የ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሆኖ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ21 ነጥብ አንድ በመቶ እድገት ማሳየቱም ተጠቁሟል፡፡
ለመደበኛ በጀት የዓመቱ የወጪ በጀት 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ደግሞ 283 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሆንም ታሳቢ ተደርጓል፡፡
ለክልል መንግሥታት 14 ቢሊዮን ብር ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚሆን የበጀት ድጋፍ ለማድረግም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተመላክቷል፡፡
ምክር ቤቱም ለ2017 በጀት ዓመት የቀረበውን ረቂቅ በጀት ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል፡፡
በጀቱ በዚህ ልክ መጨመሩ ለሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል? በበጀት ዓመቱ ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትስ ይገባል?
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገና በማደግ ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች የሚመደብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ በጀት በቁጥር ደረጃ ስንመለከተው እድገት መኖሩን የሚያመላክት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዋጋ ንረት አንጻር ከቀደሙት ዓመታት ጋር ያለው እድገት ምን ያህል ነው የሚለውን ማጥናት ይፈልጋል ይላሉ፡፡
የአንድ ሀገር ዓመታዊ በጀት ነባራዊ ሁኔታውና ሀገራዊ እቅዶችን መነሻ ባደረገ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ ይጠበቃል የሚሉት ባለሙያው፤ በጀት በባህሪውም እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት የሕዝብ ቁጥር እያደገ ስለሚመጣ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችና ሌሎችም መሠረታዊ ፍላጎቶች እየጨመሩ ይመጣሉ፡፡
ለእነዚህ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ደግሞ የመንግሥት በጀት እያደገ መምጣት አለበት፡፡
በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ መንግሥት፣ ኢንቨስተሮችና ተጠቃሚዎች ዋንኛ ተዋናዮች መሆናቸውን የሚገልጹት መምህሩ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ገና በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ በመሆኑ መንግሥት ኢኮኖሚው ላይ ያለው ድርሻና አጠቃላይ ለሚመዘገቡ እድገቶችና ለውጦች ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም በጀቱ ከፍ ማለቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ይላሉ፡፡
እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ የመንግሥት በጀት ዋንኛ ምንጭ ከኅብረተሰቡ የሚሰበሰብ ግብር እንዲሁም ከብድርና እርዳታ የሚገኝ ገንዘብ ነው፡፡
ስለሆነም ይህ በጀት በዋናነት ለሰፊው ኅብረተሰብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡
በተለይም ትምህርት፣ ጤና ግብርናና መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚያመለክቱት መምህሩ፤ መሠረተ ልማት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚውን ለመገንባት፣ ለማንቀሳቀስና የግሉን ዘርፍ ሥራዎች ለማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
የሰው ሀብት ልማት ማለትም ትምህርትና ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚጠቅሱት ምሁሩ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዘውና የአብዛኛው ሕዝባችን የተሠማራበት ግብርናም ሌላኛው የትኩረት መስክ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የግብርና ሥራውን ምርትና ምርታማነት የሚደግፉ ግብዓቶችና ኢንቨስትመንቶች ላይም መሥራት ይጠበቅብናል ይላሉ፡፡
ያደጉ ሀገራት የመንግሥት ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ድርሻ እየቀነሰ እንዲሄድ እየሠሩ መሆኑን የሚያስታውሱት መምህር ፍሬዘር፣ እኛ ጋር ግን የግሉ ዘርፍ ገና በማደግ ላይ ያለ በመሆኑ መንግሥት እንዲደርስባቸው የሚጠበቁ ዘርፎች በርካታ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የመንግሥት ወጪ ልማት ላይ ከዋለ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ መሠረት መሆኑን የሚያስታውሱት መምህሩ፤ ለዚህ ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልና አስፈላጊውን የክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የተጠያቂነትን ሥርዓት ማስፈን ያስፈልጋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጀቱ እየጨመረ መምጣት የሚጠበቅ ሂደት ነው፡፡ ትኩረት ማድረግ ያለብን ግን የተያዘው በጀት በአግባቡ ሥራ ላይ ውሎ ፍሬያማና ምርታማ መሆኑን ማረጋገጥ ላይ ነው ይላሉ፡፡
በጀቱ ጥቅም ላይ ውሎ የምናልመውን ውጤት እንዲያመጣ ተቋማት በሚጠበቅባቸው ልክ መገኘት እና የአሠራር ሕግና ደንቦች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ ማድረግ ይገባል የሚሉት ምሁሩ፤ በተለይ የውጭ እዳ ጫናን ለማቃለልና ምርትና ምርታማትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይጠበቃል፡፡
የግብርናን ጨምሮ ሌሎችም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ፡፡
አምራች ዘርፉን በማጠናከር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የሚያስታውሱት ምሁሩ፤ ሀገራዊ አቅም እስኪፈጠር ድረስም ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ኢንዱስትሪ ማስገባትና ገቢ ምርትን ለመተካት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅም አንዱ ቱሪዝም እንደሆነ የሚጠቁሙት ዶክተር ይንገስ፤ በበጀት ዓመቱ አንዱ ትኩረት ማግኘት ያለበት በቱሪዝም መስክ ያሉ እድሎችን አሟጦ መጠቀም ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በጀቱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ከሚሠሩ ሥራዎች ጎን ለጎን የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን የሚያመላክቱት ዶክተር ይንገስ፤ ለዚህ በየደረጃው ያለው አመራር በጀቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታና የዜጎች ሕይወት እንዲሻሻል መሥራት ያስፈልጋልም ሲሉ ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በጀቱ በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ አለበት የሚሉት ባለሙያው፤ ከቦታ ቦታ በነጻነት ተንቀሳቅሶ መሥራት የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ቅድሚያ ማግኘት ያለበት ተግባር ነው፡፡
እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ የአንድ ሀገር ዓመታዊ በጀት እየጨመረ እንዲሄድ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ በጀት እያደገ መምጣት የሚጠበቅ ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን በጀቱ ምርት ምርታማነትን ሊያመጡ በሚችሉና የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም ሊያረጋግጡ የሚችሉ መስኮቸ ላይ እንዲውል መሥራት ተገቢ ነው፡፡
ለሁሉም ሥራዎች መሠረቱ ሰላም በመሆኑ ሀገራዊ ሰላምን ማረጋገጥና ዜጎች ከቦታ ቦታ በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠርም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ አዲስ ዘመን ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም