የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ትህነግ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ ወደ ትግራይ የገባው የኤርትራ ጦር ክፉኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ተሰማ። ኤርትራዊያን እናቶች ልክ ትህነግ እንዳደረገው የልጆቻቸው መጨረሻ ሳይሰሙ በሃዘንና በሰቀቀን እየማቀቁ እንደሆነ ተገለጸ።
የዝግጅት ክፍላችን የአዲስ አበባ ተባባሪ የጦርነቱን ጥሪ ሸሽተው በትግራይ በኩል አዲስ አበባ የገቡ የኤርትራ ተወላጆችን ጠቅሶ እንዳለው፣ በቁጥር መግለጽ ያዳግታቸዋል እንጂ የኤርትራ ወታደሮች ላይ ሰፊ የሚባል ጉዳት ደርሷል።
” የፈተና ውጤት ይነገራችኋል፣ ስራ ትመደበላችሁ፣ ወደ ሳዋ እንድትገቡ” የሚል ጥሪ ሲተላለፍ በትግራይ በኩል አምልጦ አዲስ አበባ እንደገባ የሚናገረው ምስክር እንዳለው ከሆነ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሳዋ የገቡት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ የተላኩ ናቸው።
“ለጋ ወጣቶች ናቸው። አብዛኞቹ ሴቶች ጉዳት የደርሰባቸው ናቸው። መናገር ስለማይቻል እንጂ በኤርትራ ህዝብ ከፍቶታል። ልጆቻቸው ያልተመለሱላቸው ግብቷቸዋል። ቢሆንም ግን መርዶ ሰምተው እርም ማውጣት ይፈልጋሉ” ሲል ምስክሩ አመልክቷል።
ነዋሪነቷ አሜሪካ የሆነች የኤርትራ ተወላጅ የአዲስ አበባውን ምስክር የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥታለች። አዲስ አበባ እረፍት ላይ ያለችው ይህች ሴት ” ወንድሜ ከሳዋ ተወሰደ። የት እንዳለ አሁን ድረስ አናውቅም። እናቴ የማይቆም ሃዘን ውስጥ ናት” በማለት ሃዘን በተሞላው አንደበት ተናግራለች።
ከጦርነቱ በሁዋላ እንደወጡ የቀሩት የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ አሁን ላይ በስፋት መነሳት የተጀመረው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በስማሌ በኩልና በአማራ በኩል ኢትዮያ ላይ ጦርነት እንዲነሳ እየሰሩ ያሉትን ስራ ተከትሎ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ማየሉን ተከትሎ ነው።
“የተጀመረው መላክም ግንኙነት ቢቀጥል ጥሩ ነው። ካልሆነም አንዱ በሌላው ጉዳይ ሳይገባ በመከባበር ሊኖሩ ይገባል” ሲል አስተያየቱን የሰጠ ሌላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኤርትራዊ፣ ” የማየውና የምሰማው ዕረፍት ነስቶኛል። አላማረኝም” ሲሉ አምላኩን እየተማጽነ እንደሆነ አመልክቷል። ለኤርትራና ኢትዮጵያ ጦርነት ምንም እንዳልፈየደላቸው አንስቶ መሪዎች ልባቸውን አስፍተው ጦርነት እንዲቀር ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክቷል።
” ጦርነት ባህላችሁ ነው” በሚል ስብከት የትግራይን ታዳጊዎችና ወጣቶች የስጨረሰው ትህነግ በአዋጅ መርዶ ማስነገሩ የሚታወስ ነው። በስነስርዓቱ ላይ የጦርነቱ ወቅት አፈቀላጤ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ነበሩ አዋጁን ጥቁር ለብሰው ያወጁት። ቀደም ሲል ጦርነቱን እንደ ድራማ በየሰዓቱ ሲዘግቡና ድል ሲያበስሩ የነበሩት አቶ ጌታቸው መርዶ ሲታወጅ ፕሬዚዳንት ሆነው በተጎጂዎች ፊት ሲቆሙ ምን እንደተሰማቸው የጠየቃቸው የለም። በክልሉ የሚነቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች በሚሊዮን ቁጥር ጠርተው ሞት መመዝገቡን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ትህነግ በወቅቱ ይህን አሃዝ አላስተባበልም።
የቁጥሩ ነገር ባይታወቅም በኤርትራ ቤተሰብ ልክ በትግራይ እንደሆነ መርዶ ሰምተው መገላገል ይፈልጋሉ። የአዲስ አበባው የመጀመሪያ አስተያየት ሰጪ ” ልጄ የት ደረሰ ማለት በኤርትራ ቅንጦት ነው”
ፐሬዚዳንት ኢሳያስ ሰሞኑንን ተከብሮ ባለፈው “ነጻነት ቀን” ላይ “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጣዊ ጉዳዮቻችን ላይ የቀረበ ተጽዕኖ እና ጫና የሚያሳድሩ፤ በጎረቤቶቻችን እየታዩ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና አዝማሚያዎች፤ በእርግጥም በርካታ ናቸው” ማለታቸው አይዘነጋም። በንግግራቸው ህዝብ በማጉረምረም ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ የማይሰጡት ኢሳያስ ጦርነት ስለመኖሩ አመልክተዋል።
“ጠቅላይና ሁሉን ልቆጣጠር ባይ ኃይሎች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ ሀገራቸው በምትገኝበት ቀጠና “ሌላ የጦርነት ዑደት ለመቀስቀስ እያሴሩ ነው” ሲሉ በወነጀሉበት ንግግራቸው ። ኤርትራ ለሚያጋጥሟት ማናቸውም ጦርነቶች ራሷን በብቃት ያዘጋጀች አገር መሆኗን ገልጸዋል። “ዝግጁ ነን” ሲሉም የሚመሩት ህዝብ ስጋት እንዳይገባው ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በኤርትራ በኩል ስለተከፈለው የህይወት ዋጋ ምንም ያልተነፈሱት ኢሳያስ ይህን ቢሉም ከኢትዮጵያ ወገን ” ቀይ ባህር ህልውናችን ነው። የቀይ ባህር ጉዳይ የመንግስት አንኳር ፖሊሲ ነው” ከሚለው አቋም በዘለለ የሚባል ነገር የለም።
“ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የመሽኮርመምና የመታዘዝ ፖሊስ ታራምድ ነበር። ዛሬ ይህ የለም” የሚሉ ወገኖች ኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ከተገለለችበት የቀይ ባህር ፖለቲካ ዳግም መመለሷ ስለማይቀር የጦርነት ጉዳይ በኢትዮጵያ ፍትሃዊ ጥያቄ ላይ ለሚዛበቱ የማይቀር እንደሆነ ይናገራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገራዊ ዕርቅ ኮሚሽን የአጀንዳ ቀረጻ ስብሰባ ማስጀመሪያ ላይ ” ጠንካራ አገር ይገነባል” ማለታቸው የሚታወስ ነው። ለዚህም ይመስላል ወደ ስላታን ከመጡ ጀምሮ የተበተነውን የባህር ሃይል በማቋቋም፣ የአየር ሃይሉን እንደ አዲስ በማቋቋም፣ የአገር መከላከያን ቴክኖሎጂን የተላበሰ ግዙፍ አድረገው ገንብተዋታል። ይህ አሁን ላይ የተገነባው ሃይል በምስራቅ አፍሪቃ ግዙፉ እንደሆነ በአፍሪካም ደረጃ በሶስተኛ ደረጃ እንደሚቀመጥ መረጃዎች ያመልክታሉ።
የአገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ” የምንዘጋጀው በየመንደር ለሚሹለከለክ ወሮበላ ሳይሆን ለሌሎች ነው” በሚል በተደጋጋሚ እየገለጹ ነው። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን የሚያሰጋ ሃይል እንደሌለም ማስታወቃቸው አይዘነጋም።