በኢትዮጵያ እዛና እዚህ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ህዝብን መከራ ከመክተት የዘለለ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት የታዩትን የጦርነት ውጤቶች የተከታተሉ ይገልጻሉ። ህዝብ ከደቀቀ፣ ከሞተ፣ ከተፈናቀለ፣ ከተዘረፈ፣ ንብረትና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከወደሙ፣ የባዕድ ሃይሎች በውስጥ ጉዳይ እንዲጨፍሩ ከተደረገ፣ ወገኖች ከተደፍሩና በግፍ መከራ ከተቀበሉና አገርም ሆን ጉዳቱ የደረሰበት ህዝብ ክፉኛ ከተመታ በኋላ ተፋላሚዎች ለድርድር መቀመጣቸውን ትህነግን የቅርብ ጊዜ ምሳሌ በማድረግ ያሳያሉ።
እስከ አፍንጫው ታጥቆ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት ገንብቶና በቂ ሎጂስቲክ አዘጋጅቶ፣ ዓለም ዓቀፍ ድጋፍና ልዩ ክብካቤ ተመቻችቶለት፣ የዓለም ሚዲያዎች የፕርፓጋንዳው አጋፋሪ ሆነውለት፣ የተባበሩት መንግስታትን ድርጅት ሳይቀር ታዋቂ የዓለማችን አገራት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ራሳቸውን የመብት ተከራካሪ ብመው የሚጠሩ የስለላ ተቋማት፣ ዘመናዊ የሳተላይት ድጋፍ ሲደረገለት የነበረው ትህነግ፣ ” በቃኝ” ብሎ ለሰላም እጁን ሲሰጥ የትግራይን ህዝብ በቀላሉ ሊነሳ ከማይችልበት የችግር አረንቋ ውስጥ ቀርቅሮ እንደሆነ ዝርዝር መረጃ እያቀረቡ ያብራራሉ።
“ኦሮሞን ነጻ አወጣለሁ” የሚለው ኦነግ ሰራዊቱ ድፍን ወለጋን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ጊዜያት ህዝብ ወደማያውቀው ልመናና ተረጂነት ከመዳረጉ ውጪ ያተረፈው ትርፍ እንደሌለ የሚገልጹ ” አሁን ላይ ህዝብ መርመሮ በቃኝ ብሏል” በማለት ጃል መሮ ሰራዊታቸው ወለጋን ለቆ የወጣበትን ምክንያት ከሌላ አቅጣጫ ያመላክታሉ።
የህዝቡን ምሬት ያጤነው መንግስት፣ የህዝቡን ስሜት አስልቶ በከፈተው ማጥቃት በኦነግ ታጣቂዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው እጅ መስጠታቸውን በምስል አስደግፎ ሲያሳይና መክረሙ፣ አሁንም በተመሳሳይ እያሳያእ እንደሆነ ይታወቃል። ይህንኑ ተከትሎ ይመስላ ኦነግ ቀሪ ሃይሉን ከድፍን ወለጋ እንዳስወጣና ወደ ሸዋ እንደላከ አመልክቷል።
የኦነግ ሰራዊት መሪ ጃል መሮ ለታክቲክ የተወሰደ እርምጃ ነው ይበል እንጂ፣ ወለጋ ህዝቡ ከደቀቀ በሁዋላ፣ ንብረቱን ከተዘረፈና ጨለማ ውስጥ ከኖረ በሁዋላ ” በቃኝ” ማለቱን የአካባቢው ነዋሪዎች መስክረዋል። ዛሬ ወለጋና አካባቢው የተቋረጠ ስራና አገልግሎት መጀመሩን በይፋ በምስል መከታተል ተችሏል። ተሰደው የነበሩ የወለጋና አካባቢው ባለሃብቶች መመለስ መጀመራቸው፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴም እየተሻሻለ መሆኑን ምስክሮች እያስታወቁ ነው። አንድ ሆኖ ተመስርቶ ኤርትራ ውስጥ የተበጣጠሰው ኦነግ አንዱ ሌላውን እየከሰሰና እየወነጀለ በገባበት የትጥቅ ትግል ጉጂ፣ ቦረናና አርሲ፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ በሸዋ ዓላማው በውል የማይታወቅ ጥቃት እየፈጸመ ኖሮ አሁን ላለበት ደረጃ እንደበቃ በርካታ ማሳያዎች አሉ።
ኦሮሞ ዛሬ ላይ በጠብ መንጃ እንዲሰተው የሚፈለገው የመብት መጓደልም ሆነ ፖለቲካዊ አጀንዳ እንደሌለው በርካታ የቀድሞ ታጋዮች በአደባባይ ገልሰዋል። ለኦሮሞም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የጨዋ ፖለቲካ ትግል እንደሆነም አምነው በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉ ደጋግመው አመልክተዋል። ይህን ያልተቀበለው ወገን ደግሞ አሁን ድረስ ቃታ ቢስብም ያሰበውን ማሳካት ሳይችል እንዳለ አለ።
በኢኮኖሚውም ዘርፍ የአማራ ክልል 35 ከመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የአገሪቱን የሰብል ምርት የሚሸፍን ሆኖ ሳለ ፣ ዛሬ ማምረት እንኳ አልቻለም ፣ ማዳበሪያ ማሰራጨት አልቻለም ፣ ምርጥ ዘር ማሰራጨት አልቻልም ፣ የአበዳሪ ተቋማት ብድር መሰብሰብ አልቻሉም ፣ ባንኮች አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ፣ ነጋዴው ሰርቶ ፣ ነግዶ ራሱን ማሻሻል አልቻለም፡፡ህዝባችን የከፋ ችግር ውስጥ ነው ያለው አይናገርም ቢናገር ችግር ይደርስበታል።
በአካባቢነት የተመሰረተው፣ የተለያዩ አደረጃጀቶችና አመራሮች ያለው የፋኖ እንቅስቃሴም ከላይ ከተባለው የተለየ አይደለም። ወጥ አደረጃጀትና አመራር የሌለው ይህ የፋኖ እንቅስቃሴ ወደ አንድ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንን እስክንድር ነጋ በቅርቡ ሲያስታውቅ ” ማንኛውም ጦርነት መጨረሻ ላይ የሚቋጨው በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ነው” ማለቱ አይዘነጋም።
በግልጽ በማይታወቅ ምክንያት በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ መካከል የሰላም ውይይት ለማካሄድ ፍላጎት ያሳዩትን መዝለፍና ተለጣፊ ስም በመስጠት ማጣጣል በተለይ በውጭ አገር ያሉ የክልሉ ህዝብ ተቆርቋሪ ነን በሚሉት ዘንድ የተለመደ ነው። ከሁሉም በላይ የሚገርመው እነዚህ ውጭ አገር ያሉ የሚዲያ አውታሮች የየራሳቸው አካባቢያዊ ውክልና የመያዛቸው ጉዳይ ነው። ባዛገጁት የራሳቸው ድንበርና ሰፈርተኛነት መመሪያ የሚሰጡና አቋም መግለጫ የሚያወጡም አሉ።
በዚህ የተበጣጠሰና ወጥ አመራር አልባ በሆነው እንቅስቃሴ ሳቢያ አማራ ክልል እየሆነ ያለው ሁሉ እጅግ አሳዛኝ፣ ልብ የሚሰብር፣ ከጦርነት ያላገገመውን ክልል ዳግም ለውድመት ዳርጓል። ህዝቡን ከመከራ ወደ ሌላ መከራ ተሸጋግሯል። አርሶ አደሩ ዘርቶ፣ አጭዶና ከምሮ ጎተራውን መሙላት ህልም ሆኖበታል። አንጉቶ መጉረስ እየተሳነው ነው። ያለምን መደባበቅ አማራ ክልል በከፋ ችግር ውስጥ ነው። በተያዘው መንገድ ከዚህ ችግር መውጣት እንደሚቻል ለሚያስቡ ቀና አሳቢዎች፣ ክፉኛ ሃዘን ውስጥ የሚከታቸው ጉዳይ ሆኗል።
አንድ አሁን ስልጣን ላይ የሌሉ የድርጅት አመራር ” ፋኖ አንድ ሆኖ፣ ጠንካራና አርቆ የሚያስብ አመራር ሰይሞ፣ ራሱን ወደ ፓርቲ ከፍ ቢያደርግና ድርድር ላይ ቢቀመጥ በሚቀጥለው ምርጫ ክልሉን መረከብ ይችል ነበር። ቀደም ሲል መንግስት በአማራ ክልል የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ ደንታ አልነበረውም። የተበላሸው ጦርነት ውስጥ ሲገባ ነው። አሁን ላይ ህዝብ በፋኖ ደስተኛ እንደሆነ ቢሰላ የቀድሞው ውጤት አይኖርም። ይህንን ቁጭ ብለው መገምገም አለባቸው” ማለታቸው ይታወሳል።
ሰሞኑን ተካሂዶ የተጠናቀቀው የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የተነሳው የህዝብ ጥያቄ፣ ወቀሳና ምሬት ዞሮ ዞሮ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ የሚያሳስብ ነው። ትህነግ አማራን እንደ ህዝብ ፈርጆ፣ ጠብመንጃ ካነሳበት ጊዜ ጀምሮ አማራ በተቀነባበረ ዘመቻ መከራ ተሸክሞ የኖረ ህዝብ ስለመሆኑ የሚስማሙ የዚህ ህዝብ ችግር አሁን በተያዘው አግባብ ሊፈታ እንደማይችል ይገልጻሉ።
ዞሮ ዞሮ ልክ ትህነግ እንዳደረገው ለንግግር መቀመጥ እንደማይቀር እየታወቀ ሌላ ደም መቀባባት ውስጥ መግባቱ እንዲቆም የለምኑ ጥቂት አይደሉም። እርስ በርስ ሰፈር ለይተው የሚገዳደሉ የፋኖ ታጋዮችም ከዚሁ ደም መቃባት ወጥተው ወደ ቀላባቸው እንዲመለሱ ምክር የሚለግሱ ብዙ ናቸው። በአቋጥሬ ” ደምን መበቀል” ሳቢያ ለውደፊቱ አሳሳቢ ችግር እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚያሰሙ ” ከውስጥም ከውጭም በደመ ነፍስ ትግሉን እንመራለን የምትሉ ለሰላም ቅድሚያ ስጡ” የሚሉ ” ማንም ይሁን ማን ጣት ከመቀሳሰር በምውጣት አማራን አንድ በማድረግ ክዱን አጠንክሩ። ልዩነታችሁን አስወግዳችሁ ለህዝቡ አለኝታ ሁኑ። የፖለቲካ ትግሉን ደግሞ በስለጠነ አግባብ አድርጉት” የሚል ጥሪ ሲያሰሙ መክረማቸው ይታወሳል።
“የአሜሪካ መንግስት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር አምሩ” ሲል በግልጽ ካስታወቀ በሁዋላ መንግስት፣ የክልሉ አስተዳድር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት በገሃድ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸው በርካታ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እንዳሉ አመልካች ቢሆንም በፋኖ በኩል ወኪል፣ ተደራዳሪ አንድ ድርጅት አለመኖሩ በርካቶችን አሳዝኗል።
ራሱን የጎጃም፣ የጎንደር፣ የሸዋ፣ የወሎ፣ እንዲሁም በተተቀሱት ቦታዎችም ሆነ የስፍራ ልዩነት በመፍጠር በርካታ የፋኖ አመራር ያለው እንቅስቃሴ ወደ አንድ እንዲመጣ እየተሰራ መሆኑ ቢነገርም በሚጠበቀው ደረጃ ፍሬ አላፈራም። ይልቁኑም የሚሰማው በተቃራኒው ነው። ይህ በእንዲህ እያለ ነው በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ከሰኔ 17 እስከ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካሄዱት ክልላዊ የሰላም ኮንፈረንስ የተካሄደው።
ኮንፈራንሱ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁን የክልሉ መገናኛዎች አመልክተዋል። በርካታ ተናጋሪዎች በርካታ ጉዳዮችን አንስተው አስተያየት ሰጥተዋል። መንግስትን ወቅሰዋል። የፋኖ ታጣቂዎችንም በተመሳሳይ ስህተታቸውን ነቅሰው የተናገሩ አሉ። ሁሉም ግን ያተኮሩበት የመጨረሻ ነጥባቸው ” ሰላም” ነው።
በኮንፈራንሱ ተናጋሪ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አገኘሁ ተሻገር ” እስኪበቃን ተገዳድለናል ፤ እስኪበቃን ተዋጋን አሁን ይብቃን !! መፍትሔው ንግግር ነው፣ መነጋገር ነው፣ መከባበር ነው ” ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ግጭት በውይይት እና በድርድር እንዲቋጭ መንግስት በድጋሚ ጥሪ ማቅረቡን፣ ጥሪውን ያቀረበውም እዚያው በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ እንደሆነም ተመልክቷል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ወደ እውነታው በመቅረብ ” ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ መሄድ ቅንጦት ሆኗል” ብለዋል። በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ባሕር ዳር መምጣት ቅንጦት መሆኑንን አመልክተው “ያላቸው በአውሮፕላን ነው የሚሄዱ” በሚል ህዝብ በነጻነት የመንቀሳቀሱ ተፈጥሯዊ መብቱ መገታቱን አመልክተዋል።
“ተማሪዎች ትምህርታቸውን መማር አልቻሉም ፣ በርካታ ተማሪዎች ለክልላዊ እና ለአገራዊ ፈተናዎች መቀመጥ አልቻሉም ፣ እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች ተገቢ የሆነ ውጤት ለማምጣት እየተቸገሩ ነው፣ በርካታ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እያቋረጡ ነው። መንግስት የልማት ስራዎችን መስራት አልቻልም” ሲሉ የክልሉን ችግር አጉልተው ያሳዩት አቶ አገኘሁ፣ አማራ ክልል እንኳን ወደ ፊት ሊራመድ ፎቀቅ ማለት እንዳልቻለ በገሃድ አስታውቀዋል።
በኢኮኖሚውም ዘርፍ የአማራ ክልል 35 ከመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆነውን የአገሪቱን የሰብል ምርት የሚሸፍን ሆኖ ሳለ ፣ ዛሬ ለራሱ የሚሆን እንኳን ማምረት እንደታሳነው፣ ማዳበሪያ ማሰራጨት እንዳልተቻለ፣ ለአርሶ አደሩ ምርጥ ዘር ማሰራጨት ከአቅም በላይ እንደሆነ አቶ አገኘሁ ለኮንፈራንሱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
“የአበዳሪ ተቋማት ብድር መሰብሰብ አልቻሉም ፣ ባንኮች አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ፣ ነጋዴው ሰርቶ ፣ ነግዶ ራሱን ማሻሻል አልቻለም፡፡ህዝባችን የከፋ ችግር ውስጥ ነው ያለው። አይናገርም፣ ቢናገር ችግር ይደርስበታል” ሲሉ ህዝብ የደረሰበትንና የሚገኝበትን ሁኔታ ገልጸዋል።
በክልሉ የሚስተዋሉትን ችግሮችና ህዝብ እየተጋፈጠ ያለውን መከራ ከዘረዘሩ በሁዋላ “መገዳደሉና ፣ በጠላትነት መፈላለጉ ከበቂ በላይ ነው። ይሄን መገዳደል ካላስቆምን በስተቀር ክልላችን ወደፊት መራመድ ቀርቶ ፈቀቅ እንኳን ማለት አይችልም” በማለት አፈ ጉባኤው የሰላም ጥሪውን መቀበል አስፈላጊነት አመልክተዋል።
አቶ አገነሁ ደጋግመው ” በቃ !! እስኪበቃን ተገዳድለናል፣ እስኪበቃን ተዋጋን ስለዚህ አሁን ይብቃን፣ መፍትሔው ንግግር ነው፣ መነጋገር ነው፣ መከባበር ነው” ሲሉ ክልሉ ከገባበት ችግር የሚወጣበትን ብቸኛ መንገድ አመላክተዋል።
“ሌለው አካል ብቻ ችግር ያለበት አድርጌ እኔ እራሴን ከችግር እያወጣው አይደለም፣ እኔ ችግር የለብኝም እያልሁም አይደለም፣ እኔም ሁላችንም የችግሩ አካል ነን፣ ስለዚህ ይብቃን፣ ህዝባችን ከችግር እናውጣው።” ሲሉ ራሳቸውንም የችግሩ አካል በማድረግ ጥሪው ለሁሉም እንደሆነ አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።
ጥሪው እገሌ ከገሌ ሳይባል ለሁሉም እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አገነሁ “አሁንም መንግስታችን እና ፓርቲያችን የሰላም ጥሪ ያቀርባል፣ ለመነጋገር ፣ ለመወያየት ለመደራደር ፣ ለመመካከር የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግስት ዝግጁ ነው” ማለታቸው ተደምጧል።