በጎጃም የፋኖ ቃለ አቀባይ ማርሸት በአራቱም አቅጣጫ፣ 360 ዲግሪ ባህር ዳርን ከበወ እንደሚገኙና አስፈጊ ሲሆን ከተማዋን መቆጣጠር እጅግ ቀላል እንደሆነ ተናገሩ። በጥናት ላይ የተመሰረተ ጥቃት እነደሚሰነዘርም አመልክተዋል። የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና በበልኩላቸው ፋኖ ልክ እንደ ኦነግ ሸኔ ሁሉ መዋጋት ወደማይችልበት ደረጃ መድረሱን፣ ሁሉም በየፊናው የራሱን ቡድን ይዞ እርስ በርስ ሲጋደል የሚውል ቡድን እንደሆነ ከመከታ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
በተለያዩ የዩቲዩብ አውዶች የማርጨትን ድምጽ በማሰማት የተሰራጨው ዜና እንደሚያመልክተው አሁን ላይ ፋኖ የመንግስትን ጦር አሰፋፈር፣ ቁመና፣ ስርጭትና አከርካሬውን እየመረመረ ነው። በዚህም ጥናት መሰረት የመለካላከያ ሰራዊቱን አከርካሬ የማድቀቅ ስራ ይከተላል።
የፋኖ ታጣቂዎች 360 ዲግሪ ባህር ዳርን በሰባት ኪሎሜትር ርቀት ከበው እንደሚገኙ ያስታወቁት ማርሸት መቼ ባህር ዳርን ለመቆጣጠር እንድታሰበ አላስታወቁም። ወታደራዊ መረጃ ዝም ተብሎ እንደማይሰጥ ግን አመክተዋል። በሰባት ኪሎሜትር ርቀት ባህር ዳርን ከቦ ያለው የፋኖ ሰራዊት ግን በየትኛውም ጊዜ ያሰበውን ማድረግ እንደሚችል ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በሰላሳና አርባ ሰዎች ባህር ዳርን መቆጣጠራቸውን ያመለከቱት ቃል አቀባዩ አሁን ላይ ባህር ዳርን ለመቆጣጠር ከተፍለገ ምንም ዓይነት አዳጋች ሁኔታ እንደሌለ ሲገልጹ ” ህዝብ እንዳይጎዳና ከተማ እንዳይወድም ብለን ነው” የሚል ምክንያትም ሰጥተዋል።
የክልሉ መንግስት የባህር ዳር ከተማን የኮሪዶር መንገድ ግንባታና የከተማዋን ውበት ለማሻሻል ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን፣ የጸጥታው ሁኔታ ከቀድሞ የተሻለና ክልሉን በራስ ሃይል ለመጠበቅ የልዩ ሃይልና የሚሊሻ አደረጃጀቱ ውጤታም ስራ እየሰራ መሆኑን እያስታወቀ ይገኛል። ከዚሁም ጎን ለጎን የሰላም ጥሪና የህዝብ ለህዝብ ውይይት እያደረገ መሆኑን እየገለጸ ነው።
በቅርቡ እስከንድር ነጋ ሁሉም ጦርነት መጨረሻ ላይ የሚቋጨው በስለም ድርድር መሆኑን ጠቁሞ ፋኖ የድርድር ውሳኔ ለማሳለፍ ይችል ዘንድ አስቀድሞ አንድ ለመሆን እየየሰራ መሆኑን አስታውቆ ለቢቢሲ አፍሪካ መናገሩ ይታወሳል።
ቃለ አቀባዩ ስለ ሰላም ስምምነትም ይሁን ሌሎች አማራጮች ያሉት ነገር የለም። በጎንደር በርካታ ታጣቂዎች በሰላም እጃቸውን እየሰጡ መገባታቸው፣ በሰሜን ሸዋ የርስ በርስ ግጭቱ መቋጫ ማጣቱ፣ በውጭ አገር ያሉት የፋኖ ደጋፊና አስተባባሪ የሚባሉ ወገኖች መካከል የተፈጠረው አለመስማማት፣ ይህንኑ ተከትሎ እየወጡ ያሉ የድምጽና የቪዲዮ መረጃዎች ደጋፊዎችን ግራ ያገአቡ ሆነዋል።
በኤርትራ መንግስት እንደሚደገፍ የሚነገርለት የመረጃ ቲቪ ላይ ነጭ ነጯን የሚለው ዘመድኩን (ዘመዴ) በተከታታይ የፋኖ አመራሮችን ስም እየጠራ አብሮ ሲሰራ በነበረበት ወቅት የሚያውቀውን ሚስጢር በተከታታይ ይፋ ማድረግ መጀመሩ ይታወሳል።
ፋኖ ባህር ዳርን የመቆጣጠር አቅምና እንዳለው፣ በህር ዳርን ለመቆጣጠር በሰባት ኪሎሜትር 360 ዲግሪ መክበበኡን ቢገልጽም፣ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በየሶስት ወሩ እየታተመ ለንባብ የሚበቃው መከታ መፅሄት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ከጄኔራል ጌታቸው ጉዲና “ፋኖ ልክ እንደ ሸኔ ሁሉ ተሽመድምዷል” ሲሉ አሁናዊ ቁመናውን ገልጸዋል።
“በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሰው ፅንፈኛ ሃይል” የሚሉት የፋኖን አጠቃላይ ቁመና አስመልክቶ ጀኔራሉ የሠጡትን ሃሳብ ሙሉ ቃል ዜናውን ለማመጣጠን ከስር እንዳለ ከመከላከያ ገጽ ላይ እንዳለ አትመነዋል።

“ፅንፈኛ ሀይሉን በሚመለከት እንደሚታወቀው ፍላጎቱ በጣም ሠፊ ነው። የክልሉን አጠቃላይ ቁመና በማፍረስ ክልሉን ከተቆጣጠረ በኋላ አራት ኪሎ ሮጦ የመግባት ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ሲናገርና ሲፎክር የነበረ ሀይል ነው። አንዳንዱ የቅዠት ወሬ ስለነበር እንደ ሁኔታ ወስዶ ማንሳት አስፈላጊ ባይሆንም እንደ አጠቃላይ ግን ፍላጎታቸው ምንድነው? ስንል በሐይል፣ ህግን በጣሰ መንገድ ያለውን መንግስት በመገርሰስ ስልጣን የመቆጣጠር ነው።
ስልጣን ሲቆጣጠሩ ደግሞ ሌላውን ዝቅ በሚያደርግ መልኩ ዕቅድ አውጥተው፣ ልክ ሠራዊታችን የሠሜኑን ጦርነት ጨርሶ የተወሰነ ጊዜ እንኳን ሳያገግም ነው ጥቃት የፈፀሙት። ይህ የጠላት ሀይል ፍላጎቱ /ዕቅዱ/ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ዝግጅቱ ስርዓተ-መንግስቱን አፍርሶ በሃይል ስልጣን መያዝ፤ ስልጣን ከያዘ በኋላ ደግሞ የራሱን የበላይነት አስፍኖና ሌሎቹን የበታች አድርጎ የሚገዛበትን ስርዓት መዘርጋት ነው።
በነገራችን ላይ እንደ ተራ ነገር መታየት ያለበት አይደለም። የሠፊ ጊዜ ዝግጅት ይዘው፣ህቡዕና ግልፅ አደረጃጀት ፈጥረው ነው ወደ ውጊያ የገቡት። የዚህኛው በወታደራዊ መልክ ብቻ የሚገለፅ አይደለም ዝግጅቱ። ከውስጥም የማፍረስና አጠቃላይ መተማመን እንዳይኖር በማድረግ ፍላጎታቸውን ዕውን ለማድረግ ነው የተንቀሳቀሱት። በዚህም የቻሉትን ሁሉ ርብርብ አድርገዋል። ይሄ ብዙም አልቆየም። ፍላጎታቸው በአጭር ጊዜ ነው የመከነው።
የመጀመሪያ ውድቀታቸው ከአቅማቸው በላይ ዕቅድ ማውጣታቸውና መፎከራቸው፤ ሠራዊቱንና ሕዝቡን ለማንቋሸሽና ለማሳነስ መሞከራቸው ነው።
ሠራዊታችን ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ በአጭር ጊዜ ፍላጎታቸው እንዲመክን አድርጓል። ጉራውና ፉከራው ካልሆነ በቀር የደረሠባቸው ምት ቀላል አይደለም። እናም ይዘውት የተነሱት ዓላማ ከሽፏል።
ሁለተኛው በውስጣቸው ከፍተኛ ክፍፍል ተፈጥሯል። ተከፋፍሎ እርስበርሱ እየተጨቃጨቀ የሚውል ቡድን ነው። በነገራችን ላይ ዓላማቸው ቅንነት የጎደለው፣ዕኩይ ፍላጎትን በኃይል ሌላው ላይ ለመጫን ያለመ በመሆኑ ነው ያልሠመረው። የያዙት ዓላማ አንድ እንዲሆኑ አያደርጋቸውም። እርስበርሳቸውም በመንደርና በአካባቢ በመከፋፈል የመጫረስ ስሜት ያመጣው ይሄ ነው።
እነዚህ ፅንፈኞች ዓላማ የላቸውም፤ የህዝብን ጥያቄ እንደ ሰበብ አድርገው ቢያቀርቡም ህግና ስርዓትን በተከተለ መንገድ አይደለም። የሆነው ሆኖ ካደረጉት ሰፊ ዝግጅት አንፃር በአጭር ጊዜ ነው የመከነው።
ሁለተኛ አሁን በየአካባቢው የየራሳቸውን ቡድን ይዘው በተለያዩ ስፍራዎች አደጋ የማድረስ ሁኔታ አለ። ቢሆንም በከፍተኛ ደረጃ ነው የተሽመደመዱት” ብለዋል ጄነራል ጌታቸው።
በዚህ ስራ ሂደት ላይ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ውጤታማ ነው። የህዝቡና የመስተዳድር መዋቅሩ ቅንጅት ደግሞ አሁን የጠላት ተዋጊዎች ለደረሱበት መፈረካከስ ዳርጓቸዋል፤ አሁን ሀይላቸው በከፍተኛ ደረጃ ደቋል። አደረጃጀቱን አስመልክተው በየቦታው የሚያወሩት ይሄ ምስራቅ አማራ ፋኖ ዕዝ፣ የሸዋ ዕዝ፣ የጎጃም ፋኖ ዕዝ እና የጎንደር ፋኖ ዕዝ የሚሉት አደረጃጀት በመሬት ላይ የሌለ ነው።
ከመጀመሪያውም እንደዚህ ዓይነት አደረጃጀት አልነበራቸውም። ዕዝ ይቅርና ክፍለ ጦርና ብርጌድም በዚያ ደረጃ የሚገለፅ አይደለም። ይሄ ይታወቃል። በየአካባቢው ግን በአነስተኛ ቁጥር ተደራጅተው ይንቀሳቀሳሉ። ለምሳሌ ጎጃም ላይ የሚንቀሳቀሠው በእነ ዘመነ የሚመራው ሀይል አለ። ሆኖም ዓላማውን ሊያሳካ የሚያስችል ቁመና ያለው አይደለም። ከሸኔ ጋር አያይዤ እንደገለፅኩት ፅንፈኛው ሃይልም የተፈረካከሰበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው።
በፕሮፓጋንዳ ህዝቡ በስሜት እንዲነሳሳ በማድረግ አንድ አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮችን የአማራ ህዝብ በሌላው ማህበረሠብ እየተጠቃ እንደሆነ አስመስሎ በመቀስቀስ በዚህ ደግሞ ስሜት በመጎርጎር አርሶ አደሩንና ወጣቱን ለማደናገር ብዙ ሰርተዋል። በዚህ ላይ የሚዲያ ዘመቻው በጣም ሠፊ ነው። ከፍተኛ ንቅናቄ ለመፍጠር ሞክረው ነበር። በሂደት ህብረተሠቡ ይሄን እየተገነዘበ ከእንደዚህ ዓይነቱ ጥፋት ልጆቹ እንዲመለሱና የሀገሩን፣ የአካባቢውን ደህንነት እንዲጠብቅና ወደ ሠላምና የልማት እንቅስቃሴ እንዲገባ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል።
የመስተዳድሩ መዋቅር የህዝቡ ጠላት የሆነው ኃይል ከሚከተለው ስልትና እስትራተጂ አንፃር አደገኛነቱን ተረድቶ ምላሽ የሚሠጥበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ሰራዊታችን በተለያዩ ጊዜያቶችና አካባቢዎች ባካሄደው ኦፕሬሽን ይህ ሀይል የተመታው ተመትቶ፣ የተደመሠሠው ተደምስሶ በጣም በርካታ ኃይል በቁጥጥር ስር ውሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው ዕጅ የሠጡትና ወደ ሠላም የተመለሡት፤ በምህረት የገቡት፤ በየጊዜው እንደ ቡድን ነው ዕጅ የሚሰጡት፤ ዝም ብሎ እጅ መስጠት ብቻ አይደለም። መልሶ ሠልጥኖ ፅንፈኛውን ለመዋጋት ዝግጁነቱን እየገለፀ ነው። ይሄ በጎንደር በስፋት ታይቷል። በወሎም በተመሳሳይ። ዕጅ ሠጥተው ከገቡም በኋላ ተመልሠው ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ፀጥታና ደህንነት የመጠበቅና ይሄን የጥፋት ሀይል የመፋለም እንቅስቃሴ ላይ የመሠማራት ተነሳሽነት ታይቷል።
ስለሆነም ትርጉም ሊያመጣ የሚችል ምንም ዓይነት የፅንፈኛው እንቅስቃሴ የለም። ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በድምሩ ሲታይ አካባቢው የተረጋጋ ሆኗል።
ከተሞች አካባቢ ያደርገው የነበረውን እንቅስቃሴ በሙሉ አቁሞ አሁን በየጫካው እየተሹለከለከ የሚያጣጥርበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው። አሁንም ግን ሙሉ አደረጃጀታቸው ያልፈረሰ ጥቂት ቡድኖች አሉ። አመራሮቻቸው ይታወቃሉ። የቡድኑ ሀይልም ማለትም የሠው ብዛቱ ይታወቃል።
ከጠላት አንፃር አጠቃላይ አላማቸው ተፈረካክሷል። ሸኔም ሆነ ፅንፈኛው በስነ-ልቦናም፣በውስጣዊ ትስስሩም፣በሠው ኃይሉም፣በወታደራዊ አቅሙም እስካሁን እየተሠሩ ባሉ ስራዎች እየተሽመደመዱና ትርጉም ወደሌለው ደረጃ እየወረዱ ነው። ይህን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲሉ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት