በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ማለት በሚቻል ደረጃ አግቶ ገንዘብ መጠየቅ ስራ ሆኗል። መግደልም ተለምዷል። ይህ ዝርፊያ ላይ የተመረኮዘ አካሄድ ልማድ እየሆነ የበርካቶችን ደጅ አንኳኩቷል። በትግራይ ታፍና የነበረችው ማህሌት ሶስት ወር ድምጿ ተፍቶ ከቆየች በሁዋላ ሶስት ሚልዮን ተጠይቀው የነበሩት ቤተሰቦቿ ዱብዳ ሰምተዋል። በእንዲህ ዓይነት ተግባር የሚሳተፉ አስቸኳይ የሞት ቅጣት እንደሚገባቸው የተቆጡ እየገለጹ ነው
መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም በዓድዋ ከተማ ” ዓዲ ማሕለኻ ” ከሚባል ስፍራ ነው ታግታ የተሰወረችው። የታገተችውም ቋንቋ ወደ ምትማርበት ትምህርት ቤት እየሄደች ሳለ ነበር። ያገቷትም ባጃጅ ይዘው የመጡ ሰዎች ነበሩ።
ማህሌት ተኽላይ ታግታ ከተወሰደች በኃላ አጋቾች ለማስለቀቂያ 3 ሚሊዮን ብር እንደጠየቁ ወላጅ አባቷ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው። የዓድዋ ከተማ ፓሊስም ከሳምንታት በኃላ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ ገልጾ ነበር።
አባት ተኽላይና መላ ቤተሰብ ላለፉት ሶስት ወራት እረፍት አጥተው ነበር ያሳለፉት። ቁርጡን ያላወቀ የወላጅ አንጀት ከዛሬ ነገ በተስፋ ሶስት ወር ቢያሳልፉም መጨረሻ ላይ ልጃቸው ማህሌት በአፋኞቹ ተገድላ መቀበሯ ገዳዮቹ አመኑ።
አቶ ተኽላይ ግርማይ እና መላው ቤተሰቦች ከዛሬ ነገ የልጃቸውን በህይወት ቤት መምጣት ሲጠብቁ ከርመው ልጃቸው በህይወት እንደሌለች መርዶ ተነግሯቸው።
“ለ91 ቀናት ታግታ የተሰወረችው ተማሪ ማህሌት ተኽላይ ተገድላ ተገኝታለች” የሚለው ዜና ይፋ ሲሆን፣ “ግድያውን ምን አመጣው?” በሚል ዜናውን የሰሙ በሃዘኔታ ድምጻቸውን አሰሙ።
ከ3 ወር በላይ ታግታ አድራሻዋ ጠፍቶ ዛሬ በግፍ መገደለዋ የተረጋገጠው ተማሪ ማህሌት ተኽላይ አጋቾችዋ ገድለው እንደቀበሯት ማመናቸውን ፓሊስ ይፋ አድርጓል። ፖሊስ ለምን እንደገደሉና በስውር ሊቀብሯት እንደፈለጉ የገለጸው ነገር የለም።
የትግራይ ማእከላይ ዞን ፓሊስ የወንጀል ምርመራ ሃላፊ ኮማንደር ፀጋይ ኣስፍሃ ዛሬ ለ104.4 የመቐለ ኤፍኤም በስልክ በሰጡት ቃል ፣ በእገታው እና ግድያው የተጠረጠሩ መያዛቸውን አስታውሰው፣ ግለሰቦቹ ለፓሊስ በሰጡት ቃል ተማሪ ማህሌትን ገድለው በዓድዋ የፓንአፍሪካ ዩኒቨርስቲ ሊገነባበት የመሰረተ ደንጋይ የተጣለበት ቦታ መቅበራቸውን ቦታው ድረስ በመምራት ማሳየታቸውንና ድርጊቱን መፈጸማቸውን እንዳመኑ ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ማህሌትን እንዴት እንዳገቷት ፣ አግተው ወዴት እንደወሰዱዋት ፣ እንዴት ገድለው እንደቀበርዋትና አስከሬንዋ የተቀበረበት ቦታ ጭምር በዝርዝር ለፓሊስ ማሰየታቸውን ቲክቫህ የጠቀሳቸው ኮማንደር አረጋግጠዋል።
የተማሪ ማህሌት ተኽላይ አስከሬን ከተቀበረበት ጉድጓድ የማውጣት ስነ-ሰርዓት በመከናወን ላይ መሆኑ የገለፁት ኮማንደር ፀጋይ ፤ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደረግ አመልክተዋል።
በመጨረሻ ከትክቫህ ለመረዳት እንደታቻለው የተማሪ ማህሌት ተኽላይ ስርዓተ ቀብር ተፈጽሟል። የማህሌት አስክሬን አጋቾች ከቀበሩበት ስውር ቦታ ወጥቶ የአስከሬን ምርመራ ተጠናቅቆ በተመሳሳይ ቀን ከቀኑ 9:00 ሰዓት በዓድዋ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስትያን የቀብር ስነ-ሰርዓት ተፈጽሟል።
የቀብር ስነ-ስርዓቱ የክልል ፣ የዞን እና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በርካታ የዓድዋ ነዋሪዎች ተገኝተው ነበር። የቀብር ስነስርዓቱን የሚያሳዩ ምስሎች እንዳመለከቱት ከሆነ አስከሬኑ የትግራይን ባንዲራ በሰልፍ በያዙ ወጣቶች ታጅቦ ታይቷል።
የአስከሬኑን መገኘት ያስታወቀው ፖሊስ፣ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው አጋቾች ለምን እንደገደሏት፣ ገድለውም ለምን በድብቅ እንደቀበሯት ተጠርጣሪዎቹን ጠቅሶ ያለው ነገር የለም። በትግራይ በተመሳሳይ የታገቱና ህይወታቸው ያለፈ ወጣቶችን ፎቶ በማሰራጨት በርካቶች ወንጀሉን በሰብአዊነት ኮንነዋል።
ዜናውን ከሰሙ መካከል የቀድሞ ሟቾችንና ታጋቾችን ፎቶ በማያያዝ በእንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል የሚሰማሩ አፋታኝ የአደባባይ ሞት ፍርድ ሊፈርድባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል። በአብዛኛው ለአሰቃቂ ወንጀል ፈጻሚዎች የሚሰጠው ያልተመጣጠነ ቅጣት እንደሆነ የሚናገሩ ለሌሎች መቀጣጫ የሚሆን ከባድ ቅጣት ሊጣል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የትግራይ ማዕከላይ ዞን ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ፀጋይ ኣስፍሃ ፥ አጋቾቹ የጠየቁትን ብር ቤተሰቦቿ አቅም ስለሌላቸው መክፈል ባለመቻላቸው ማህሌትን ገድለው እንደቀበሯት ገልጸዋል።