“ትህነግ በሰዎች ላይ ግድያ እና በተቋማት ላይ ውድመት እየፈጸመብን ነው” ሲሉ የራያ ነዋሪዎች በሰላማዊ ስለፍ ተቃውሞ ማድረጋቸውን የሚያሳይ በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ ይፋ ሆኗል።
በሰሜን ወሎ ዞን የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ትህነግ በራያ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በመቃወም ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም በሕዝባዊ የሰላማዊ ሰልፍ ተቃውመዋል።
ሰልፈኞቹ የፌዴራል መንግሥት ለራያ ሕዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል፤ መንግሥት ህወሓትን ከአካባቢያችን ያስወጣልን፤ ህወሓት ትጥቅ ፈትቶ በሰላም እንኑር፤ ከአሸባሪነቱ ያልተለየው ህወሓትን የፖለቲካ ህጋዊ ፓርቲ ሆኖ መመዝገብን እንቃወማለን፤ የራያ የማንነት ጥያቄ በሀገር አፍራሾች አይደበዝዝም የሚሉ መልዕክቶችን የያዙ መፈክሮችን ከፍ አድርገው በማንሳት ነው ተቃውሞ ያሰሙት።
ሰሞኑን ቢቢሲ የትህነግ ታጣቂዎች ተማሪዎችን አስወጥተው ትምህርት ቤቶችን የወታደር ካምፕ እንዳደረጉ ጠቅሶ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ቢቢሲ የአይን እማኞች እንደነገሩትና ይህንኑ ከአካባቢው አስተዳደሮች ማረጋገጡን ጠቅሶ ቢዘግብም ከትግራይ የአካባቢው አስተዳደሮች ወገን “ፈጽሞ ሃሰት ነው” ተብሏል። አቶ ጌታቸውን ግን ከተጠቀሱት ቦታዎች የትግራይ ሃይሎች መውጣታቸውን በኤክስ ገጻቸው በማስታወቅ ማስተባበያው ትክክል እንዳልሆነ በተዘዋዋሪ አመልክተው ነበር። ይሁን እንጂ የትህነግ ታጣቂዎች ወረው በያዙት ቦታ ህዝብ እያሰቃዩ፣ ንብረት እየዘረፉና እያጋዙ፣ ንጽሃንን እየገደሉ መሆናቸውን የሟቾችን ስም ጠቅሰው የዘገቡ አሉ።
ህወሓት በሰዎች ላይ ግድያ እና በተቋማት ላይ ውድመት እየፈጸመብን ነው ማለታቸውን አሚኮ ከስፍራው ዘግቧል። አሁንም ትህነግ እየገደላቸው እንደሆነ፣ ግድያውም መቀጠሉን የተቃወሙት ሰልፈኞች፣ “የራያ እናት ዳግም በልጇ ሞት ማልቀስ የለባትም፤ ለማንነታችን መመለስም በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን” ብለዋል፡፡
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የራያ ነዋሪ ባለፉት ጊዜያት የህወሓት የጥፋት ተግባር መቀጠሉን ጠቅሰው ባለፉት ሁለት ቀናትም የሰዎች ግድያ መፈጸሙን አምልክተዋል።
ማኅበረሰቡም ግፉ ስለበዛበት እንደመረረው እና ከገዳዩ ቡድን ጋር አንኖርም በሚል መብቱ እና ሰላሙ እንዲከበር መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ በገጠሩ የእርሻ ሰብሉን እያወደመ ያለው የታጠቀው የህወሓት ቡድንን መንግሥት ከራያ እንዲያስወጣልን ነው እየጠየቅን ያለነው ብለዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው “ለተወሰኑ ጊዜያት በሰላም ኖረን ነበር አሁን ግን ህወሓት ተመልሶ በመምጣት ሰላማችንን እያደፈረሰው፣ እየገደለን እና እየዘረፈን ነው” ብለዋል፡፡ በየገጠሩ ሰውን በዱላ እና በጥይት በመደብደብ በራያዎች ላይ ግፍ እየፈጸሙ ነው ብለዋል፡፡
የህወሓት ታጣቂ ኀይል ዙሪያውን እንደከበባቸው፣ ትምህርት ቤቶችን የወታደር ካምፕ እንዳደረጓቸው እና የፌዴራል መንግሥት ሕግ በማስከበር የህወሓትን ታጣቂ ኀይል ከራያ ምድር እንዲያስወጣላቸው ነው የጠየቁት፡፡ የአማራ ክልል መንግሥትም የራያ ወሎ አማራነት ጥያቄያቸውን ለፌዴራል መንግሥት እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሌላኛው የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊ እና የወሎ ራያ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አመራር ሕዝቡ ባለፉት 30 ዓመታት በህወሓት ከፍተኛ በደል ሲደርስበት እና ይህንንም ሲታገል እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ ህወሓት አሁንም በድጋሚ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ አካባቢውን በመውረር የራያ ነዋሪዎችን በመግደል፣ በመዝረፍ፣ አፍኖ በመውሰድ እንዲሁም ንብረት እና ሰብል በማውደም ላይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በኮረም፣ በራያ ባላ፣ በገርጀሌ፣ በኮረም ወፍላ እና ዛታ ሰዎችን በመግደል፣ አፍኖ በመውሰድ እና በመቀማት ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል አስተያየት ሰጪው።
የሰልፉ ጥያቄ የፕሪቶሪያው ስምምነት ይከበር፤ ግድያ ይቁምልን፤ በሰላም ወጥተን የመግባት ደኅንነታችን ይከበርልን፤ ትምህርት ቤቶች ከጦር ካምፕነት ነጻ ይሁኑ የሚል ጥያቄ ነው ይዘን የተሰለፍነውም ብለዋል፡፡
ህወሓት ከእኩይ ተግባሩ ባለመላቀቅ እየወረረ እና ግድያ እየፈጸመ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነትን መፍቀድ የራያ ሕዝብ እንዲሰቃይ መፍቀድ መኾኑን እያሳሰብን ነውም ብለዋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን ሕግ ዳግም እንዲያጤነውም እናሳስባለን ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ መንግሥት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከበር ማድረግ አለበትም ብለዋል።
ህወሓት የራያን ሕዝብ እየወረረ ያለው አማራ ክልል ላይ ያለውን የሰላም መደፍረስ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ የውስጥ ችግሮቹን በውይይት ፈትቶ፣ አንድነቱን ጠብቆ እና ተናብቦ ከጎናችን እንዲኾን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ሰልፈኞ ከያዟቸው እና ካሰሟቸው መልዕክቶች መካከል፦
- ራያ ወሎ አማራ ነው!
- ፍትሕ በህወሓት ለተገደሉ ወገኖቻችን!
- ታጥቀው ትምህርት ቤት ላይ የመሸጉ የህወሓት ኀይሎች በአፋጣኝ ይውጡልን!
- ከመንግሥት ኀይል ጋር ተቃውሞ የለንም፤
- መንግስት ለትህነግ ሊመልስ ያሰበውን ህጋዊነት እንቃወማለን
- ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! የሚሉት ይገኙበታል፡፡