በአመሐ ኃይለ ማርያም
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ‹‹ለውጭ ተቋማት ክፍት የተደረገው የፋይናንስ ዘርፍና የኢትዮጵያ ባንኮች ሥጋት›› በሚል ርዕስ ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በሪፖርተር ዕትም በቀረበ ዜና ላይ አስተያየት መስጠት ነው፡፡
‹‹የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች እንዲከፈት መንግሥት ውሳኔ ያሳለፈና ለተግባራዊነቱም እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ አሁንም የውጭ ኩባንያዎች በዚህ ዘርፍ መግባታቸው ቢዘገይ መልካም ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡
‹‹ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ላይ ይኸው ሐሳብ የተንፀባረቀ ሲሆን፣ መንግሥት ግን ውሳኔውን እንዳፀና መሆኑ ታውቋል፡፡ በውጭ ባንኮች መግባት ዙሪያ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ላይ ተቃውሞ ባይኖራቸውም፣ የሚገቡበት ጊዜ ቢራዘም የተሻለ ይሆናል በማለት ሐሳባቸውን በዚሁ ጉባዔ ላይ ሲያንፀባርቁ ተሰምቷል፤›› በፋይናንስ ተቋማት መሪዎች የቀረቡ ሐሳቦች ምክንያቶች ለማለት አያስደፍርም፡፡
‹‹የአገሪቱ ባንኮች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ በተለይ የካፒታል አቅማቸው ዝቅተኛ መሆኑን፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ምናልባት የምንዛሪ ለውጥ ቢደረግ ደግሞ፣ የእነዚህ ባንኮች ካፒታል ከዶላር አንፃር ካፒታላቸው ይመዘን ቢባል የበለጠ የካፒታል አቅማቸው የሚያዘቀዝቅ በመሆኑና የውጭ ባንኮች አሁን ባለው ሁኔታ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ደንበኞችን ብሎም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና መሰል ተቋማትን ትኩረት ሊያደርጉባቸው እንደሚችሉ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ገበያው ሲገቡ አሁን ያሉ ብቁ የሚባሉ ሠራተኞች ወደ እነዚህ ባንኮች ሊፈልሱ እንደሚችሉ በመጥቀስ፣ ይህንም ጉዳይ የሚያሳስብ እንደሆነ አስረድተዋል፤››፡፡
የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ
በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ የውጭ ኢንቨስትመንት የተለመደና በሁሉም ዘርፎች ያለ ምንም ገደብ በስፋት የተሠራጨ ነበር፡፡ የጣሊያን፣ የግሪክ፣ የህንድ፣ የየመንና የአርመን ወዘተ የውጭ አገር ዜጎች፣ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚና ማኅበረሰቡ አካል ነበሩ፡፡ የእነዚህን በአንድ ወቅት ክፍትና ንቁ የነበሩ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ቅሪቶች፣ ዛሬም ድረስ በራሳቸው በመሠረቷቸው አያሌ የማኅበረሰብ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶችና ምግብ ቤቶች አማካይነት ማየት እንችላለን፡፡ የግሪክ ትምህርት ቤት፣ የህንድ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ ጁቬንቱስ ክለብ፣ ግሪክ ክለብና የጣሊያን የባህል ማዕከል ከአያሌዎቹ ውስጥ ጥቂት አብነቶች ናቸው፡፡
በ1930ዎቹ ኢትዮጵያ በአኅጉሪቱ መቶ በመቶ በአፍሪካውያን ባለቤትነት የተያዘ የመጀመሪያው ባንክ ባለቤት ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ በአኅጉሪቱ የአክሲዮን ገበያ ያላት ሁለተኛዋ አገር ነበረች፣ ከግብፅ በመቀጠል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የውጭ ባንኮችና 16 የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ኢኮኖሚው ክፍት በመሆኑ ከውጭ ካፒታል፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በእጅጉ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ የኢኮኖሚውንና የኅብረተሰቡን የዝመናና የለውጥ ሒደትና በፊታውራሪነት የሚመራው የግል ዘርፉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች ይልቅ ወደ ውጭ ገበያ የምትልከው ይበልጥ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ በቋሚ ተመን በቀላሉ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአንድ ሺሕ ዶላር በላይ ስለነበር፣ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ያላት አገር አድርጓታል፡፡ ኢኮኖሚው ንቁና አዳዲስ አሠራሮችን የሚከተል ሆኖ ሚዛናዊ የመዋቅር ትራንስፎርሜሽን ሒደት ላይ ነበር፡፡
መንግሥት ለአገራዊ ባንኮች ከለላ የሚያደርገው ለምንድነው?
ለአገራዊ ባንኮች ከለላ ማድረግ ስንል በትክክል እየተናገርን ያለነው ስለማነው? ስለአክሲዮን ባለቤቶች? ስለደንበኞች? ወይስ ስለኢኮኖሚው? ጉዳዩ በእርግጠኝነት ደንበኞችን የሚመለከት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በአፍሪካ እጅግ ወደኋላ ከቀሩት አንዱ ነው፡፡ ፉክክር ወይም አዲስ አሠራር የሌለውና የተዘጋ ገበያ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ፣ ለኢኮኖሚው ትልቅ ማነቆ ነው፡፡ የብዙኃኑ ሸማች ገበያ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ውስን የብድር አቅርቦት ነው ያላቸው፡፡ የግል ባንኮች ባለ አክሲዮኖች (በግምት 520 ሺሕ ገደማ የሚደርሱ) እና ሁለቱ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የፖሊሲ ባንኮች ብቻ ናቸው ከውጭ ባንኮች መገለል የሚጠቀሙት፡፡
የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በሚከተሉት ባህሪያት ይገለጻል
ኢትዮጵያ በባንክ ኢንዱስትሪ በራቸውን ለውጭ ኢንቨስትመንት ዝግ ካደረጉ የመጨረሻዎቹ የዓለም አገሮች አንዷ ናት፡፡ በዚህ ረገድ ኤርትራና ሰሜን ኮሪያን ከመሳሰሉ አገሮች ተርታ እንመደባለን፡፡ ኢኮኖሚው በዚህ ከልካይና ዘመን ያለፈበት ፖሊሲ ሳቢያ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡
የዕድገት መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩ የአምራች ወይም ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂን የመሳሰሉ ዘርፎች፣ የፋይናንስ አቅርቦት የመሳብ ዕድላቸው እምብዛም ነው፡፡ ካፒታል ለማግኘት የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ ፋይዳ ያለው ምርታማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ለሆነው ምርምር፣ ልማትና ፈጠራ የሚኖረውን የፋይናንስ አቅርቦት ይበልጥ ይገድቡታል፡፡
የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ ባንኮች 90 በመቶ የሚሆነውን ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል የባንክ ፍላጎት ለማሟላት ምንም ጥረት ሳያደርጉ መቅረታቸው ነው፡፡ ብዙኃኑን ወይም ደሃውን ታሳቢ ያደረጉ የፋይናንስ ውጤቶች ወይም አገልግሎቶች የሉም፡፡ በኢትዮጵያ ሀብታሙ የኅብረተሰብ ክፍል በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መበደር ይችላል፡፡ ለሸማቹ የአንድ ሺሕ ብር ብድር ግን የለም፡፡
ለባንክ ዘርፉ ልማት፣ እንዲሁም ለግል ዘርፉና በጥቅሉም ለኅብረተሰቡ ዕድገት የሚመጥኑ የፋይናንስ አገልግሎቶች ለማቅረብ ትልቁ ማነቆ አዲስ የአመራር ክህሎት አለመኖር ነው፡፡ አዳዲስ የአመራር ክህሎቶችና ሐሳቦች ዕጦትም ዘርፉ እንዳይሻሻል ገድቦታል፡፡ ሲጠቃለል የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በሚከተሉት ባህሪያት ይገለጻል፡፡
የባንክ አገልግሎት የማያገኝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ፣ የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከፍተኛ ዋጋ ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች፣ አዳዲስ አሠራር የሌለው፣ ፉክክርና ውድድር የሌለበት፣ ሙስና በብድርና በውጭ ምንዛሪ አገልግሎት፣ የተሳሳተ የአገራዊ ሀብት ምደባ፣ ደካማና ራዕይ የሌለው አመራርና እጅ በእጅ (በካሽ) ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚና ደካማ የኤሌክትሮኒክ የአከፋፈል ሥርዓት፡፡
የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግ አስፈላጊነት
የፋይናንስ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ አንጎል፣ ልብና የደም ሥር የመሆኑን ያህል የፋይናንስ መሠረተ ልማት ዕጦት (አልያም ቁጠባን በመሳብ የሚያስተናብርና ኢንቨስትመንትን የሚመግብ ሌላ አማራጭ መንገድ ማጣት) ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያጨልም ክፉ አደጋ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ተገቢ የካፒታል አቅርቦት ያለመኖር፣ የትርፋማ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት ዕድገትን እየገደበ ነው፡፡ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች በአገር ውስጥና በውጭ ገበያዎች፣ ትርፋማና ውጤታማ የመሆን አቅም ባላቸው የቢዝነስ ዕድሎች ላይ ደፍረው ኢንቨስት እንዳያደርጉ እያገዳቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ባንኮች ፕሮጀክት ተኮር ለሆነ ኢንቨስትመንት የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ ክህሎት የላቸውም፡፡ ስለዚህም ብድር ድርጅቶች በሚያቀርቡት የማስያዣ (ኮላተራል) ወይም የዋስትና መጠን የተገደበ ነው፡፡ ወይም እምብዛም ፍሬያማ ላልሆኑ ኢንቨስትመንቶች ይፈሳል፡፡ ለምሳሌ ባንኮች እንደ ማስያዣ (ኮላተራል) የሚቆጥሯቸው የሪል ስቴት ልማቶች ናቸው፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ባንኮች ፉክክርን በማሳደግ የላቀ ክህሎትና የሙያ ተደራሽነትን በማጎልበት፣ የተሻለ የካፒታል ተደራሽነትን በመፍጠርና ኢኮኖሚውን በማስፋት የአስተናጋጅ አገሮችን የባንክ ዘርፍ ይጠቅማሉ፡፡ ይበልጥ በስፋት ሲታይ፣ የአስተዳደር መዋቅሮችን በማሻሻል በጎ ተፅዕኖ ሊፈጥሩም ይችላሉ፡፡
ያላደገ የባንክ ዘርፍ በሚገኝበት የኢትዮጵያ ዓውድ ውስጥ የበለጠ ክህሎት ያላቸው፣ በተሻለ መንገድ የተመሩና የተሻለ የገንዘብ አቅም ያላቸው ተፎካካሪዎች መምጣት ትርጉም ያለው በጎ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ባንኮች ከአገራቸው የተለየ ሙያዊ ክህሎትን በማምጣት የፋይናንስ አካታችነትን ያስፋፋሉ፡፡ ቀድሞ የባንክ አገልግሎት ያላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ ከቻሉ፡፡
በባንኮች መካከል ጠንካራ ፉክክር ሲኖር ለብድር አገልግሎቶች የሚከፈለውን የወለድ መጠን በእጅጉ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ብድር የሚሰጡ ባንኮች ሲበራከቱ የአገር ውስጥና የውጭ ተበዳሪዎች የአነስተኛ ወይም ትልቅ ቢዝነስ የብድር አገልግሎት በማራኪ የወለድ መጠንና ውል ለማግኘት ይችላሉ፡፡
ለንፅፅር የአፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪ ዓይነተ ብዙ ገጽታዎች
የአፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪ በዓይነተ ብዙ ገጽታዎቹ የሚታወቅ ነው፡፡ በስፋት በመሠረተ ልማት፣ በባንክ አገልግሎት ሥርጭትና በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የጎላ ልዩነት ያላቸው ብሔራዊ ገበያዎች ያሉት ነው፡፡ በአፍሪካ የባንክ ገበያዎች ውስጥ አራት ዓይነተኛ ዘርፎች አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በባንክ አገልግሎት ሥርጭት፣ በገቢ ዕድገት፣ በትርፋማነትና በፋይናንስ መሠረተ ልማት ጉልህ ልዩነት የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡
የመጀመሪያው በአንፃራዊነት የዳበረ ገበያ ሲሆን፣ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢና የሀብት ሥርጭት ያላቸውን ግብፅና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ አገሮችን የሚያካትት ነው፡፡ እነዚህ ገበያዎች ከፍተኛ የቅርንጫፍ ሥርጭት አላቸው፡፡ ለመቶ ሺሕ ሰዎች 17 ቅርንጫፎች ሲሆንኑ በአንፃሩ የአፍሪካውያን አማካይ አምስት ቅርንጫፎች ናቸው፣ ለመቶ ሺሕ ሰዎች፡፡ በተጨማሪም 22 በመቶ ያህሉን አዋቂዎች የሚሸፍን ከፍተኛ የብድር አገልግሎት ሥርጭት አላቸው፡፡ ይህም ከአፍሪካውያን አማካይ እጥፍ ነው፡፡ በእነዚህ ገበያዎች ‹ሪቴይል› ባንኪንግ ከፍተኛውን የገቢ ድርሻ የሚወስድ ሲሆን፣ ይበልጥ የዘመኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችም ተስፋፍተዋል፡፡ ለምሳሌ የሀብት አስተዳደርና የሞርጌጅ ብድሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሁለተኛው በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኘው የሽግግር ገበያ ሆኖ ጋና፣ ኮትዲቯርና ኬንያን የመሳሰሉ አገሮችን ያካትታል፡፡ በእነዚህ አገሮች የባንክ አገልግሎት ሥርጭቱ ከተለመደው ልቆ የተሻገረ ነው፡፡ እነዚህ ያደጉና የተወዳዳሪነት አቅም ያላቸው የሪቴይል ባንኪንግ ገበያዎች ሲሆኑ፣ በከፍተኛ ደረጃ የሞባይል ባንኪንግና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡
ሦስተኛው ዓይነተኛ ገበያ አንጎላንና ናይጄሪያን የመሳሰሉ የሚያንቀላፉ ግዙፍ አገሮችን የሚያካትት ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ሰፊ ገበያዎች ያሏቸው ሲሆኑ፣ የባንክ አገልግሎት ሥርጭት ከገቢ ደረጃቸው አንፃር ዝቅተኛ ነው፡፡ እነዚህ የሚያንቀላፉ ግዙፍ አገሮች ደግሞ ነዳጅ በመላክ የሚታወቁ ናቸው፡፡ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የነዳጅ ዘይት ጉልህ ቦታ ሲኖረው፣ ብዙውን ጊዜ ባንኮች ለሌሎች ዘርፎች ወይም ለሸማች ገበያው ብድር ከመስጠት ያፈገፍጋሉ፡፡ በእነዚህ ገበያዎች የብድር አገልግሎት ሽፋን ሦስት በመቶ ብቻ መሆኑንም እናያለን፡፡ ይህም ከአራቱ ዓይነተኛ ገበያዎች ዝቅተኛው ሽፋን ነው፡፡ የሞባይል የገንዘብ ዝውውር በመሳሰሉ ዘርፎችም አዲስ አሠራር እምብዛም ነው፡፡
የመጨረሻው ዓይነተኛ ገበያ ገና ለጋ ገበያ ሲሆን፣ ዝቅተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢና የሀብት ሥርጭት ያላቸው ኢትዮጵያና ታንዛንያ የመሳሰሉ አገሮችን ያካትታል፡፡ ከመቶ ሚሊዮን በላይ በሆነው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛቷ ከፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷ ጋር ተዳምሮ፣ ኢትዮጵያን ለውጭ ባንኮች እጅግ ማራኪ ገበያ ያደርጋታል፡፡
ማጠቃለያ
የውጭ ኢንቨስትመንትን ከባንክ ዘርፉ በሚያገለው ፖሊሲ ሳቢያ ኢኮኖሚው ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡ ፉክክር፣ ቀልጣፋ አሠራር፣ ፈጠራና አካታችነት በከፍተኛ የኢኮኖሚ ዋጋ መስዋዕት እየተደረጉ ነው፡፡
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድን በተመለከተ እምብዛም ማቅማማት ሊኖር አይገባም፡፡ ዝግ የባንክ ዘርፍ ካላቸው የመጨረሻዎቹ የዓለም አገሮች ውስጥ አንዱ እኛ ነን፡፡ ትንሿ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን እንኳን በኢኮኖሚያቸው ውስጥ በውጤታማነት የሚንቀሳቀሱ የውጭ ባንኮች አሏቸው፡፡ እኛ፣ ኤርትራና ሰሜን ኮሪያ ትክክል ሆነን የቀረው ዓለም ተሳስቶ ይሆን? የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከመሠረታዊ የኢኮኖሚክስና የፋይናንስ ሳይንስና መርሆዎች ውጪ የሚሆንበት የተለየ ሁኔታ አለው እንዴ? የአገሪቱ ባንኮች በካፒታል አቅማቸው እስኪጠናከሩ ስንት ዓመት ይፈልጉ ይሆን? የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ከሞኝ ለቅሶ በመውጣት ለማይቀረው ፍልሚያ መዘጋጀት ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
ዋናውን ጽሁፍ ሪፖርተር ላይ ሊንኩን ተጭነው ያንብቡ ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡