የባንኮችን ጓዳ ጎድጓዳ መንግሥትና ብሔራዊ ባንክ ሳይዘገዩ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፣ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ባንኮች የሚያወጧዎቸው ሪፖርቶች ተዓማኒነታቸውን የጠበቁ መሆናቸዉን (Free From Window Dressing or Data Cooking) ለማረጋገጥ ባንኮች በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ የገዙት የ(Core Banking System Automation Report Generation Module) ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ መዋሉን (Free from Manual Intervention) ማረጋገጥ አሌ መባል የሌለበት ተግባር ነው፡፡
በአመሐ ኃይለ ማርያም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት የባንክ ሥራን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አምስት መመርያዎችን እንዳሻሻለ አሳውቋል። እነዚህ መመርያዎች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የተመደቡ ናቸው። በመጀመሪያው ምድብ የሚካተቱት፣
‹‹የብድር ተጋላጭነት ጣሪያ ስለመወሰን››፣ ‹‹ከባንኩ ጋር ዝምድና/ግንኙነት ባላቸው ወገኖች አማካይነት ስለሚኖር የብድር ተጋላጭነት››፣ ‹‹ስለንብረት ምደባና ለተዛማጅ ሥጋቶች ስለሚያዝ የመጠባበቂያ ፕሮቪዥን›› የተመለከቱ መመርያዎች ናቸው። በሁለተኛው ምድብ የሚካተቱት መመርያዎች ‹‹በባንክ ውስጥ ከፍተኛ ተዕዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አካላት ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ መሥፈርቶች›› እና 1የኩባንያ አስተዳደርን›› የሚመለከቱ ናቸው።
ከተደረጉ ማሻሻያዎች አንዱ በከፍተኛ የብድር ተጋላጭነት ገደብ መመርያ ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። የመመሪያው ዓላማ አንድ ተበዳሪ (ተያያዥነት ያላቸው ወገኖችን ጨምሮ) ከባንኩ ጋር በገባው ውል መሠረት ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ ምክንያት፣ በባንኩ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ለመቀነስና የባንኮች የተጋላጭነት መጠንን በወቅቱ ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂ ፖሊሲና አሠራር እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል። መመርያው በባዝል መርህ መሠረት ማንኛውም ባንክ ለአንድ ወይም ተያያዥነት ላላቸው ደንበኞች የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት፣ ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከ25 በመቶ እንዳይበልጥ ገድቧል፡፡ ይህ መመርያ ተያያዥነት ያላቸው አካላት እንደ አንድ የባንክ ተበዳሪ ሆነው እንዲቆጠሩ ይደነግጋል። ነጮቹ እንደሚሉት ‹‹Better Late than Never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል)፡፡
ከላይ የተዘረዘረው ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቼ የኢንዱስትሪውን ውድቀትና ኪሳራውን አሊያም ተስፋውን እንደ መነሻ እንድተነትን፣ ብሔራዊ ባንክም በተራው ራሱንና በሥሩ የተኮለኮሉትን ባንኮች በጥንቃቄ እንዲፈትሽ የሚያመላክት ጥያቄ እንዳጭር ያደረገኝና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንድደርስ ያስገደደኝ አሥጊ ሁኔታዎችን ለመታዘብ በመብቃቴ ነው፡፡
ፈረንጆቹ እንደሚሉት ሰይጣኑ የሚገኘው በዝርዝሩ ውስጥ ስለሆነ (The Devil is in the Detail) እስቲ ወደ ባንኮቹ ጓዳ ጎራ ብለን ውስጣዊ ገመናቸውን በደምሳሳው እንፈትሸው፡፡
የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ባህሪያት ወይም ተግባራት በጨረፍታ
‹‹የዓሳ… ከአናቱ ነው›› እንዲሉ የብዙዎቹ ባንኮች ችግር የሚጀምረው ከቦርድ ነው፡፡ የአብዛኞቹ ባንኮች የቦርድ አባላት ከሚያገኙት የትርፍ ህዳግ መጠን ውጪ፣ በሌላው ጉዳይ ላይ አዕምሯቸው መሥራት ያቆመ እስኪመስል ድረስ በሕጋዊነትና በሕገወጥነት መካከል እየተገላበጡ በእሳት የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በምሳሌነት የሚቀርበው የአንዳንድ ባንኮች የቦርድ አመራሮቹ ብድርና የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ሒደትና ብድር በመስጠት ዙሪያ ሥርዓተ አልበኝነትንና ሕገወጥነትን ያለ ኃፍረት የሚያበረታቱ፣ ሙስናና እጅ መንሻ መቀበል እጅግ አስነዋሪና በማኅበራዊ ጠንቅነቱ የተወገዘ መሆኑን እያወቁ የሚያወድሱና የሚያበረታቱ ናቸው፡፡
‹‹በዳፍንት ላይ… ተጨምሮበት›› እንዲሉ አብዛኞቹ የቦርድ አመራር አባላት በባንኪንግ ሙያም ሆነ በባንኪንግ አስተዳደር ዘርፍ ግንዛቤ የሌላቸው፣ በዚህም ምክንያት በባንኮቹ የውስጥ አሠራር ውስጥ ጣልቃ የሚገቡበት የተጋፊነት ደረጃ በሙያ ያልታገዘ፣ ገደብ የሌለውና በተለይ ደግሞ ከግል ጥቅማቸውና ዕውቀት ማነስ ከሚፈጠረው የበታችነት ስሜት የሚመነጭ ነው፡፡
በተለይ የቦርዶቹ ሥር የሰደደ ጣልቃ ገብነት የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ከሚነሳ ስግብግብነት የሚመነጭ መሆኑን ግልጽ የሚያደርገው፣ ብድርና የውጭ ምንዛሪ የሚያመቻችላቸውን ጥገኛ ከመሾምና ከመቅጠር የማይቦዝኑ መሆናቸው በተደጋጋሚ በባንኮቹ ሠራተኞች እሮሮ የሚሰማበት ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ባንኮቹ በሙያ ይመሩ በሚሉትና ግለኝነት በተጠናወታቸው መካከል በሚደረገው ግብግብ፣ ጥቂት የማይባሉ ባንኮች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ሌሎቹ ዓይነቶች የቦርድ አባላት ደግሞ የእኔ ክልልና የብሔሬ ሰዎች አልተሾሙም በማለት ንግድና ብሔርተኝነትን የሚያደበላልቁና ዘረኝነት የሚያሠራጩ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የባንክ ቦርድ አባላት ደግሞ የትልቅ አክሲዮን ባለቤት ውክልና ስላላቸው ብቻ ባንኩን እንደ ጓዳቸው፣ ሠራተኞቹን እንደ አሽከራቸው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ለሁሉም ዓይነት የቦርድ አባላት ያልተገለጸላቸው ጉዳይ ግን ተቀማጩ ገንዘብም ሆነ የውጭ ምንዛሪው፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልፋትና የአገሪቱ አንጡራ ሀብት መሆኑን ነው፡፡
ሁሉም የቦርድ አባላት ሊባል በሚችል ደረጃ በገቡበት ቅጥ ያጣ የትርፍ ውድድር ውስጥ ተዘፍቀው በመርህ ደረጃ ሠራተኛውን በሙስና እንዲዘፈቅና በሕዝብ ሀብት ኪሱን አደልቦ የእነሱን ጥቅም እንዲያስከብር የሚበረታቱ ከሆነ፣ የሌላቸውን ተቀማጭ የሚያበድሩና ያላፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለአየር በአየር ንግድ የሚያከፋፍሉ ከሆነ፣ ወይም ባለቤትና የቦርድ አባላት እየተፈራረቁ ዕምቅ ሀብቱን የሚከፋፈሉት ከሆነ፣ ባንኮቹ እንዴት በቴክኖሎጂና በዘመናዊ አሠራር እየተደራጁ እንደ ተቋም በእግራቸው ሊቆሙ ይችላሉ? ባንኮቹስ ከትርፍ ውጪ ራቅ አድርገው በማሰብና በመሥራት አገራዊ ግዴታቸውን እንዴት ሊወጡ ይችላሉ?
በባንኮች የውስጥ አሠራር ላይ ከፍተኛ ሚና ያለቸው ወሳኝ አካላት ደግሞ የባንኮቹ የማኔጅመት ወይም ከፍተኛ አመራር አካላት ናቸው፡፡ ከፍተኛ የባንኩ አመራሮች በአገሪቱ ውድና ዕምቅ አንጡራ ሀብት ላይ የሚወስኑ ተቋማትን የሚመሩ እንደ መሆናቸው መጠን፣ የኃላፊነት ደረጃቸውም በዚያው ልክ ከፍተኛ ነው፡፡ በግለሰብ ከሚመሩና በዕምቅ ሀብት ላይ ከማይወስኑ ሌሎች ተቋማት እኩል ሊታዩ አይገባም፡፡ ከፍተኛ ኃላፊዎች በየተቋማቸው ውስጥ የሚገኘውን ወሳኝ የሆኑ አገራዊ ሀብት፣ ማለትም በውጭ ምንዛሪና በብድር ላይ የሚወስኑ ኃላፊዎችን ሲሾሙና ሲመርጡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በእነዚህ አንጡራ ሀብቶች ላይ የሚወስኑ ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም በተግባርም ሆነ በዝንባሌ ደረጃ በሙስና ተሳትፎ ያልነበራቸውና አስተሳሰባቸውም ያልተበከለ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሥራቸው የሚሰማሩት ሠራተኞችም ሰብዕናቸው የሙስና ዝንባሌ የሌለው (Incorruptible) መሆኑን፣ ሚዛናዊነት ያልጎደላቸው፣ ለግለሰባዊ ጥቅም፣ ለዝምድና ወይም ለወዳጅነት ሲባል ውድ ሀብትን አሳልፈው የማይሰጡ መሆናቸውንና በሚመደቡበት ቦታ ላይ ከተለመደው በላይ ሙያዊ ብቃት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የሚወስኑበትን ዕምቅ ሀብት በአግባቡና እጅግ ውጤታማ በሆነ መንገድ በበቂ መተማመኛ ተደግፎ እንዲሰጥ በማድረግና በተገቢው ሁኔታ ለተገቢው ጥቅም መዋሉን ማረጋገጥ የሚችሉ፣ ለዚህም ድፍረቱና ተነሳሽነቱ አልፎ ተርፎም ግልጽነቱ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡
መሠረታዊ በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ግብዓቶች ላይ ተቀምጠው የውጭ ምንዛሪና ብድር አሰጣጥ ላይ ውሳኔ የሚሰጡ ኃላፊዎች መመርያዎችንና ደንቦችን ተከትለው በመሥራት፣ አገሪቱ በከፍተኛ ጥረት ያፈራችውን ወሳኝ የሆነ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ከትርፍ ባሻገር አርቆ በማቀድ የተፈጠረውን እጥረት ለማካካስ አገራዊ ጥቅምን በሚያረጋግጥ መንገድ እንዲከፋፈል አሠራሮችን ማመቻቸት የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አመራሮቹ ትርፍ ከማጋበስ ውጪ አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ቅድሚያ የምትሰጣቸው ዘርፎች ቅድሚያ የሚገኙበትን ሁኔታ የማረጋገጥ፣ ሕጋዊ ግዴታቸውን የመወጣትና አገራዊ ወገንተኛነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡
ብድር በቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዘርፎችም በአግባቡ ተለይተው ዘርፎቹ በአገሪቱ ልማትና ዕድገት ላይ ባላቸው ተፅዕኖ ልክ ትኩረት መስጠት እንጂ፣ የቦርድ አባል በመሆናቸው ወይም እጅ መንሻና ጉቦ በማቀባበላቸው መሆን አይገባውም፡፡ ለዚህ ደግሞ የባንክ አመራሮች ምርጫ መካሄድ ያለበት እንደዚህ ዓይነቱን ኃላፊነት ለመውሰድ ባላቸው ተነሳሽነት ተመዝኖ መሆን አለበት፡፡ የባንኮቹ ከፍተኛ አመራሮችም የብድር አሰጣጡን ማማከል ያለባቸው ውጤታማ የሆኑ፣ ግን ሥር የሰደደ እጥረት ያለባቸው ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አምራቾች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን፣ በተለይ ደግሞ ያለ መጉላላትና ያለ እጅ መንሻ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሥርዓት መዘርጋቱን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በአንፃራዊነትም ቢሆን በኑሮ ያልተደላደለው ማኅበረሰብ በባንኮች ዙሪያ ከተፈጠረው ዕምቅ አቅም ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ በተመጣጣኝ ወለድ ቤት የሚሠራበት፣ ከፍተኛ ትምህርት የሚማርበት፣ ልጆቹን የሚያስተምርበትና ንብረት የሚያፈራበት መንገድ ማመቻቸት አለባቸው፡፡
ባንኮች ተቋማዊ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን (Corporate Social Responsibility) ያውቁታልን?
በተለይም ደግሞ ግርም የሚለኝ የእነዚህን ባንኮች ተልዕኮ፣ እሴትና የተመሠረቱበትን ዓላማ ላነበበ ሰው አንድ ደስ የሚል ዓረፍተ ነገር ተጽፎ ይገኛል፡፡ ‹‹Corporate Social Responsibility›› ተቋማዊ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ይገልጻሉ፡፡ ይህንንም ባየሁት ቁጥር እገረማለሁ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ሰብስበው መልሰው የሚያበድሩ ባንኮች፣ ይህንን ሕዝብ ከድህነት ለማላቀቅ ምን ሠርተዋል? ከ80 በመቶ በላይ ገበሬ በሆነበት አገር ገበሬውን ከሞፈርና ቀንበር (ጥንታዊ ማረሻው) መቼ አላቀቁት? ከተሞች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቤት እጥረትና የትራንስፖርት ችግር እንዳለ እየታወቀና ሠራተኛው በቤት ኪራይና በኑሮ ውድነት እየተማረረ፣ ኅብረተሰቡ ቤት ሠርቶ እንዲኖር መቼ ብድር በዝቅተኛ የወለድ መጠን ማቅረብ ቻሉ? ይህንን ጥያቄ ባንኮቻችን ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ባንኮቹ ከትርፍ ባሻገር ማኅበረሰባዊ ግዴታቸውን የመወጣት ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ፈጽመው መዘንጋታቸውን ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ግዴታ ማለት ደግሞ፣ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከተንበሸበሹበት ትርፍ ላይ ትንሽ ቆንጥረው በምፅዋት መልክ ለመረጡት በጎ አድራጎት ድርጅት ድጎማ መስጠት ብቻ የሚመስላቸውም ባንኮች አሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ያለው የትርፍ መነሻቸው የሆነው ከሕዝብ በቁጠባ መልክ በአደራ የሚሰበስቡት ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የአገሪቱን ዕድገት በማቀላጠፍ ገንቢ ሚና ለሚኖራቸውና እሴት ለሚፈጥሩ ልማታዊ ሥራዎች ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ ድርሻቸውን መወጣት ስላለባቸው፣ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት አለመፈለግ ላይ ነው፡፡ ዜጎች በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከዚህ ዕምቅ ሀብት የሚጠቀሙበትን መንገድ መቀየስ ነው፡፡
መውጫ ሐሳብ
በደምሳሳው ሲታይ ብሔራዊ ባንክ የጀመረው አዳዲስ መመርያ የማውጣትና ነባሩን የማሻሻል ሒደት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከተቋቋመባቸው ዋነኛ ዓላማዎች መካከል የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሥርዓትና የተፋጠነ ልማት ማምጣት በመሆኑ ከላይ በዝርዝር ያነሳናቸው የባንኮቹ ድክመት እንዲታረም፣ ያለ ባንክ ስለዕድገትም ሆነ ስለልማት ማሰብ ያለመቻሉን ያህል፣ በሥርዓት ስለሚመሩ ባንኮች ማቀድና ችግር ሲኖር የእርምት ዕርምጃ መውስድ ከግዴታም በላይ አገራዊ ግዴታ ነው፡፡ የባንኮችን ጓዳ ጎድጓዳ መንግሥትና ብሔራዊ ባንክ ሳይዘገዩ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፣ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ባንኮች የሚያወጧዎቸው ሪፖርቶች ተዓማኒነታቸውን የጠበቁ መሆናቸዉን (Free From Window Dressing or Data Cooking) ለማረጋገጥ ባንኮች በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ የገዙት የ(Core Banking System Automation Report Generation Module) ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ መዋሉን (Free from Manual Intervention) ማረጋገጥ አሌ መባል የሌለበት ተግባር ነው፡፡
Reporter Amharic – ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የፋይናንስ ባለሙያና በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡