ሰሞኑንን ከፍተኛ ቁጥር ያለውና ከባድ መሳሪያ የታጠቀ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያለ ፈቃድ የሶማሊያን ድንበር ጥሶ እንደገባ በመግለጽ በስፋት ዜና ሲሰራጭ ሰንብቷል። “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ሚዲያዎችም ” ጀግናው መከላከያ” እያሉ ዜናውን ለተራ የዩቲዩብ ማዳመቂያ አድርገውት ከርመው ነበር። ኢትዮጵያ ግን ኤምንም አዲስ ነገር የለም” ስትል ክሱን አስተባብላለች። በይፋ ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአፍሪካ ህብረትና ከራሱ የሶማሌ መንግስት ውጡ የሚል ጥያቄ ከወረበ እንደምትቀበልም አስታውቃለች።
አገራዊ ጉዳይ፣ ስትራቴጂካዊ ጉዳይና ፖለቲካዊ እንደምታ ሳይለይ ያገኘውን ሁሉ የሚፈጨው የአገራችን ሚዲያ ጉዳዩን ከሶማሌ ወገን ሆኖ ነበር ሲዘገብ የሰነበተው። ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችውን ስምምነት ልክ እንደ ኤርትራ፣ ግብጽና የሶማሌ መንግስት ሲያጣጥልና ሲኮንን የነበረው የ”ኢትዮጵያዊያን” መገናኛዎች፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለምን መንቀሳቀስ እንደፈለጉ እንኳን ሳይጠይቁ ነበር የውጭ ሚዲያ ያቀናበረውን ዘገባ ሲረጩ የከረሙት።
ቢቢሲ ያናገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ግን ነገሩን ሁሉ በባዶ አባዝተውታል። የኢትዮጵያ ወታደሮች “በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ወደ ግዛቴ ገብተዋል” ስትል ሶማሊያ ያቀረበችው ክስ መሠረተ ቢስ ነው ብለዋል። በሶማሌ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ አስቀድሞ እንደሚያደርገው እንቅስቃሴ ሊያደርግ እንደሚችል፣ ቦታ እንደሚቀያይር አንስተው ምንም አዲስ ጉዳይ እንዳልተከሰተ አምልክተዋል። ሙሉ ንየቢቢሲን ሪፖርት ከስር ያንብቡ።
ሶማሊያ ከአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውጪ የሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሕገወጥ መልኩ ድንበር ተሻግረው ወደ ሶማሊያ ገብተዋል ስትል በመንግሥታቱ ድርጅት ተወካይዋ አምባሳደር አቡባካር ኡስማን በኩል ሰኔ 17/2016 ዓ.ም. ለፀጥታው ምክር ቤት ከሳለች።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት በሶማሊያ በርካታ ወታደሮችን እንዳሰማራች የጠቀሱት ቃል አቀባዩ ሠራዊቱ ከዚህ ቀደም ከሚያደርገው መደበኛ እንቅስቃሴ ውጪ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ብለዋል።
ስለዚህም በሶማሊያ በኩል እንደተባለው “ድንበር ተሻጋሪ የሆነ ኦፐሬሽን [ዘመቻ] አልተካሄደም” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አምባሳደር ነቢዩ በጉዳዩ ላይ በሶማሊያ ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከሚመሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በውይይቱም በተገኘው መረጃ መሠረት “ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው ማንኛውም በቀጣይ ሊከሰት የሚችል ስጋት ካለ ለመከላከል እና ለመቋቋም የሚያስችል መደበኛ የሆነ ወታደራዊ ሥልጠና ነው ሲካሄድ የነበረው” ብለዋል።
በሶማሊያ በሰፈረው የኢትዮጵያ ኃይል ቦታ መቀያየር፣ ከአንድ የጦር ሰፈር ወደ ሌላው መንቀሳቀስ እንዲሁም የመሳሪያ ወይም የሌሎች ወታደራዊ ግብዓቶች እንቅስቃሴ እንደሚደረግም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በቅርቡም ይሄው መደበኛ እንቅስቃሴ እንደነበር የሚገልጹት አምባሳደር ነብዩ የሶማሊያን ክስ “አሁን ካለው ውዝግብ ጋር ተያይዞ በሚዲያ ነገሩን ለማቀጣጠል የሚደረግ ጥረት ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
“የሶማሊያ መንግሥት አሁን ባለው ሁኔታ ከቪላ ሶማሊያ [የአገሪቱ ፕሬዝዳንት መቀመጫ] ውጪ ያለውን የሶማሊያ ግዛት የሚቆጣጠር እንዳልሆነም” አጽንአት ሰጥተዋል።
ተመድ እና የአፍሪካ ኅብረት በሶማሊያ ፀጥታ ላይ ባላቸው ሚና ዙሪያ በመከረው የሰኞው ሰኔ 17/2016 ዓ.ም. ስብሰባ ላይ ነው በመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያ አምባሳደር አቡባከር ኡስማን የኢትዮጵያ ወታደሮችን ድንበር ጥሰው በመግባት የከሰሱት።
“የኢትዮጵያ ወታደሮች በሕገወጥ መልኩ ድንበር መጣስን ጨምሮ በሚፈጽሟቸው እርምጃዎች ምክንያት አገሪቷ መስከረም ወር ላይ ያቀደችውን ሽግግር ለማራዘም ተገዳለች” ብለዋል።
አምባሳደሩን በመጪው መስከረም ሊደረግ ስለታሰበው እና በዚህ ምክንያት ተራዝሟል ስላሉት ሽግግር ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።
“እነዚህ የማተራመስ እርምጃዎች በሶማሊያ እንዲሁም በቀጠናው ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታ ምክር ቤቱ እንዲያስብበት የሶማሊያ መንግሥት ያሳስባል” ሲሉም አምባሳደሩ ለምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢትዮጵያ ጋር ከሚዋሰኑ የሶማሊያ ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችው የሂራን ግዛት ከተማ ማታባ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላትን መመልከታቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የማታባን ከተማ አስተዳዳሪ ወታደሮቹ የአል-ሸባብ ታጣቂዎችን እየተከተሉ ከመንግሥት ፍቃድ ውጪ የሶማሊያን ድንበር ማቋረጣቸውን ከገለጹ በኋላ የሠራዊቱ አባላት ወደመጡበት መመለሳቸውን ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።
በደቡባዊ ሶማሊያ የምትገኘው ሂራን ግዛት አስተዳዳሪ በሽር አብዲራሃማን ሼኬዬ ለቢቢሲ ሶማልኛ ወደ ሶማሊያ ግዛት ገብተው የነበሩት ወታደሮች ቁጥር ወደ 3ሺህ እንደሚጠጋ ገልጸዋል።
አንዳንዶች በቁጥር ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ የሚያደርሷቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከኢትዮጵያዋ ፈርፈር ከተባለች የድንበር ከተማ ተነስተው ሶማሊያ የገቡት አርብ ሰኔ 14/2016 ዓ.ም. መሆኑ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወታደሮቿን እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአስራ ሰባት ዓመታት ያህል በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ልዑክ አሰማርታ ትገኛለች።
ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተፈረመ የባሕር በር መግባቢያ አወዛጋቢ ስምምነት ምክንያት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ከመጠናቀቁ በፊት ሶማሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንዲወጡ እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአትሚስ ስር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ አስጠንቅቀዋል።
ይህንን የሶማሊያ አቋም አስመልክቶ የተጠየቁት ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያላት ተልዕኮ በሶማሊያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት የተቀበለው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ኃላፊነት ያለው ነው ብለዋል። ጥያቄውም የሚመጣው ከሶማሊያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሆንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ወታደሯቿን እንድታስወጣ ከተፈለገ በይፋ ጥያቄው ሲቀርብ ተግባራዊ እንደሚሆን አምባሳደር ነብዩ ጠቁመው “ከሶማሊያ መንግሥት፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ይሁን ከተባበሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያለውን ኃይሏን ታስወጣ የሚል በይፋ የቀረበ ነገር የለም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በሶማሊያ ተሰማርተው ከሚገኙት 18 ሺህ 500 ያህሉ 5 ሺዎቹ ከአገሪቱ እንዲወጡ ተደርገዋል።
በሚቀጥሉት ሳምንታትም በርካታ ወታደሮች የሚቀነሱ ሲሆን የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር የሰላም ተልዕኮ በመጪው ዓመት ጥር ተልዕኮውን አጠናቆ የፀጥታውን ሁኔታም የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ ይደረጋል።
ሆኖም የፀጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከአስር ሺህ የማይበልጡ ወታደሮች ያሉበት የሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለበት እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።
ከአትሚስ በኋላ የሚሰማራው ኃይል እና ያለው ዝግጅት ገና እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ነቢዩ “ለእኛ ቀላል ነው ኃይላችንን ስበን ‘በፈር ዞን’ [የጦር መጠባበቂያ ሰፈር] እንፈጥራለን” ብለዋል።
ነገር ግን ለኢትዮጵያ የሚያሰጋ ነገር ካለ አገሪቷ እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥ ጠቁመዋል “ለእኛ የብሔራዊ ደኅንነት የሚያሰጋ ከሆነ የማንንም ፍቃድ የምንጠብቅበት ነገር አይደለም እኛ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ቃል አቀባዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት በምን ላይ እንዳለ የተጠየቁት ቃለ አቀባዩ “ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ እንዲህ ነው የምንለው ነገር አሁን አይኖርም፤ በቀጣይ ቀናት የምንለው ነገር ይኖራል። ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ሰፈር በኪራይ የምታገኝበት እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና የምትሰጥበት ስምምነት በሁለት ወራት ገደማ እንደሚፈረም የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ከሳምንታት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች። ‘
ዘገባው የቢ ቢሲ ነው