ኢትዮጵያ ከሶማሊ ላንድ ጋር ለምን የባህር በር ስምምነት ፈጸመች በሚል ለዓመታት ለሶማሌ ደህንነት ህይወት የከፈለውን የሰላም አስከባሪ ሰራዊት እንዲወጣ ስትዝት የነበረችው ሶማሊያ በአደባባይ ” የሰላም አስከባሪዎች ይቆዩልኝ” ስትል ተማጽኖ አሰምታለች። አልሸባብ ዳግም ማንሰራራቱ ሶማሊያን ብቻ ሳይሆን ድፍን ቀይ ባህርንና ጎረቤት አገራትን አስግቷል።
ቢቢሲ ሮይተርስን ጠቅሶ ይህን ዘግቧል። የአል-ሸባብ ዳግም መልሶ የመደራጀት ስጋትን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ከአገሪቱ የሚወጡበትን ጊዜ እንዲያራዝሙ ጠየቀች።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የመንግሥት ሰነዶችን ተመልክቶ እንደዘገበው በቀጠናው ያሉ ጎረቤት አገራት አል-ሸባብ ስልጣን ሊይዝ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትም ሰላም አስከባሪዎችን ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅት ከሶማሊያ ማስወጣት “በአገሪቱ የደኅንነት ክፍተት ይፈጥራል” ሲል አስጠንቅቆ ነበር።
በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ተሰማርቶ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ትራንዚሽን ሚሽን ኢን ሶማሊያ (የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ) – አትሚስ እአአ በ2024 መጨረሻ ቆይታው ይጠናቀቃል።
በዕቅዱ መሠረት የሰላም አስከባሪ ኃይሎቹ ቀስ በቀስ እየወጡ 2024 ማብቂያ ላይ ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው ከሶማሊያ ከወጡ በኋላ የሶማሊያ ጦር ኃላፊነቱን ይረከባል።
ይሁን እንጂ የሶማሊያ መንግሥት ለአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ደኅንነት ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ ሰኔ 2016 ዓ.ም. መውጣት ያለባቸው የ2000 ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ቆይታ እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም. ድረስ እንዲራዘም ጠይቋል።
የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ከአገሪቱ በማስወጣት ረገድ በተለይ ደግሞ በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሠራዊትን በተመለከተ በባለስልጣናት መካከል የተለያዩ ሃሳቦች ሲንጸባረቁ ቆይተዋል።
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የኢትዮጵያን ሠራዊት ከሶማሊያ ለማስወጣት ቢወስንም አንዳንድ የሶማሊያ ግዛት መሪዎች እና የምክር ቤት አባላት ውሳኔውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት መፈረሟ በሁለቱ አገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት ፈጥሯል።
የአትሚስ ዕጣ ፈንታ
በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ -አትሚስን በገንዘብ የሚደግፉት የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ፤ ሰላም አስከባሪ ኃይሉን ለረዥም ጊዜ በገንዘብ መደገፍ አዋጭ እና ዘለቄታዊ አይደለም ብለው እንደሚያምኑ 4 የዲፕሎማቲክ ምንጮች እና አንድ ከፍተኛ የኡጋንዳ መንግሥት ኃላፊ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የሮይተርስ ምንጮች በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሹ መካከል የተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አል-ሸባብን በመዋጋት ልምድ ያዳበረውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በአገሪቱ የማስቀጠል ንግግርን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል።
የአትሚስ ኃላፊ እና በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ተወካይ የሆኑት ሞሐመድ ኤል-አሚን ሱኤፍ፤ ሰላም አስከባሪ ኃይሉ የሚወጣበትን ጊዜ በተመለከተ እስካሁን የተቆረጠ ቀን የለም ካሉ በኋላ ሁሉም አካል ለሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
ኃላፊው የሶማሊያ መንግሥት እና የአፍሪካ ኅብረት ዋና ትኩረት ሰላም አስከባሪ ኃይሉ ከአገሪቱ ሲወጣ የደኅንነት ከፍተት እንዳይፈጠር ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ሶማሊያ በአል-ሸባብ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ አጠናክራ ቀጥላ በቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱ ሲገለጽ ነበር።
ይህን ተከትሎም የሶማሊያ መንግሥት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች አገሪቱን ለቀው ሲወጡ ሞቃዲሾ ደኅንነት የማስጠበቅ ስራውን መውጣት እንደምትችል መተማመን ፈጥራለች።
ይሁን እንጂ በቅርቡ እስላማዊ ቡድኑ እራሱን እያደራጀ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
የጎረቤት አገራት ስጋት
ሶማሊያን ለቅቆ በሚወጣው ሰላም አስከባሪ ውስጥ ሠራዊት አዋጥተው የቆዩት ኡጋንዳ እና ኬንያ የአገሪቱ ደኅንነት ያሰጋናል ይላሉ።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄነሪ ኦኬሎ ኦርዬም የሶማሊያ ሠራዊት ረዥም ስልጠና ቢሰጠው እንኳ ለረዥም ጊዜ በውጊያ ውስጥ መቆየት አይቻለውም ብለዋል።
ሚኒስትሩ ለሮይተርስ ሲናገሩ “ተቻኩለን ወጥተን አፍጋኒስታን እንደተፈጠረው አይነት ነገር እንዲፈጠር አንፈልግም” ብለዋል።
ሚኒስትሩ ኬንያም ብትሆን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ጥያቄን ተከትሎ ከሶማሊያ ለመውጣት ብትስማማም በሶማሊያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት መግባት አለበት የሚል አቋም አላት ብለዋል።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዋሽንግተን በነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅት መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ሳናገናዝብ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች እንዲወጡ ከወሰንን “አሸባሪዎች ሶማሊያን ይረከቧታል” ብለው ነበር።
በተመሳሳይ በቅርቡ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ሲናገሩ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሶማሊያ ግዛት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ “የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ መካለከያ ሠራዊት ነው” በማለት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነገ ቢወጣ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሞቃዲሾ የሚቀመጥ አይመስለኝም” ብለዋል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው