ሱዳን ጦርነት ውስጥ ከመግባቷ በፊት በነበረው የመጨረሻ ዓመት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሞገስ መኮንን ከ54.6 ሚልየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀው ነበር። ተቋሙ አሁን ላይ እንዳለው ወደ ሱዳን የሚላከው የኤሌክትሪክ ሃይል ቀደም ሲል ሱዳን በቀን ውስጥ ትወስድ ከነበረው ከ200 ሜጋዋት ወደ 50 ሜጋዋት መርዷል። ክፍያም አይፈጸምም። ባለፉት 40 አመታት በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ረሀብ በሱዳን ሊከሰት ይችላል ተባለ።
በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትወስደው የኤሌክትሩክ ኃይል በእጅጉ መቀነሱን ገልጾ ሸገር ኤፍ ኤም እንዳለው፣ ሱዳን ጦርነትውስጥ ከመግባቷ በፊት ከኢትዮጵያ የምትገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል በቀን እስከ 200 ሜጋዋት ነበር። አሁን ላይ ግን 50 ሜጋዋት እና ከዚያ በታች ሆኗል ወርዷል።
የካቲት 27 ቀን 2016 አቶ ሞገስ ሱዳን ጎረቤት ሀገር በመሆኗ ምክንያት ከኢትዮጵያ የምታገኘውን ሃይል ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ እንዳልተቻለ አመልክተው ነበር። ሱዳን ጎረቤት ሀገር በመሆኗ ምክንያት እንዲሁም ሃገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከኢትዮጵያ የሚደርሳትን የሃይል አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ያልተቻለበትን ምክንያት አስረድተው ነበር።
ለሱዳን የሚቀርበው ኃይል ከመውረዱም በላይ ” ለተጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል እየከፈሉ አይደለም ” ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ለሸገር እንዳለው “በታሰረው ውል መሰረት ለተጠቀሙበት ካልከፈሉ አገልግሎቱን ማቋረጥ የሚቻል ቢሆንም ግንኙነቱ እንዳይሻክር ኢትዮጵያ ይህንን አላደረገችም”2
ኢትዮጵያ ከሱዳን ከጅቡቲ እና ከኬኒያ የኃይል ትስስር ያላት ሲሆን በቀን እስከ ሁለት ቴራ ዋት ሀወር ለሶስቱ ሀገራት ኃይል እንምድታቀርብ ሸገር የጠቀሳቸው ሃላፊ አመልክተዋል።
ጅቡቲ የምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል አብዛኛው ከኢትዮጵያ የሚሄድ ሲሆን ኬኒያም ከምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል 10 ከመቶ ከኢትዮጵያ በምትገዛው ነው።
ሱዳን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያላት ሲሆን በቅርቡ በዓመት ጊዜ ውስጥ ለሱዳን ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ከ54.6 ሚልየን ዶላር በላይ ገቢ ማስገባት ተችሎ ነበር፡፡
በሌላ የሱዳን አስዛኝ ዜና ዓለም ከ40 ዓመታት ወዲህ አይታ የማታውቀው ከፍተኛ ረሀብ በሱዳን ሊከሰት ይችላል ተብሏል። ሁለት የስልጣን ጥመኞች ጀርባ የውጭ ሃይሎች ተዋናይ የሆኑበት የሱዳን አሁናዊ ገጽታ አንድ ሚሊዮን ህይወት ከቀጠፈው የ1977 የኢትዮጵያ ረሃብ ይልቅ የከፋ እንደሚሆን ነው የተነገረው።
በሱዳን በሁለቱ ጄነራሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ሊያስከፍል እንደሚችል የአለም አቀፍ ተራድኦ ደርጅቶች በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ የተዘነጋው ጦርነት እየተባለ በሚጠራው ግጭት የተከሰተው ረሀብ ከ40 አመታት ወዲሁ በአስከፊነቱ የመጀመርያው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሀን የሚመራው የሱዳን ጦር እና በጀነራል ሀምዳን ደጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች ሰብአዊ እርዳታዎች እንዲጓጓዙ ምቹ ሁኔታዎችን ባለመፍጠራቸው ግዙፍ ሰብአዊ ኪሳራ ሊደርስ ይችላል ነው የተባለው፡፡
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤድ ዋና ሃላፊ ሳማንታ ፓወር የእርዳታ ተሽከርካሪዎችን ጉዞ በማስተጓጎል ሁለቱንም ሀይሎች ከሰዋል፡፡ ሃላፊዋ የሚገባውን ያክል ትኩረት ከአለም አቀፍ መንግስታት እና መገናኛ ብዙሀን የተነፈገው የሱዳን ጦርነት ሰው ሰራሽ ረሀብ እያንሰራራበት እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን መሰረታዊ የሰበአዊ ድጋፎችን ለማድረስ ከሚያስፈልገው ገንዘብ 16 በመቶውን ብቻ እንዳገኝ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት በበኩሉ ባሳለፍነው ሳምንት ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በኤልፋሺር ያደረገውን ከበባ እንዲያቆም እና ለሰብአዊ ድጋፍ መተላለፍያዎቸን እንዲከፍት በብሪታንያ የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ሰጥቷል፡፡
አሜሪካ 315 ሚሊየን ዶላር ለሱዳን ሰብአዊ ድጋፍ ይውል ዘንድ መመደቧን ያስታወቁት የዩኤስኤድ ዋና ሀላፊ ነገር ግን እርዳታው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች እየደረሰ አይደለም ብለዋል፡፡ ሁለቱ ተፋላሚዎች የእርዳታ መጋዘኖችን በመቆጣጠር ምግብን እንደ ጦር መሳሪያነት እየተጠቀሙበት ሲሉ ከሰዋል፡፡
በተጨማሪም የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የእርዳታ እህሎችን ፣ የቁም እንስሳትን እንዲሁም የጥራጥሬ እህሎች ዘረፋ ላይ መሰማራቱን ነው የገለጹት፡፡
የሱዳን ጦር በበኩሉ ከቻድ ወደ ሱዳን የሚወስደውን በዳርፉር ግዛት ብቸኛ የእርዳታ መተላለፊያ ሀገር አቋራጭ መንገድ በመዝጋት ለእርዳታ ድርጅቶች ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አድርጓል፡፡ በዚህ የተነሳም ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ከጦርነቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች በረሀብ እየሞቱ ይገኛሉ፡፡
በተባበሩት መንስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ ሁኔታዎች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ የረሀብ አደጋው በከፋባቸው ዳርፉር እና ኮርዶፋን እስከ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ብለዋል፡፡
በሱዳን ያለው ስጋት ከ1977ቱ የኢትዮጵያ ረሀብ በኋላ ምድር የምታስተናግደው አስከፊው ሰበአዊ ቀውስ ሊሆን ይችላል፡፡
በሀገሪቱ ለዜጎች እርዳታ ለማድረስ ካለው ፈተና ባለፈ በቂ ድጋፎችን ለማሰራጨት ያለው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ሌላው እራስ ምታት ነው።
በዩክሬን እና ጋዛ ጦርነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው አለም የሱዳንን ጉዳይ ቸል ያለው ይመስላል፣ ሁለቱ ጦርነቶች የአለም አቀፍ ጂኦፖለቲክስ መፋተጊያ በመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረትን ሲያገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን ያስተዋለው ጥቂት ነው፡፡
ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ላይ የተቀሰቀሰው የሁለቱ ጀነራሎች ጦርነት እስካሁን የ14ሺ ንጹሀን ሱዳናዊያንን ህይወት ሲቀጥፍ 10 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አልአይን ያሰባሰበው መረጃ ያስረዳል።