸመው ሻዕቢያ ሁሉንም ረስቶ ዛሬ ይህነግን አቅፎ ዳግም ትግራይን የጦርነት አውድማ ለማድረግ ከሚሰሩ የትህነግ ሃይሎች ጋር ባደረገው ምክክር ሳይወል ሳያድር ጦርነት እንዲጀመር ይፈልጋል። እንደሚሰማው ከሆነ መንግስት ምህረት የሌለው እርምጃ እንደሚወስድ ማስተንቀቁን ተከትሎ፣ ሻዕቢያን መበቀል ቅድሚያ ሊሆን እንደሚገባ ከሚያምኑ አካላት አቋም ጋር ተዳምሮ ነገሩ እንዳልሆነ ሆኗል። ይልቁኑም ሻዕቢያ በደሉን በራሱ ላይ እየከመረ፣ ኢትዮጵያዊያን ምህረት አልባ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
በኦምሃጀር በኩል ኤርትራ ድንበር ላይ ሃይል አከማችቶ እንደሚጠብቅ መንግስት ሙሉ መረጃ ስላለው ድንበሩን ዘግቶታል። ቀደም ሲል በኮንትሮባንድ እህልና ማእድን ወደ ኤርትራ የሚዘልቅበት ይህ አቅጣጫ ከፍተኛ ሃይልና መሳሪያ ላንቅውን ወልውሎ የሚቆጣጠረው በመሆኑ ሻዕቢያ ከትግራይ አቅጣጫ ሙሉ ጦርነት እንዲነሳና ሱዳን ያለው የትህነግ ሃይል በመተማ እንዲያጠቃ ይፈልጋል። ዳሩ ግን መንግስት በተጠቀሱት ቦታዎችም ይሁን በሌሎች ኮሪደሮች ምን እንደሚያደርግ ዝግጅት ስላለው ስጋት የለም። ከሁሉም በላይ በዚያ አቅጣጫ ያለው ህዝብ ከመከላከያ ጋር ተናቦ የሚሰራ፣ ህዝቡ ሁሉ ሃያ አራት ሰዓት ነቅቶ የሚጠብቅ ወታደር በመሆኑ የታሰበው እንደማይሳካ ግምገማ አለ።
ለሁሉም ግን ሻዕቢያ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ ጫፍ መድረሱ በጥቂት ወዳጅ አገሮቹም በኩል ቢሆን ተፈላጊነቱን ስለሚያሳጣው፣ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጡንቻዋን ስለሚያጎለብተው ፈጥኖ ማስተጓጎል የተጠመደበት ተግባሩ ነው። በዋናነት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከእጇ የወጣባት ግብጽና የአንድ ቀበሌ ያልህ ጉልበት የሌለውን የበርበራ መንግስት ጋር በማበር ኢትዮጵያን ከሰሜን ጀምሮ እስከ ምስራቅ ለማተራመስ እየሰራ ያለው ሻዕቢያ ካላረፈ ላንቃው እንደሚዘጋ መረጃ አለኝ። ጣጣው “ለሰላማዊ ” ለሆኑ ዜጎች እንዳይደርስ እንጂ ከሻዕቢያ ጋር እድሜ ልክ በዚህ መልኩ መቀጠል ለኢትዮጵያ እልህ አስጨራሽ ሆኗል።
በሲ አይ ኤ ድጋፍና በእነ ሻለቃ ዳዊት ተላልኪነት እንዲሸነፍ የተደረገው፣ መሪዎቹ ሆን ተብሎ እንዲከሽፍ በተደረገ መፈንቀለ መንግስት እንዲያልቁበት የተፈረደበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እውን ጅግንነት ጎድሎት ተሸንፎ እንደሆነ ልናይም እንችላለን። ጦርነት ፍጹም የሚደገፍ ባይሆንም ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ላይ ከሚያራምደው የኖረ ሴራው አንጻር ጨዋታውን ለጠቅላይ ከማድረግ ውጭ አማራጭ የለም። ይህ የግል እምነቴ ነው ኤርትራዊያንም እንደማትቀየሙኝ እርግጠኛ ነኝ።
ኢትዮጵያ አገራችንን “ኢትዮጵያዊ ነን” በሚል ያልካድዋትንና ” ጨቋኝ፣ ቅኝ ገዚዎች” ብለው የረገሟትን ጨምሮ ሁሉንም አቅፋ የምታኖር፣ መድሎ የማያውቅ፣ አልቅሶ የሚሸኝ፣ እልል ብሎ የሚቀበል ሙሉ ሞራል ያለው ህዝብ ያላት አገር ናት። ኤርትራ “ነጻ አገር ናት” ብለው አዲስ አበባ ሲዘፍኑና ፈንዲሻ እየረጩ በጎዳና ላይ ወደብ አልባ በመሆናችን ሲያሽካኩ ምንም የማይል አምላኩን የሚፈራ ህዝብ ያላት አገር ናት። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ከሞራል መሰረታቸው በመነሳትና ካላቸው ጥልቅ እሴት በመነሳት እንጂ አላዋቂ ሆነው አይደለም።
ከተራ የማህበርና የተስካር ስር ስለላ ጀምሮ በየቤቱ ምን ሲፈጸም እንደነበር ህዝብ ያውቃል። ዛሬ ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑ ደግሞ ብዙውን ጉዳይ ገላልጦታል። ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያደርገውን ዘመቻ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው የሚያጧጡዙና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጠቅጥቀው ይዘው ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ የሚከፍቱትን ወገኖች መንግስትም ህዝብም ያውቃቸዋል።
በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት ለማድረግ የጀመርችውን ስምምነት ተከትሎ ተቃውሞ ካሰሙት አገሮች መካከል ኤርትራ አንዷ ናት። ምክንያቱ ባይገባኝም አዲስ አበባ ተቀምጠው ከኤርትራ መንግስት ጋር አብረው ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ እያራቡ ያሉ ኤርትራዊያን ብዙ ናቸው። በአይ ፒ አድርሻ በተደረገ ዳሰሳ ከ90 ከመቶ በላይ ኢትዮጵያ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ የዘመቱባት እነሱ ናቸው። ግን ለምን? ይህ አግባብ አይመስለኝም። ኤርትራን መደግፍ መብታችሁ ነው። ቢቻል እዛው ሄዳችሁ ፍቅራችሁንም ግለጹ። አዲስ አበባ ቁጭ ተብሎ ኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ዘመቻ ማካሄድ ግን ከህዝብ ጋር ያጣላል። መንግስት ዝም ቢል እንኳ ህዝብ ቁጣው ሊነድ ይችላል። ድሮ አቡነ አረጋይን ጸበል ተንተርሶ የተሰራው ስራ ተመዝግቦ መቅመጡ መዘንጋት የለበትም። አገር የህልውና ሚስጢር ናትና!! አገር የመኖር የመጨረሻ አማራጭ ናት። ኢትዮጵያዊያን ልጅ ልጆቻቸው በሰላም እንዲኖሩ ይመኛሉና ….
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የባህር በር ብታገኝ ኤርትራዊያንን የሚጎዳ ከሆነ እንዴት እንደሚጎዳ ጠቅሶ መወያየት፣ መነጋገር ይቻላል። ነገር ግን መሃል አዲስ አበባ በቀበሌና በመንግስት ቤት እየተኖረ ጸረ ኢትዮጵያ መሆን አይቻልም። ምንም ዓይነት የይቻላል አመክንዮም ሊቀርብ አይችልም። ይህ ይልቁኑም “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንዲሉ ነው።
ይህን ጽሁፍ ሳበቃ ምክር ቢጤ አለኝ። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን አገር ናት። ኢትዮጵያ ባለቤትነቷ ለኢትዮጵያዊያን ነው። በኢትዮጵያ የውጭ አገር ዜጎች መኖር ይችላሉ። ተመዝግበውና ህጋዊ ፈቃድ ወስደው የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም። በፖለቲካ ውስጥም የመሳተፍ መብት የላቸውም። ይህ ህግ ለዩጋንዳውም፣ ለአሜሪካውም፣ ከኬንያዊውም፣ ለኤርትራዊውም እኩል ይሰራል። ህግን ተላልፎ መገኘት አግባብ የማይሆነው ከህግ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከራስም የህሊና ፍርድ አንጻር ነው።
ካሉ ማለቴ ነው፤ አንድም ኢትዮጵያዊ ኤርትራ ውስጥ ሆኖ ኤርትራ ላይ ዘመቻ አይከፍትም። ላድርገው ቢልም የሚደርስበት ይታወቃል። ኮንትሮባንድ አይነግድም፣ ዶላር አያጥብም፣ በድንበር ከብት አይነዳም፣ በማንኛውም ወንጀል አይሳተፉም። በተመሳሳይ ከኢትዮጵያዊያን ጋር እየኖሩ ያሉ የኤርትራ ተወላጆች በኢትዮጵያ ጥገኞች ስለሆናችሁ በሰላም ከመኖር ውጭ ኮንትሮባንድ መነገድ፣ ዶላር ማጠብ፣ ከብት በድንበር መንዳት፣ በወንጀል ድርጊት መሳተፍ አትችሉም። ይህ እውነት ነው። ትህነግ የፈጸመውን ወንጀል ተከትሎ የትግራይን ህዝብ ማጣጣልም ሆነ መንካትም አይፈቀድም። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። ክፍተት ተጠቅሞ ከትግራይ ህዝብ በላይ ኢትዮጵያዊ ለመሆን መጋጋጥ ሌሎችን መናቅ ነው ዋጋ ያስከፍላል። መከባበርና አብሮ ማደግ ቀላሉ መንገድ ቢሆንም ሻዕቢያ እያለ ሊሳካ ስለማይችል አስቡበት!! ሻዕቢያ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሴራውን የጥፋት ወጥመድ ተቃወሙ!! ይህ ደግሞ ወገናዊ ጥሪዬ ነው።
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን የዋህ ህዝብ አስቡት። ደግማችሁ ውለታውን ቁጠሩ። ታጋሽነቱን አስሉ። ሃይማኖቱን፣ ወዳጁን፣ ባህሉንና መልካም እሴቱን ሁሉ አትዘንጉ። የዚህ ሁሉ እሴቶቹ ተካፋይ ናችሁ፣ ለዚህ ሁሉ እሴቶች እንግዳም አይደላችሁም፤ ስለዚህ አታሳዝኑት። በሰማይም በምድርም አዲስ አበባ ተቀምጦ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ማሴር ሩቅ አያስኬድም። ዘመን ተቅይሯል። የሚጠቅመው ተከባብሮ በወድጃነት መኖርና ከማንም ወገን ቢመጣም ሴራን አብሮ ማወገዝ ብቻ ነው!! ሻዕቢያ ኢትዮጵያን አፈራርሶ ዳር ቆሞ ሊስቅ እየሰራ መሆኑን መረዳትና አደጋውን ማስላት ኢትዮጵያን ማክበር ነው። ኢትዮጵያዊያንንም ዋጋቸውን ማወቅ ነው። የሻዕቢያ የአሁኑ አካሄድ ለኢትዮጵያዊያን ህልውናቸው እንደሆነ በቅርቡ የሚመለከታቸው ይፋ ያደርጉታልና እንዘጋጅ!!
ሰለሞን ገሬ – ለቡ
ዝግጅት ክፍሉ
ጸሃፊው የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። በአንድ ወቅት የመንግስት አመራር ነበሩ። ጥያቄ ወይም ምላሽ ካለ በዝግጅት ክፍሉ አድርሻ ይላኩ። ጽሁፉ የጸሃፊው አስተያየት ብቻ ነው። ኢትዮሪቪውን አይመለከትም። አንዳንድ ያልተገቡ አገላለጾችን ከማረም ውጭ ምንም አይነት ለውጥ አላደረግንም።