በተለያዩ ሚዲያዎችና ባለሙያዎች “ሰማን” መንግስት የብርን የመግዛት አቅም ለማዳከም መስማማቱን በተደጋጋሚ ቢገልጹም የግንዘብ ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው በሚልየፌዴራል መንግሥት የ2017 በጀት ሲዘጋጅ ብርን ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሬ ተመን የሚያዳክም አሳብ እንደሌለ ይፋ አድርገዋል። ዓመታዊ በጀቱ ሲዘጋጅም ብርን የማዳከም አካሄድ ይኖራል በሚል ታሳቢነት እንዳልሆነ ተመልክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ለተወካዮች ም/ ቤት ቀርበው በኢመደበኛውና በባንኮች በሚደረግ ይፋዊ ምንዛሬ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያጠብ እርምጃን እንደሚወስድ በተባራሪ የሚወጡ መረጃዎችን እንደ ስጋት በመውሰድ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው ” ምንም የቀረበ ነገር የለም ” በሚል ጉዳዩን ጭራሽ መንግስት እንዳላየው አስታውቀዋል። አክለውም የመንግሥት በጀት የተዘጋጀው ” የነበረው አካሄድ እንደሚቀጥል ታሳቢ ተደርጎ ” እንደሆነ አመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ” ዘንድሮ የነበረውን ይፋዊ የውጭ ምንዛሬ መጠን ታሳቢ አድርጎ ነው በጀቱ የቀረበው ” ሲሉም አጽንኦት ማብራሪያቸውን የተከታተሉ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ተናግረዋል።
በም/ቤቱ የኢዜማ ተወካይ ዶ/ር አብርሃም በርታ ” ህጋዊውን እና ኢመደበኛውን የውጭ ምንዛሬ ገበያ እኩል ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች እንዳሉ ከአንዳንድ ወገኖች እየሰማን ነው” ብለዋል። ጠያቂው አክለውም የውጭ መንግስታት በብድር ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር ይህንኑ ለማስፈጸም እንደሚንቀሳቀሱ የሚገልጹ መረጃዎችም መኖራቸውን ጠቁመዋል። እንዲህ አይነቱ እርምጃ የማንወጣው ችግር ውስጥ ይከተናል የሚል የባለሙያዎች ትንታኔ አለ ” ላሉት ነበር አቶ አሕመድ ሸዴ መልስ የሰጡት።
በተያያዘ ዜና ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ከሚልከው ገንዘብ(ሬሚታንስ) ባለፉት 5 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
በተጨማሪም ዳያስፖራው ለሀገራዊ ጥሪዎችና የልማት ስራዎች እያደረገ ያለው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ተገልጿል።
የ2016 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የመጨረሻ የሆነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት ተጀምሯል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በዚሁ መድረክ ያለፉት 100 ቀናትና የሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል።
በሪፖርታቸው በ2016 በጀት ዓመት 10 ወራት የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ከላኩት ገንዘብ(ሬሚታንስ) 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ የተሻለ እድገት ማሳየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ባለፉት 5 የለውጥ ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ዳያስፖራው ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር እየላከ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከዳያስፖራው እየተገኘ ያለው ገቢ ከለውጡ በፊት ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ አንጻር ከፍተኛ እድገት ያለው መሆኑን ጠቅሰው እድገቱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች የተገኘ ነው ብለዋል።
ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ የሚልኩትን የገንዘብ መጠን ለማሳደግ ገንዘብ የሚልኩባቸውን አማራጮች ቀልጣፋ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስምንት ወራት 1 ሺህ 745 የዳያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥሮችን በመክፈት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተቀማጭ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ድርሻ ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ 9 ወራት 17 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 210 የዳያስፖራ ፕሮጀክቶች በክልሎች መሬት እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል 21ዱ ወደ ስራ ገብተው ለ1 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዘጠኝ ወራቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ከስጦታና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች፣ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እንዲሁም ለልዩ ልዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ከዳያስፖራው ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጥሬ እና በአይነት ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የዳያስፖራው ማህበረሰብ ልዩነት ሳይገድበው በሀገሩ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
መንግስት የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ዳያስፖራው በሀገራዊ ጥሪዎችና የልማት ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ በላይነህ አቅናው ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ አመልክቷል።