በአማራ ክልል የሰላም ጉዳይ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ። በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ከሰኔ 17 እስከ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካሄዱት ክልላዊ የሰላም ኮንፈረንስ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
ሙሉ መግለጫው ቀጥሎ ቀርቧል፦
በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ከሰኔ 17 እስከ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም ከሁሉም የክልላችን አካባቢዎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጣን ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካሄድነውን ክልላዊ የሰላም ኮንፈረንስ አስመልክቶ የተዘጋጀ የአቋም መግለጫ፦
ኢትዮጵያ ሀገራችን ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር፣ የበርካታ ባሕል እና ቋንቋ ባለቤት፣ የነፃነትና የአንድነት ተምሳሌት፣በገፀ ምድርና በከርሰ ምድር ሀብት የበለፀገች፣ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች መገኛና ድንቅ የባህል እሴቶች ባለቤት መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያቶች በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲፈትኗት ቆይተዋል፡፡ይሁን እንጂ እነዚህን በየጊዜው የገጠሟትን ፈተናዎች በህዝቦቿ ትብብርና አንድነት በከፍተኛ የድል አድራጊነት መንፈስ በመታገል እየተሻገረች እዚህ የደረሰች ሃገር መሆኗ ግልፅ ነዉ ፡፡
በመሆኑም የአማራ ሕዝብ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችን ጨምሮ ይህን የኢትዮጵያዊነት እሴት የተላበሱ ናቸው፡፡ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትም ከሌሎች ወንድምና እህት ኢትጵያውያን ጋር በመሆን የራሱን አስተዋፅኦ ያበረከተ እና በርካታ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ነው፡፡
ስለሆነም የሕዝቦችን የአብሮነትና የአንድነት ገመድ ለመበጣጠስ የተለያዩ ግጭቶች በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እያጋጠሙ ቆይተዋል፡፡ በአማራ ክልልም ገጥሞን የቆየው ችግር ለበርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች ዳርጎን ቆይቷል፡፡
ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረ ቢሆንም ወደ ቀድሞ ሰላሙና ወደ ዘላቂ ልማት ለመመለስ እንዲሁም ሕዝቡ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ በማድረግ ረገድ በርካታ ቀሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉን ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ክልሉ ሰላማዊና የተረጋጋ፣ እንደቀድሞ ታሪኩ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገትና አንድነት የድርሻውን እንድወጣ ለማስቻል ይህን የሰላም ኮንፍረንስ ያደረግን ሲሆን በውይይታችንም የተገኙ ግብአቶች ሕዝቡ በሰላም ለመኖር ያለውን መሻት በጉልህ የተረዳንበት እንዲሁም አሉን የምንላቸውን ጥያቄዎች በግልፅ ያቀረብንበት ነው፡፡
ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ ሲከፍል ለቆየው መስዋዕትነት በአማራ ሕዝብ ስም ታላቅ ክብር እየሰጠን የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ጀኔራል መኮነኖች ለነበራችው የመሪነት ሚና ከፍተኛ ምስጋና እያቀረብን ለመላው የሀገር መከታ እና አለኝታ ለሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ያለንን አክብሮትና አድናቆት ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ሥለሆነም ከሰኔ 17/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም ለተከታታይ ሁለት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ያደረግነውን ክልላዊ የሰላም ኮንፍረንስ አስመልክቶ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የጋራ ማድረጋችንን እናረጋግጣለን፡፡
በሰላምና በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በማንነትናበራስ አስተዳደር ጉዳይ እንዲሁም ህገመንግሥትን ስለማሻሻል አስመልክቶ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በየፈርጃቸው ለፌደራል መንግሥትና ለክልሉ መንግስት እንዲቀርብልን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንደማይመለሱ ስለምናምን መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም በፍጥነት መመለስ ያለባቸውን ለመፍታት የሚኖረውን ዝግጁነት በጋራ እያየን እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ እየተወያየን ጥያቄዎቹ እንዲፈቱልን መጠየቃችንን እንቀጥላለን፡፡
በክልሉ ውስጥ በርካታ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ የልማት ጥያቄዎች ያለ ሰላም ሊታሰቡ ስለማይችሉ ቅድሚያ በክልላችን ውስጥ ማንኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት በውይይታችን የተስማማን መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
ለሚድያ ተቋማትና ሙያተኞች እንዲሁም ለማኅበረሰብ አንቂዎች የክልሉ ሕዝብ በርካታ ሁለንተናዊ ችግሮች ተጋርጠውበት ቆይተዋል፡፡ በርካታ ምስቅልቅሎችም ደርሰውበታል፡፡ ስለሆነም ይህን ዘርፈ ብዙ ችግር ተገንዝባችሁ ሕዝቡን ወደ ሰላም የሚመልስና የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በጋራ የገነባናት ሀገር ተከባብሮና በነፃነት ተዘዋውሮ እንዲሰራባት ለማስቻል የሚድያውን አየር በሰላም እንዲትሞሉልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች፣ እንዲሁም መላ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ በልልላችን ከተፈጠረው ቀውስ በመውጣት አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በምናደርገው ጥረት ለክልላችን ሰላም ስትሉ ሁሉንም አይነት የሰላም ድጋፍ እንዲታደርጉ፣ ከመገፋፋትና ከመጠላለፍ በመውጣት ለክልሉ ሕዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በጋራ እንድትቆሙ እንጠይቃችኋለን፡፡
ታጥቃችሁ ጫካ የገባችሁ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንታገልለታለን የምትሉት ሕዝብ ያለበትን ችግርና የክልሉ ሕዝብ ኅልውና እንዴት እንደተፈተነ በግልፅ ታውቃላችሁ፡፡ ስለሆነም ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር እንዲታቀርቡ እንዲሁም የወገናችሁን ስቃይ ለመቀነስ እንዲቻል መገዳደል ይብቃን ብላችሁ ወደ ወገኖቻችሁ እንድትቀላቀሉ የሰላም ኮንፈረንሳችን ተሳታፊ በሙሉ ወገናዊ ጥሪ እያስተላለፍን መንግሥትም ሆደ ሰፊ በመሆን እነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመወያየት እና በመደራደር ለሕዝባችን ሰላም ሲባል በይቅርታና በክብር እንዲቀበላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም የዞንና የከተማ አስተዳደሮች በምታገለግሉት ሕዝብ ውስጥ የክልላችን ተወላጆች እናንተን የመንግሥት አስተዳደሮችን እና አብሮ ለዘመናት የኖረውን ወገኖቹን አምኖ እየኖረ መሆኑን በመገንዘብ ሕዝባችን ባይተዋርነትና ብቸኝነት እንዳይሰማው፣ ጥቃት እንዳይደርስበት፤ በክልላችን ለሚኖረው ሕዝብ የጥያቄ ምንጭ እንዳይሆን እንድሁም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደታችንን በአስተማማኝ ሁኔታ መሰረት እንድኖረዉ በጋራ እንዲንቀሳቀስ በሰላም ኮንፈረንሳችን ጥሪያችንን እያሰተላለፍን በአማራ ክልል ማንኛውም ዜጋ በብሔሩ ወይም በእምነቱ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የማይገለልበት ክልል እንዲሆን እኛም እንደቀደመው ሁሉ እንደምንሠራ ቃል እንገባለን፡፡
በክልላችን ውስጥ የምትንቀሳቀሱ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኀይሎች በማንም ይጠንሰስ ማንም ይጀምረው በክልላችን ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ወንድም ወንድሙን እየገደለና ሕዝባችን የከፋ ችግር እየደረሰበት በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የጀመርነው የሰላም ጥረት እንዲሳካ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉና ከጫካ የሚመጡ ወንድሞቻችሁ ወንድም መሆናቸውን አውቃችሁ በፍፁም ሙያዊ ዲስፕሊንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አቀባበል ታደርጉላቸው ዘንድ የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኃላ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ በታሰበውና ተስፋ በተጣለበት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ያላቸውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ አቅርበው የሕዝቡን ችግር በትክክለኛው መንገድ እንዲፈታ በማድረግ ታሪካዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ሁሉም አካል የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናሰተላልፋለን፡፡
በክልሉ ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ማለትም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ለምንገነባው ዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት በይቅርታና በምህረት ነፃ እንዲወጡ በማድረግ ሚናቸውንና ድርሻቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት መንግሥት በሆደ ሰፊነት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የፊደራል መንግስትና የክልላችን መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በሚገኙበት በዚህ ወቅት በህወሀት በኩል ገና ከጅምሩ ጀምሮ ስምምነቱን እንደ ጊዜ መግዣ በመጠቀም የማንነት እና የራስ አሥተዳደር ጥያቄ ባለባቸዉ አካባቢዎች ወረራ በመፈፀም ላይ ይገኛል ፡፡ በመሆኑም መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊና ተፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ ወራሪ ኀይሎች ከወረሩበት ቦታ በፍጥነት እንዲወጡ እንድሁም ጥያቄዎች በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እልባት እንዲሰጣቸው ስንል የሰላም ኮንፈረንሳችን ይጠይቃል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ሰላም ለክልላችን
ሰኔ 18/2016 ዓ.ም
ባሕር ዳር