ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ውስብስብ የሆኑ የሰውነት ውስጥ ለውጦች/physiological changes/ለተለያዩ የአፍ ውስጥ ችግሮች ሊያጋልጡ ቢችሉም;ብዙ ሴቶች ግን በእርግዝናቸው ወቅት ለአፍ ውስጥ ጤና እንክብካቤ ያን ያህል ትኩረት ሲሰጡ አይታይም።
እናም ይህ በቂ ያልሆነ/የተገደበ/የአፍ ውስጥ ጤና ታድያ ከእርግዝናው አጠቃላይ የሰውነት ውስጥ ለውጦች ጋር ተዳምሮ ለተለያዩ ከጥርስ እና አካባቢው ካሉ አካላት ለሚነሱ ኢንፌክሽኖች (ህመሞች) በቀላሉ ከማጋለጥ አልፈው እጅግ የከፋ የጤና መታወክን ባስሲል ደግሞ የነፍሰጡሯን እና ፅንሱን ህይወት አደጋ ላይ እሰከመጣል ወይም እስከማሳጣት ሊያደርስ የሚችል ኢንፌክሽንን ሊያስከትል ይችላል።
ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱት ጤናማ እና ጊዜያዊ የሆኑ ለውጦች በአብዛኛው ከሆርሞን ጋር የተያያዙ እና እንዲሁም አካላዊ ለውጦች ሲሆኑ ;እነኚህም ለውጦች በተለያዩ የሰውነታችን ክፉሎች ወይም ስርአቶች ላይ የተለያዩ ተፅኖዎችን ሊያሳድሩ ይችላሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ተፅኖዎች ጊዜያዊ እና ሰውነታችን በራሱ ተፈጥሮአዊ መንገድ ሊቆጣጠራቸው ሚችላቸው ወይም ለክፉ የማይሰጡ እና ከወሊድ ቡሀላ ሚስተካከሉ ሲሆኑ : አንዳንዶቹ ግን በጊዜ ታውቀዉ ልንቆጣጠራቸው ካልተቻለ ወደ ከፍተኛ የጤና ችግሮች ሊሻገሩ ይችላሉ።
በእርግዝና ላይ ያለች ሴት በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች የተጋለጠች ስትሆን : ከእነዚህም ውስጥ ደግሞ የአፋ ውስጥ ወይም የጥርስ ኢንፌክሽን አንዱ ነወ።
ለጥርስ /የአፍ ውስጥ ኢንፌክሽን አጋላጭ የሆኑ ዋነኞቹ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች:
1.የአፍ ውስጥ ስጋ አካላት; ድድን ጨምሮ በቀላሉ መቆጣት:ማበጥ:መቅላት:በቀላሉ መቆራረጥ/መበጣጠስ
2.የሰውነት በሽታ የመከላከል ሀይል ለውጥ;የበሽታ መከላከል አቅም ፍጥነቱ መቀነስ/መዘግየት..
3.የእርግዝ ወቅት የስኳር ህመም እና የምራቅ መቀነስ
4.ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ሌሎች አካላዊ ለውጦች እና ተጓዳኝ ህመሞች
እነኚህ ከላይ የተዘረዘሩት እና ሌሎች ያልተጠቀሱ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች ታድያ ለአፍ ውስጥ እና ለጥርስ ኢንፌክሽኖች መነሻነት :እድገት እና ወደ ከፍተኛ ደረጃነት መሸጋገር የራሳቸው ድርሻ አላቸው።
እናም መነሻቸው ቀለል ያሉ የሚመስሉ ወይም የሆኑ የጥርስ እና ተያያዥ አካላት ኢንፌክሽኖች ከእርግዝናው ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የሰውነት ውስጥ ለውጦች እና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች እንዲሁም ከነፍሰጡሯ ወይም ከአንዳንድ የጤና ባለሞያዎች ቸልተኝነት ጋር ተዳምሮ ነፍሰጡር ሴቶችን ከፍተኛ ለሆነ እና የራሳቸውንም ሆነ የፅንሱን ህይወት አደጋ ላይ ለሚጥል የጥርስ ኢንፌክሽን ሊያጋልጣቸው ይችላል።
ከእነዚህ አደገኛ ከሆኑ የጥርስ ኢንፌክሽኖች ውስጥ አንዱ ታድያ ሉድ-ዊግስ አንጂና (Ludwig’s angina) ተብሎ ይታወቃል።
ይህ ከቀላል የጥርስ መቦርቦር ወይም ተያያዥ የአፍ ውስጥ አካላት ኢንፌክሽን ተነስቶ ወደ ተለያዩ የፊታችንክፍሎች:በአንገታችን እና በምላሳችን ስር ባሉ ስጋዎች ውስጥ በፍጥነት በመሰራጨት (እብጠት በመፍጠር) አልፎም ወደታች እስከ ደረታችን ሊወርድ በመቻል የላይኛውን የመተንፈሻ አካላቶቻችንን በመዝጋት(አየር ወደ ሳንባ መተላለፍ በመከልከል) ለከፍተኛ ህመም ስቃይ እና አልፎም ለሞት ሊዳርግ የሚችል የጥርስ ኢንፌክሽን ሲሆን :በእርግዝና ወቅት ላይ ከሆነ የተከሰተው ደግሞ የሚያስከትለው የጤና ቀውስ እጅግ የከፋ እና የእናቲቱንም ሆነ የተሸከመችውን ፅንስ ሂይወት እስከመንጠቅ የደረሰ ነው።
በአብዛኛው የሀገራችን ህብረተሰ ዘንድ የጥርስ ህመም ሲከሰት ወደ ተገቢው ህክምና ባለሞያ ቀጥታ ከመሄድ ይልቅ ካለማወቅም ይሁን ከቸልተኝነት እና የጥርስ ህመምን’ ቀላል ‘አርጎ ከማየትም የተነሳ በተለምዶ የሚወሰዱ የባህል መድሃኒቶችን /መፍትሄዎችን መሞከር ወይም የተለመዱ ጊዜያዊ ማስታገሻዎችን/ መድሃኒቶችን ሀኪም ሳያማክሩ በራስ በመውሰድ ለጊዜው ህመሙን ለማርገብ መሞከር እና ህመሙ በጣም ሲብስ ወይም ለእነዚ ጊዜያዊ መፍትሔዎች አልመለስ ሲል ብቻ ወደ ሀኪም ዘንድ መሄድ የተለመደ ነው።
እናም ይህ ባለማወቅም ይሁን በቸልተኝነት የሚደረግ መዘናጋት ታድያ በተለይ በእርግዝና ወቅት ላይ ሲሆን ለዚህ አደገኛ የሆነ የጥርስ ኢንፌክሽን ሲያጋልጥ እና ብዙ ዋጋ ሲያስከፍል ይታያል።
የጥርስ ኢንፌክሽኑ ወደ አደገኛ ደረጃ አየሄደ ነው የምንለው መቼ ነው?
1.ትኩሳት ሲኖረው
2.ከፍተኛ እብጠቶች ፊት ላይ:አንገት ላይ:ከምላሳችን ስር:በሁለቱም የፊት ጎኖች ላይ ሲከሰት /በፍጥነት እያደገ ሲሄድ
3.ምግብ ለመዋጥ መቸገር እና ማቅለሽለሽ ሲኖር
4.ለመተንፈስ መቸገር ሲኖር
5.አፍችን በከፊል ወይም በሙሉ ለመክፈት ስንቸገር / ሳንችል ስንቀር
6.ድካም እንዲሁም የምራቅ ከአፋችን ውጪ መዝረክረክ ሲኖር…
መፍትሔዎቹ
*በእርግዝና ወቅት ‘ቀላል’የሚባሉ የጥርስ ህመሞች እንኳን ቢሆኑ በጊዜ/በቶሎ እና በተገቢው ባለሞያ መታከም ይኖርባቸዋል
**በእርግዝና ወቅት ላይ ከጥርስ ህመም እና ህክምና ጋር ተያይዘው ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች/አረዳዶችን ማስተካከል
“በእርግዝና ወቅት ጥርስ ፈፅሞ አይነቀልም”
“በእርግዝና ወቅት ለጥርስ ህከምና የሚሰጡ መድሃኒቶች ሁሉ ፅንሱ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ”
“የጥርስ ህመም ቀላል ነው እርግዝናውን ከተገላገልኩ ቡሀላ እታከመዋለሁ”
“በእርግዝና ወቅት የጥርስ ራጆች እና ህክምናዎች ፅንሱን ይጎዳሉ”…
እነዚህ እና ሌሎችም የተሳሳቱ ወይም በከፊል የአረዳድ ችግር ያለባቸው በህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት የተሰራጩ አመለካከቶች ታድያ ብዙዎችን እርጉዝ ሴቶች የጥርስ ህመም ሲያጋጥማቸው ወደ ተገቢው ባለሞያ እንዳይሄዱ የሚያዘናጓቸው ምክንያቶች ሲሆኑ ይህም ለከፍ የጥርስ ኢንፌክሽን ሲዳርጋቸው ይታያል።
ህክምናዎቹ
*ህክምናው ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ የእናቲቱን ጥቅም (ጤና ያስበለጠ) ያስቀደመ እንዲሁም በፅንሱ ላይ ሊደርስ የሚችልን ማነኛውም ጉዳት መቀነስን አለማው ያደረገ ነው።
*በእርግዝና ወቀት ላይም እንኳን ቢሆን የተለያዩ የአፍ ውስጥ እና የጥርስ ኢንፌክሽኖች በተለያዩ የጥርስ ህክምናዎች:ጥርስን ከመንቀል ጀምሮ የተመረጡ መድሃኒቶች እስከመስጠት እንዲሁም መለስተኛ እና ብሎም ከፍተኛ የቀዶ ህክምናዎችን በተገቢው ባለሞያ:ሁኔታው ባገናዘበ መልኩ ተገቢውን ወቅት/ጊዜ በማመቻቸት በእናቲቱም ሆነ ፅንሱ ላይ ጉዳት በማየስከትል/በቀነሰ መልኩ ሊሰጥ ይችላል።
*ማንኛውም የጤና ባለሞያ ቢሆን የእዚህ አይነት አደገኛ የሆነ የጥርስ ኢንፌክሽኖችን ምልክት ምታሳይ ነፍሰጡር ሴት ስታጋጥመው ያለምንም ማመንታት ታካሚዋን በአስቸኳይ ተገቢውን ህክምና ወደምታገኝበት ሆስፒታል በተለይ : የማግዚሎፋሻል ሰርጅን :የማህፀን እና ፅንስ እንዲሁም የአንስቲዢኦሎጂስት ስፔሻሊስቶች እና የፅኑ ህሙማን ከፍል ወደያዘ ተቋም መላክ ይኖርበታል።
ቸር ያሰማን!!
Dr. Fuad M, Assi.Prof. of Oral & Maxillofacial surgery
Telegram: t.me/HakimEthio