የአማራ ክልል አመቻች የሰላም ካውንስል መንግስትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ለውይይትና ድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቀረበ። ጥሪው
የአማራ ክልል አመቻች የሰላም ካውንስል መንግስትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁመው ለውይይትና ድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቀረበ።
“ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ ሃሳብ ያመጣሉ ተብለው ከተመረጡ የማኅበረተሰብ ክፍሎች ጋር ከሰኔ 17/2016 ዓ.ም እስከ 18/2016 ዓ.ም በተደረገው የባሕር ዳር ጉባኤ ሁለት ቀን ከመከረ በኋላ በመጨረሻም ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ደረጃ በየትኛውም ቦታ በየትኛውም አደራደሪ የመንግስት ኀይሎች እና በጫካ የሚገኙ የፋኖ ወንድሞቻችን የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ መወሰኑ ይታወሳል።
ጉባኤው ቢያንስ ዘላቂ ተኩስ ለማቆም ንግግርና ድርድር እንዲያደርጉ ጉባኤው በወሰነው መሰረት 15 አባለት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል መሰየሙም የሚዘነጋ አይደለም። በመሆኑም የተመረጠው የሰላም ካውንስል ሲመክር ሰብቶ ዛሬ ሰኔ 22/2016 ዓ.ም ሁለቱም ወገኖች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ አስተላልፏል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን የሰላም ቀውስ ለማስቆምና በሰላማዊ ውይይት ክልሉን ለማርጋት ብሎም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስትና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ እንዲመጡ ለማመቻቸት የተሰየመው አስራ አምስት አባላት ያሉት የማህበረሰብ ተወካዮች የተካከቱበት ካውንስል፣ የተኩስ ማቆም ጥሪውን ሲያስተላለፍ አክሎም ለአንድ ዓመት የዘለቀውን ግጭት ለመፍታት ሁሉም ተፋላሚ ሀይሎችን ለማወያየት መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል። ካውንስሉ በኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት የተፈታ ችግርም የመጣ መፍትሔም እንደሌለ ገልጿል።
በመሆኑም የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል የተከሰተው አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ ጠይቋል።
መንግስት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ለሰላም ውይይት እና ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጫ እንዲያሳውቁም ጥሪ ማቅረቡን መግለጫው ያስረዳል። ሙሉ መግለጫው ከስር ያለው ነው።

የአማራ ክልል ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተው ሚና ከፍተኛ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያን ብቻውን ጠፍጥፎ የሠራት ይመስል አንዳንድ የሀገሩ ልጆች የቀኝ ገዥዎችን ሃሳብ በመቀበል የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክት በመፍጠር በተነዛው የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ክልሉን አሁን ላለበት ደረጃ አድርሶታል ብለው የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። እርግጥ መልኩ መቀየሩ ካልሆነ በስተቀር እርስ በርስ መዋጋት መፍትሄ ያላመጣ ፣በድህነት ወደኋላ እንድንቀር ያደረገን ፣በሺ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረና ያለ ልንሻገረው ያልቻልን በኋላ ቀርነታችን መገለጫ እንጂ አሁን አዲስ ተፈጥሮ የሚያስደንቀን አይደለም።
ምን አልባት ሊያስደንቀን የሚችለው ከታሪካችን መማር አቅቶን ለዛውም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ጋርዮሽ ዘመን በሚመለስ አይነት አስቀያሚ የእርስ በርስ ጦርነት እያስኬደን መገኘታችን ነው። ከሺ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ሀገር ይዘን መደማመጥ፣ መነጋገርና ወደ ጦርነት ሊወስዱ የሚችሉ ቸግሮቻችንን በድርድር መፍታት አቅቶን በሴራ ፖለቲካ፣ በኋላ ቀር አመለካከት ወንድም ወንድሙን እያጠፋ ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ኢትዮጵያዊያን ብዙ የሚያኮራ አድዋን የመሰለ ታሪከ ያለን ቢሆንም እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ይዘነው የዘለቀው የእርስ በርስ ግጭት ግን የታሪካችን ስብራት፣ መሻገር ያቃተን ሁነት መሆኑ ሁላችንም የኢትዮጵያ ዜጎች ሊቆጨን፣ ሊከነክነንና የመፍትሔ ሃሳብ እንቅልፍ አጥተን ልናስብ ይገባል። እርግጥ አንዳንድ ምሁራን ጦርነት የሀገረ መንግሥት ግንባታ አንዱ አካል አድርገው ቢወስዱትም እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ካለን ስሪትና ከመጣንበት መንገድ አንጻር ስንቃኝ በጦርነት እንጨራረሳለን እንጂ አንሸናነፍም። በአሁኑ ሰዓት የአማራ ሕዝብ በዚህ ዘመን ሊፈጠር የማይገባው ግጭት ተፈጥሮ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል አጋጥሞት ይገኛል። አማራ ክልል ተከስቶ ያለው ግጭት አጠቃላይ ሀገራችንን ለጉዳትና ወደ ባሰ ድህነት አረንቋ እየወሰዳት መሆኑ ግልጽ ነው።
ለዚህ ግጭት መነሻ ምከንያት የአማራ ሕዝብ ለዘመናት ሲጠይቃቸው የነበሩ ጥያቄዎች በሠለጠነ ንግግርና ድርድር አለመፈታታቸው ወይም የሚፈቱበት ሂደት ግልጽ ፍኖተ ካርታ አለመቀመጡ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ዋና ዋናዎቹ የአማራ ክልል ሕዝብ ጥያቄዎች ተብለው የተለዩት፦
1. የተዛባ ትርክትን ማረቅና ማስተካከል
2. የሕገ መንግሥት መሻሻልን
3. የወሰንና የማንነት ጉዳይ
4. ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የውክልና ጉዳይ
5. በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ሕዝብ ጉዳይ
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃን የአማራ ተወላጆች ለሚደርሰባቸው ግድያና መፈናቀል ተጠያቂነት ያለመስፈን ጉዳይ ወዘተ የሚሉ ሁነው ለበርካታ ዓመታት ትግል ሲደረግባቸው ቆይቷል ።
እነዚህ ጥያቄዎች በሀገሪቱ ጥላ ስር በቅንነት በንግግርና በድርድር ሊፈቱ የሚገባቸው እንጂ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚፈታተኑ ጥያቄዎች ይመስል ወደ ጦርነት የሚያስገቡ አልነበሩም። በተለይ በ2008 በኢትዮጵያ አቆጣጠር የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በ2010 በነበረው ለውጥ “የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ሊመልሱ ይችላሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ለጥያቄዎቹ በቂ ትኩረት ሳይሰጥቸው ቀጥሏል።
አሁንም የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምን ላይ እንዳሉ ምን አይነት የመፍቻ መንገድ እንደተዘጋጀላቸው በተግባር የታዬ ግልጽ ነገር የለም ብሎ ያመነው ሕዝቡ ጥያቄዎች እንዲመለሱለት በሰላማዊ መንገድ ማለትም በሕዝባዊ ሰልፍና ስብሰባ እንዲሁም በኮሚቴዎችና የሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት በተደጋጋሚ ሲጥይቅ ቆይቷል። የክልሉ መንግስትም በሕዝቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሂዷል። በተጨማሪም ከችግሩ የሚያወጣው ስትራቴጂካልና ታክቲካል መሪ እያጣ እንዲሁም የተደራጀ የፖለቲካ ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ የሚፈጥርለት ምሁር የመከነበት እስኪመስል ድረስ ደርሷል።
ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚና የማህበራዊ መገለልን የሚቀርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ ክልሉ በተለያዩ ወቅታዊ አጀንዳዎች በመወጠርና የደህንነት ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ በማድረግ ለከፋ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተጋልጦ ይገኛል። በተለይ በቅርቡ የፌደራል መንግስት ከህወሃት ጋር በነበረው ጦርነት ለማስቆም ያደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት በአግባቡ ሳይተገበርና የአማራ ሕዝብ የህልውና ስጋት ዋስትና ሳይበጅለት የክልሉ ልዩ ኀይል መፍረስና በጦርነት ተሳትፎ የነበራቸው ታጣቂዎች ለሕዝቡ በቂ ግልጸኝነት ሳይፈጠር በክልሉ መንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች በሕዝቡ ላይ ጥርጣሬና ስጋት ፈጥረውበታል።
በዚህ ምክንያት የከልሉ የጽጥታ ችግር አየተባባሰ የመጣ ሲሆን ከሀምሌ ወር መጨረሻ 2015 ጀምሮ በክልሉ በነፍጥ የታገዘ ግጭት የተጀመረ ሲሆን ጉዳዩ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አስቸግሯል በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አንድ ዓመት ለተቃረበ ጊዜ የተደረገው ጦርነት ሕዝቡ መከራና ምስቅልቅል ሕይዎት ውስጥ ገብቶ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ በርካታ የከልሉ አካባቢዎች በመንግሥትና የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ጭካ ገባን ባሉ ፋኖዎች መካከል በሚካሄድ በትጥቅ የታግዘ ግጭት ወይም ጦርነት ሳቢያ ብዙ የሕዝብ ሃብት ከ12 እስከ 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፤ ንጹሃን ተገድለዋል ፤ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ዉጭ ሁነውል ፤የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ክፉኛ ተጎድቷል ፤የግልና የመንግስት ተቋማት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ባለምቻላቸው ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጥ ከፉኛ ተዛብቷል።
ነፍሰጡር እናቶች በአግባቡ የአምቡላንስና የወላድ አገልግሎት አያገኙም፤እናቶችና ህጻናት ከጦርነት ተሳትፎ ዉጭ የሆኑ የክልሉ ዜጎች ለከፋ የስነ ልቦና ጫና ተዳርገዋል፤ እገታ ተስፋፍቷል፣ ዜጎች ያለከልካይ በጠራራ ጸሃይ ይዘረፋሉ፤ ይገደላሉ፤ ታላላቅ ፕሮጀከቶች ተስተጓጉለዋል፤ ሕዝቡ ለሁለት ወገን ግብርና ቀረጥ ይከፍላል እና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ግጭቱ ወይም ጦርነቱ ካመጣቸው መዘዞች በጥቂቱ ናቸው።
ይህን ቀውስ በመረዳት ከሰኔ 17/2016 እስከ 19 /2016 አዲስ አበባን ጨምሮ በ8 መድረኮች ችግሩን በትክክል አንስተው የመፍትሄ ሃሳብ ያመጣሉ የተባሉ ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ ተጽእኖ ፈጣሪ የማህበረሰብ ከፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል። በኋላም በ8ቱ መድረኮች በተሳታፊዎች ከተመረጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ከሰኔ 17/2016 እስከ 18/ 2016 ዓ.ም ከሀገሪቱ የጦር ጀኔራሎችና መኮንኖች እንዲሁም የሲቪል አመራሮች ጋር ምክከር ተደርጓል።
በመጀመሪያው ዙር በ8ቱ መድረኮች የተነሱ የመፍትሄ ሃሳቦችና በየቀጠናው የተሰጡ የማጠቃለያ መግለጫዎች መለያየትና ቅሬታ የነበረባቸው ቢሆንም በባሕር ዳሩ ማጠቃለያ መድረክ ግን ከሞላ ጎደል በመድረኩ የተነሳው የመፍትሄ ሃሳብ መግባባትን ፈጥሯል። በዚህ ጉባኤ ጦርነቱ አሸናፊ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ስለሆነ በንግግርና በውይይት በድርድር ይፈታ የሚል ድምዳሜ ተደርሷል። ይህ ደግሞ በክልል ደረጃ ሊሆን ይችላል ፤ በሀገር ደረጃ ሊሆን ይችላል፤ ብቻ በየትኛውም መንገድ ይሁን የአማራን ሕዝብ ጥቅም ይዤ ነው የምዋጋው ከሚል ኀይል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ንግግርና ድርድር እንዲደረግ የሚል የጉባኤው ማደማደሚያ የመፍትሄ ሃሳብ ነበር።
በጉባኤው ማጠቃለያ መንግሥት ይህ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው አውዳሚ የእርስ በእርስ ጦርነት በንግግርና በድርድር ለመፍታት ፈቃደኛ ነኝ ነገር ግን ፋኖ አደረጃጀቱና መሪው ብዙ ነው። ለመደራደር አንድ መሆን አለባቸው በማለቱና የድርድሩ ደረጃ ፣ጊዜና ቦታ ተደራዳሪዎች ተለይተው ሁለቱን ወገኖች እያነጋገረ ለንግግርና ለድርድር ጥረት የሚያደርግ 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል ተመርጧል።
ካውንስሉ በርካታ ሃላፊነትና ተግባራት ያሉት ሲሆን ከነዚህ መካከል፦
1. ካውንስሉ በሁለቱም ወገኖች እስካልተመረጠ ድረስ አመቻች እንጂ አደራዳሪ አይደለም ። አመቻች ማለት ሁለቱ ወገኖች እኩል ድርድርና ንግግር እንዲቀበሉ አደራዳሪና ተደራዳሪ እንዲመርጡ ቦታና ጊዜ እንዲወስኑ እያለቀ ያለውን ንጹሃን እየተጎዳ ያለው ማህበረሰብ ከፍል ግምት ውስጥ አስገብተው ተኩስ አቁመው እንዲነጋገሩ የማግባባትና የማመቻቸው ሥራ ይሠራል ማለት ነው።
2. ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱም ወገኖች በቅንነት እንዲቀራረቡና እንዲደራደሩ የአመቻችነት ሚናውን ይወጣል። ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት አያስተናግድም። በጉባኤው ማደማደሚያ መስረት ሥራውን ይወጣል።
ለፌደራል መንግሥት ፣ለአማራ ክልል መንግሥና ለፋኖ ኃይሎች፦
እየተደረገ ያለው የእርስበርስ ጦርነት ነው። ወንድም ከወንድሙ ልጅ ከአባቱ ጋር መገዳደል ነው። በእርስ በርስ ጦርነት የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለም። በሺ አመታት ተሞከሮ መፍትሄ ያላመጣ የእርስበርስ ጦርነት ዛሬ ለዛውም የዘር፣ የብሄርና የሃይማኖት አዝማሚያ ታክሎበት የሚደረግ የእርስ በርስ ጦርነት ከመተላለቅ ውጪ አንዳችም መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም። ለአኛ ለኢትዮጵያውያን ሰበር ዜና ሊሆን የሚችለው መፍትሄ የማያመጣ የእርስ በርስ ጦርነት ማድረጋችን ሳይሆን ከመገዳደል ወጥተን ፖለቲካዊ ልዩነታችን በውይይት፣ በመነጋገር፣ በመደራደርና በሰጥቶ መቀበል በሚፈታ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ስንገባና ባህል ስናደርግ ያኔ ነው ለኢትዮጵያ ሰበር ዜና መባል ያለበት። ስለሆነም የወገናችሁ ስቃይ ተረድታችሁ መሸናነፍ በማትችሉበት ጦርነት ከመቆየት ሁለታችሁም ማሸነፍ ወደ ምትችሉበት ንግግርና ድርድር እንድትገቡ አመቻች የሰላም ካውንስሉ አበክሮ ይጠይቃል፣ለማግባባትም ይጥራል።
አንደኛ ለፌደራል መንግስትና ለአማራ ከልል መንግስት መግለጽ የምንፈልገው ይህ የሰላም ካውንስል ሲቋቋም በርቱ፣ሞከሩ ከጎናችሁ ነን የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ በሌላ ወገን ደግሞ ለሌላ አላማ ወይም ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስመሰል ካልሆነ በስተቀር እናንተ የምትሉት መንግድ መንግስት የሚቀበለው አይመስለንም ብለው ስጋታቸውን ሲገልጹ ይሰማል።እርግጥ ሲሆን ከኖረውና እየሆነ ካለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አንጻር የሚጠበቅ አባባል ቢሆንም የህዝባችን ስቃይ አይተን በቅንነት ለምናቀርበው ሃሳብ መንግሥት በቅንነት ተረድቶ ቀጥታ በንግግርና በድርድር የእርስበርስ ጦርነት የምናቆምበት መንገድ ብቻ እንድናተኩር ከመንግስት መታመንን የሰላም ካውንስሉ በትልቁ ይጠብቃል።
ሁለተኛ ለፋኖ ወንድሞቻችንም አጥብቀን ማሳሰብ የምንፈልገው ህዘባችሁ ያለበት ስቃይ ተረድታችሁ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለው ጦርነት ከመቀጠል ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርግ የሚችለው የድርድር መርህ ተቀበላችሁና ተከትላችሁ እንታገልለታለን የምትሉትን የህዝብ አጀንዳ በንግግርና ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ እንድትሆኑ እንጠይቃለን።
ለፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ለምሁራንና ለማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፤ ለመላው የአማራ ክልል ነዋሪና ለቀሪው የሃገራችን ህዝብ ከፍል፤በውጭ ሀገር ለምትኖሩ የአማራ ክልል እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ
የአማራ ከልል ወገናችሁ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ስቃይ ውስጥ ነው ብለን ስንነግራችሁ ሰምተን ሳይሆን አይተንና መከራና ስቃዩ ግድያው አልፎብን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ በ21ኛው ክ/ዘመን አስቀያሚ ጦርነት እያደረግን ያለነው ሰላማዊ ትግል እግር ባለመትከሉና ህዝቡ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ ትግል እንዲከተል ያልሆነው ሁላችንም የየራሳችን የድከመት ድርሻ አለብን ብለን አለማመናችን ነው።የእርስ በርስ ጦርነት እየተፈጠረ ያለው በሰላማዊ ትግል የሚያምን ፖለቲካል ማህበረሰብ አለመፈጠሩ ነው ።የፈለገውን ያህል ጦርነት ቢካሄድ ወጣቱ ካለቀ በኋላ አዋጊዎች ወደ ድርድር እንደሚመጡ ከሰሜኑ ጦርነት መማር ያስፈልጋል።ስለሆነም በእናንተ በኩል ስቃይ ውስጥ ያለውን ማህበረሰብ የእርስ በርስ ጦርነት ማባባስ ሳይሆን ሁለቱ ወገኖች ንግግርና ድርድር የሚያስቀድሙበትን መንገድ ውስጥ እንዲገቡ መገፋፋት ማበረታታትና ማገዝ ትልቁ ድርሻቸሁ እንዲሆን እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ሰላም የግለስብ ፤የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ፤የተማሪዎች ፤የሴቶችና የወንዶች የሃይማኖት አባቶች የባለሃቶች፣የአንድ ክልል ህዝብ ፤የመንግስት ሃይሎች፤ጭካ የገቡ የፋኖ አባላት የብቻ ጉዳይ አይደለም።ሰላም የሁሉም ከሁሉም ነው።ስለሆነም በየደረጃው ጥሪ የተደረገላችሁ አካላት የበኩላችሁን እንድትወጡና ይህ የሰላም ጥሪያችን በአዎንታዊ መልኩ ታይቶ የሀገራችንን ሰላም በጋራ እናምጣ፣የወንድማማቾች መገዳደል ይብቃ በማለት የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ጥሪውን ያቀርባል።