ከአፍሪካ ሕብረት ሒሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር የምዝበራ ሙከራ ጋር ተያይዞ የተከሰሱት እነ ቀሲስ በላይ መኮንን ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዙ።
ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹም 1ኛ ቄስ በላይ መኮንን፣ 2ኛ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው ኢያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ 3ኛ በኮሚሽን ሥራ ላይ የተሰማራው በረከት ሙላቱ ጃፋር፣ 4ኛ አለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና 5ኛ የኒሞና ንግድ ሥራ ኃላ.የተ.የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ ናቸው።
ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ችሎት የቀረቡ ሲሆን÷ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ዛሬም ችሎት አልቀረቡም።
ችሎቱ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት እና ዘግይተው የዋስትና ጥያቄ ባቀረቡት 3ኛ ተከሳሽ ዋስትና ላይ ብይን ለመስጠት በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ተሰይሞ ብይን ሰጥቷል።
በዚህም ተከሳሾቹ ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ነጥቦችን መርምሮ ወደፊት በማስረጃ እንደሚጣራ ገልጾ መቃወሚያቸውን አለመቀበሉን አብራርቷል።
ከሌሎች ተከሳሾች ተነጥለው ዘግይተው የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡት 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት የተከሰሱበት ድንጋጌ ዋስትና በሚያስከለክል ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ድንጋጌ መከሰሳቸውን ጠቅሶ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል።
ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውንና አለመፈጸማቸውን የማረጋገጫ ጥያቄ በፍርድ ቤት የተጠየቁ ሲሆን ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እንዲሰሙለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ፍርድ ቤቱ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለሰኔ 26 እና 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት ፖሊስ 4ኛ ተከሳሽ ይኖሩበታል የተባለው ቦታ የፀጥታ ችግር እንዳለ ጠቅሶ፤ 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በአድራሻቸው አለመገኘታቸውን ገልጾ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው በጽሑፍ ጠይቋል።
የተከሳሽ ጠበቆችም በ4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ምክንያት ጉዳያቸው እንዳይጓተትባቸው ስጋታቸውን ጠቅሰው አስተያየት ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱም ፖሊስ 4ኛ ተከሳሽ ያሉበት ቦታ የፀጥታ ችግር ስለመኖሩ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ያዘዘ ሲሆን፤ 5ኛ ተከሳሽን የወረዳው ነዋሪ መሆናቸው ወይም አለመሆናቸውን ከወረዳው ማረጋጋጫ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡