በፀሀይ ጫኔ
ከንግድ በረራዎች እስከ የጠፈር ምርምር፣ ከጂፒኤስ ቴክኖሎጂ እስከ ህክምና እና የግብርና ስራ እድገት፤ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ ፕላኔታችንን እና አጽናፈ ዓለም/universe/ የምናስስበትን መንገድ ቀይሯል። ለመሆኑ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አዳጊ ሀገራትስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
የኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ በጎርጎሪያኑ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ/ በ1903/ ብቅ ያለ ሲሆን፤በዓለማችን የተካሄዱትን የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ተከትሎ ኢንደስትሪው በተለይም ወታደራዊ ዘርፉ የበለጠ እድገት አሳይቷል።
ሞቃት አየር ፊኛዎችን በማብረር የተጀመረው የኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ እስከሚውሉት እጅግ ፈጣን እና ዘመናዊ አውሮፕላኖች እና የጠፈር መንኮራኩሮች ድረስ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ደግሞ እየተሻሻለ እና በህብረተሰቡ ላይ ያለው ተፅዕኖም እየጨመረ መጥቷል።
ኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ አውሮፕላኖችን እና የጠፈር መንኮራኩሮችን ለመንደፍ፣ለመገጣጠም እና ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውል የቴክኖሎጂ ነው። ይህም የተለያዩ የአውሮፕላን እና የጠፈር ምርቶችን ማለትም የመንገደኞች እና ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ፣ሄሊኮፕተሮችን ፣ የጠፈር መንኮራኩሮችን ፣ሳተላይቶችን እና ሌሎች ከህዋ ጋር የተገናኙ ቁሳቁሶች ማምረትን ያጠቃልላል። ከዚህ አንፃር ኤሮስፔስ በአብዛኛው ያደጉ ሀገራት ቴክሎጂ ተደርጎ ይታያል። ለመሆኑ የኤሮስፔስ ቴክኖሎጂ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሀገራት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? የኢትዮጵያ ኤሮ ክለብ መስራች እና ብሪታኒያ ውስጥ ለሚታተመው አፍሪካን ኤሮስፔስ እና ወልስትሪት ለመሳሰሉ ጋዜጦች የሚፅፈው ዮናታን መንክር ካሳ፤ አስፈላጊ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ይላል።
«ኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ ለአፍሪቃ የህልውና ጉዳይ ነው ብዬ ነው የምከራከረው።ከግብርናም ከሌሎችም ከየትኛውም ዘርፍ የአቤሽን እና የኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ የበለጠ ጠቃሚ ነው አስፈላጊ ነው በሚል ደረጃ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ብዬ እከራከራለሁ።ምክንያቱም ኤሮ ስፔስ ኢንደስትሪ በውስጡ የሚይዛቸው በተለይ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ፣የመከላከያ እንደዚሁም «ኮኔክቲቪቲ»በአየር ትራንስፖርት በኩል አውሮፕላኖችን በማምረት ጉልህ ስፍራ አለው።»ካለ በኋላ፤ ነገር ግን እንኳን ኤሮ ስፔስ በአቤሽን እንደስትሪም አፍሪቃ 2% ብቻ ድርሻ እንዳላት ተናግሯል።ከዚህ አንፃር አህጉሪቱ በዚህ ዘርፍ ውስጥ የለችም ማለት ይቻላል በማለት ገልጿል። ዮናታን አያይዞም «ኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ ስንል የቴሌኮምኒኬሽን፣ ለግብርናም፣ ለጤናም፤በአጠቃላይ ለእድገት የሚያስፈልጉ ነገሮች በሙሉ የሳተላይት ቴክኖሎጂ በጣም ከፍተኛ የሆነ እገዛ አለው።»በማለት የኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ አስፈላጊነትን አብራርቷል።

ዮናታን መንክር ካሳ፤የኢትዮጵያ ኤሮ ክለብ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም ብሪታኒያ ውስጥ ለሚታተመው አፍሪካን ኤሮስፔስ እና ወልስትሪትን ለመሳሰሉ ጋዜጦች በአቤሽን ዙሪያ የሚፅፍ
የሰው ልጆች በምድር ከባቢ አየር እና በህዋ ለሚደረጉት ጉዞ እና ምርምር ኤሮስፔስ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እድገት ነው። ቴክኖሎጂው ለብዙ አሥርተ ዓመታት ወሳኝ ኢንዱስትሪ ሆኖ የዘለቀ ሲሆን፤ተፅዕኖው በበሰው ልጆች ዘመናዊ የአኗኗር እና የዕለ ተዕለት ህይወት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለው።
የኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ ፤ከንግድ በረራዎች እስከ የጠፈር ምርምር፣ ከጂፒኤስ ቴክኖሎጂ እስከ ህክምና እድገት፣ከእርሻ እስከ ሳተላይት ግንኙነት እና የጠፈር ምርምር ፤ በአጠቃላይ የምንኖርባትን ፕላኔት መሬትን እና ከዚያ ባሻገር ያለውን አፅናፈ ዓለምን/universe/ የምንቃኝበትን መንገድ ቀይሯል።
ዓለም በቴክኖሎጂ እያደገች እና እየተሻሻለች በመምጣቷ ደግሞ፤በተለያዩ ዘርፎች የኤሮስፔስ አስፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል።
የኤሮስፔስን የሳተላይት ቴክኖሎጅ መስክ ስንመለከትም፤ እንደ የአየር ሁኔታ ትንበያ፣ የርቀት ዳሰሳ፣ የሳተላይት ዳሰሳ ስርዓት፣ የሳተላይት ቴሌቪዥን እና አንዳንድ የረዥም ርቀት የመገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀምን ያሉ፤ የዕለት ተዕለት አገልግሎቶችም በጠፈር መሠረተ ልማት ላይ ጥገኛ ናቸው።
የስነ ፈለክ እና የከርሰ ምድር ጥናት ሳይንሶችም ከሳተላይት ቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ያም ሆኖ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአፍሪቃ ሀገራት በዘርፉ ወደ ኋላ በመቅረታቸው ተጠቃሚ አለመሆናቸውን የአቤሽን ባለሙያው ያስረዳል።
«ዛሬ አፍሪካ በከርሰ ምድርም ይሁን በመሬት ላይ ያላትን ሀብቶች በራሷ አቅም የመለየት እና የማጎልበት አቅም የላትም።ሁልጊዜም ከአህጉሪቱ ውጭ በሆኑ ሀገራት እርዳታ እና ድጋፍ ተንጠልጥላ ነው ምን አለኝ የሚለውን ነገር የምታየው ።ይህ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ነው።» በማለት ከገለፀ በኋላ ፤ የአህጉሪቱ ህዝብ የሚጠቀምበት ስልክ እና በይነመረብም ቢሆን ኪራዩ የሚገኘው ከአፍሪካ ውጭ በሆኑ ሀገራት ተቋማት መሆኑን ጠቅሶ፤ እንደ ሀገር እንደ አህጉር ሚስጥር የሚባል ነገር የለም ብሏል።ይህም ከሀገራት ሉዓላዊነት ጋር እንደሚያያዝ ገልጿል።
ከውጭ አንፃርም ለኪራይ የሚከፈለው ገንዘብ ቀላል አለመሆኑን አስረድቷል።ይህ ወጭም በተዘዋዋሪ መንገድ በዜጎችን ላይ የሚጫን ነው ይላል።
ይህ ቴክኖሎጂ በብዙ የእለት ተእለት የህይወት ገፅታዎች ውስጥ በጣም የተዋሃደ ቢሆንም፤ ብዙውን ጊዜ ለተራው ተጠቃሚ የሚታይ አይለም።አንዳንዴም የቅንጦት ቴክሎጂ ተደርጎ ይታያል።
ነገር ግን ሳተላይቶች በአሁኑ ወቅት የትራፊክ መጨናነቅን ለማስወገድ ከሚረዱ የጉዞ መስመሮች እስከ መንገድ የሚመሩ ካርታዎች ድረስ በርካታ መተግበሪያዎችን ያቀርባሉ።የስልክ እና በይነመረብ ላይ የተመሰረቱ መስተጋብሮም ከዚሁ ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ናቸው።
በበይነመረብ ግብይትን በተመለከተም የተገዙ እቃዎች ለገዥው መድረሳቸውን በተንቀሳቃሽ ስልክ ወይም በኩባንያው ድረ-ገጽ በኩል ለመከታተል ይህ ቴክኖሎጅ ወሳኝ ነው። የርቀት ዳሳሽ ሳተላይቶች በምድር ላይ ምን እየተከናወነ እንዳለ ያሳያሉ። የአየር ሁኔታ ሳተላይቶችም በየቀኑ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችን የሚያግዙ መረጃ እና ምስሎችን ይልካሉ።

የሰው ልጆች በምድር ከባቢ አየር እና በህዋ ለሚደረጉት ጉዞ እና ምርምር ኤሮስፔስ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ እድገት ነው።ምስል Peopleimages/Pond5 Images/IMAGO
የኤሮስፔስ ኮፕሬሽን የተባለ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ የጥናት ተቋም እንዳመለከተው ከ2,200 በላይ ስራ ላይ ከሚገኙ ሳተላይቶች መሠረተ ልማቶችን፣ ኢኮኖሚዎችን እና ብሔራዊ የደህንነት ሥርዓቶችን በመደገፍ በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢን ያስገኛሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ድሃ የአፍሪቃ ሀገራት ግን የራሳቸውን ቴክኖሎጅ ባለማበልፀጋቸው ዮናታን እንደሚለው ከገቢ ይልቅ በሌለ አቅማቸው በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪን ያወጣሉ።
«የራሳችንን ቴክኖሎጅ ባለማበልፀጋችን በየዓመቱ ከሌለን አንጡራ ሀብት መልሰን ከአህጉሪቱ ውጭ ወደ አሉ ሀገራት የምንልከው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ወደ ማያቋርጥ የድህነት ዑደት ውስጥ ነው የምሽከረከረው ማለት ነው።ግብርናን ብንወስድ ዘመናዊ የአየር ትንበያ ፣ ማዕድናትን ወይም ሌሎች ነገሮችን በቀላሉ የሚያሳይ የሚጠቁም ሁኔታዎችን የሚተነትን የሳተላይት ቴክኖሎጂ ይፈልጋል።ይህም የለንም።ስለዚህ አርሶ አደሮቻችን ገበሬዎቻችን ወይም አርብቶ አደሮቻችን በተፈጥሮ እና ካላቸው እና ከትውልድ ሲወራረስ ከመጣው እውቀት ውጭ ሌላ እውቀት የላቸውም ።ያማለት ደግሞ ድሮ ለትንሽ ሰዎች ይበቃ የነበረ ምርት ሊሰጥ ይችል የነበረ እውቀት ከዚያ ባለፈ አሁን ላለው እና እየጨመረ ለሄደው የህዝብ ቁጥር ላለው ፍላጎት የሚበቃ ሰፊ የሆነ የእርሻ ስራ ለመስራት የሚስችል ቴክኖሎጂ የላቸውም። መንግስታትም ይህንን ማቅረብ አይችሉም።»በማለት አብራርቷል።
በሌላ በኩል የኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተም ዘርፉ፤ እንደ ሮኬት፤ ሚሳይል ፣ሰው አልቫ አውሮፕላኖችን እና ተዋጊ አውሮፕላኖችን የማምረት፣ ንድፍ የመስራት እና የመጠገን ስራን የሚያካት በመሆኑም፤ የኤሮስፔስ ኢንደስትሪ የአንድ ሀገር የብሔራዊ ደህንነት ወሳኝ አካል ተደርጎም ይወሰዳል።ከዚህ አንፃርም አፍሪቃ ራሷን መጠበቅ የማትችል አህጉር ነች ይላል ባለሙያው።
ያም ሆኖ የሀገራት መልካም አስተዳደር እና ግልጽ የፖሊሲ መመሪያ ለቴክኖሎጅ እድገት ወሳኝ መሆኑን አብራርቷል።
የኤሮስፔስ መስክ ምርምር እና ልማት ፣ የአውሮፕላን ንድፍ መስራትን እና ማምረትን ያጠቃልላል። ኢትዮጵያ ዘርፉን ለመቀላቀል የመጀመሪያውን አውሮፕላን በጀርመናዊው መሐንዲስ እና የአፄ ሀይለስላሴ አብራሪ በነበረው በጀርመናዊው ሉድቪሽ ቬበር እና በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን መሀንዲሶች ትብብር በጎርጎሪያኑ 1935 «ፀሃይ» ተብላ የምትጠራውን አውሮፕላን መገጣጠም የጀመረች ሀገር ነች።

ፀሃይ ተብላ የምትጠራው አውሮፕላን በጎርጎሪያኑ 1935 በጀርመናዊው መሐንዲስ እና የአፄ ሀይለስላሴ አብራሪ በነበረው በሉድቪሽ ቬበር እና በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን መሀንዲሶች ትብብር የተገጣጠመች ነች።ምስል Office of the Prime Minster Ethiopia
ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ እስካሁን ብዙ አለመጓዟን ባለሙያው ይጠቅሳል።የኤሮስፔስ ቴክኖሎጅ እድገት የአቬሽን እና ሌሎች የቴክኖሎጅ ዘርፎችን የሚመራ ነው። የሚለው ዮናታን፤ ኢትዮጵያ የራሷን ቴክኖሎጅ ባለማሳደጓ ደግሞ ለአውሮፕላን ግዢ እጅግ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣ ያስረዳል።«በዚህ በምንፈጥረው ኢንደስትሪ ምክንያት ያለንን የንግድ ጉድለት መሙላት እንችላለን።የውጭ ምንዛሪያችንን እንቀንሳለን።የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንዴ የሚገዛቸው አውሮፕላኖች ዋጋ የሀገሪቱን አጠቃላይ የ«ኤክስፖርት»ገቢ ይበልጣል።እኛ ከአሜሪካ ጋር ባለን የንግድ ልውውጥ ውስጥ ከፍተኛ ገዢ እና ነን።አሜሪካ አይለችም።ብዙ ጊዜ ይህ እውነት ተሸፋፍኖ ይቀራል።» ዮናታን አያይዞም ይህ ግምት ውስጥ ሳይገባም አሜሪካ እርዳታ እንደምትሰጥ ይታሰባል ብሏል። «ስለዚህ ቡና ፣ሰሊጥ ተሽጦ ሶስት አውሮፕላን የሚገዛ ከሆነ መቼ ነው ማሰብ ያለብን? መቼ ነው ቅንጦት የማይሆነው? መቼ ነው የህልውና ጉዳይ የማይሆነው?» ሲልም ይጠይቃል።
በአቬሽን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?
በሌላ በኩል፤ ኤሮስፔስ እና አቬሽን በረራ ላይ የሚያተኩሩ ዘርፎች ቢሆኑም፤ አቪዬሽን በምንኖርባት ፕላኔት በምድር ከባቢ አየር ላይ የሚደረግን የአውሮፕላን በረራ ወይም ቁጥጥርን የሚመለከት ነው።በአንፃሩ ኤሮስፔስ በምድር ከባቢ አየር እና በህዋ ላይ የሚደረግን የበረራ ሳይንስን የሚመለከት ነው። ምንም እንኳ በዚህ ሁኔታ ሁለቱ ዘርፎች የተለያዩ እና የተለያዬ አደረጃጄት የሚፈልጉ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ግን እንደሌሎቹ ሀገራት የኤሮስፔስ ዘርፍን በብቃት የሚሸከም ተቋም ባለመኖሩ ለመጓጓዣ አገልግሎት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ዘርፍ ደርቦ ለመስራት እየሞከረ ይገኛል።ነገር ግን የኤሮስፔስ ዘርፍን ለማሳደግ የተለዬ ትኩረት እና የተለዬ ተቋም እንደሚያስፈልገው ባለሙያው መክሯል።