በርካታ ሰዎች በአቋራጭ መንገድ ለመክበር ካላቸው መሻት የተነሳ አያሌ ወንጀሎችንና የሽብር ተግባራት ላይ በመሳተፍ ረብጣ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ይህንን ያገኙትን ገንዘብና ንብረት ወደፋይናንስ ሥርዓቱ ለማስገባት በርካታ ጥረቶችን ያደርጋሉ፡፡ በወንጀል የተገኘን ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እንቅስቃሴ በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምን ይሆን? ወንጀሉንስ ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው?
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ለገሠ እንደሚገልጹት፤ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሙስና፣ ኮንትሮባንድና ሌሎችም ምክንያቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ማነቆ እየሆኑ ነው። ከነዚህ በተጨማሪ ሌላኛውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ፈተና (መኒ ላውንደሪንግ) ነው። ይህ አሠራር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ በርካታ ጉዳቶችን ያደርሳል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፤ መንግሥት የዋጋ ንረትን በቀላሉ እንዳይቆጣጠርና በኢኮኖሚ ውስጥ ምን ያህል ብር እየተዘዋወረ እንደሚገኝ ለማወቅ አዳጋች እንደሚያደርገውም ይገልጻሉ።
የወንጀል እንቅስቃሴው በሚጨምርበት ወቅትም የገንዘብ አቅርቦት የመዋዠቅ ሁኔታዎች ይታዩበታል፤ እንዲሁም መንግሥት የገንዘብ አቅርቦትንና ዝውውርን የሚቆጣጠርበትን አቅም ከመፈታተን ባለፈ መሰብሰብ ያለበትን ግብር እንዳይሰበስብ ያደርገዋል ይላሉ። እንደ መምህር ሀብታሙ ገለጻ፤ የጉዳት መጠናቸውም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህም የፋይናንስ ተቋማትን መልካም ስም የሚያጠለሽና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በተዓማኒነት እንዳይሠራ ያደርገዋል። እንዲሁም የሀገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት በማዛባት የኢኮኖሚና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ይፈጥራል።
በዋናነት በዚህ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ተቋማት በሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መረጋጋት ላይ ትልቅ ሚና አላቸው። ግለሰቦቹ በዚህ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ አላስፈላጊ ቁሶችን ወደሀገር ውስጥ ለማስገባትና ዜጎችን ሊጎዱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ፈሰስ የሚያደርጉ ሲሆን ለአብነትም በሕገወጥ የጦር መሣሪያ ግዥ ላይ እንደሚውል መምህር ሀብታሙ ያስረዳሉ።
“በአሁን ወቅት ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያሰጓት ነገሮች ውስጥ አንዱ ሽብርተኝነት ነው። በእርግጥ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብና ንብረት የሽብር ወንጀል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በርካታ ወንጀሎችም መፈፀሚያ መሣሪያ ሲሆን እንደየሽብር ቡድኑ አደረጃጀት፣ ዓላማና ሁኔታ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ የሽብር ወንጀሎች የሚፈጸሙት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተገኘ ገንዘብና ንብረትን በመጠቀም ነው” ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ።
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ እንዳለ አሰፋ እንደሚናገሩት፤ አገልግሎቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ከማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ስጋቶች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ይቀበላል፣ ያከማቻል፣ ይመረምራል፣ ይተነትናል፣ ያሰራጫል። ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ የሕዝቡ ግንዛቤ እንዲዳብር ያደርጋል፣ በተጨማሪም የወንጀሉን መነሻ፣ የአፈጻፀም ስልት፣ ዓይነት፣ ባሕሪና አደጋ በማጥናት ለሚመለከታቸው አካላትም የመፍትሔ አቅጣጫ ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ የጉዳት መጠናቸው ከፍተኛ እንደሆነ የተለዩ ወንጀሎችና ለፋይናንስ ዘርፉ ተግዳሮት እየሆኑ ካሉት መካከል ሙስና፣ የታክስ ጥሰት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ፣ ጥቁር ገበያና ሌሎችም ናቸው። በዚህ መልኩ የተገኘውን ገንዘብ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በማሳለፍ ሕጋዊ ለማስመሰል በርካታ ጥረቶች እንደሚስተዋሉ አቶ እንዳለ ይጠቁማሉ።
እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ እነኝህ ወንጀሎች በዋናነት የሚፈጸሙበት ምክንያት በአቋራጭ መንገድ ከፍተኛ ሀብት ለማፍራት የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው። የሚፈጸሙትም በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ልምድ ባላቸው ግለሰቦች መሆኑ የወንጀል መከላከል ሥራውን ከባድ ያደርገዋል።
“የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎትም እነኝህን ወንጀሎች ለመከላከል የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ብሎ ከሰየማቸው ተቋማት ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል። ከባንኮች ሪፖርት በሚመጣበት ወቅት አገልግሎቱ ከሰበሰባቸው መረጃዎች ጋር በማመሳከር የማጣራት ተግባር ይከናወናል” የሚሉት አቶ እንዳለ፤ ወደተቋሙ የሚመጡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ምርመራዎች የሚያስፈልጉበት ሁኔታዎችም ሲኖሩ ለፖሊስ ተላልፎ ይሰጣል ነው ያሉት።
ሀገራትም ወንጀሉን ለመከላከል ያመቻቸው ዘንድ ከሕገ መንግሥታቸው ጋር በተገናኘ መልኩ ተፈፃሚ ሕጎችን ያወጣሉ። ኢትዮጵያም የሽብር ወንጀሎችንና ተዛማጅ የፋይናንስ ወንጀሎችን ይከላከልኛል ያለችውን ሕግ አውጥታ ተግባራዊ እያደረገች ነው። ይህም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 780/2005 ተብሎ ይታወቃል።
በአዋጁ መሠረትም ወንጀሉን በመፈፀም የተሳተፈ፣ ለመፈፀም ያደመ፣ የሞከረ፣ የረዳ፣ ያመቻቸ ወይም እንዲፈጸም ያማከረ እንደሆነ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ንብረቱ በዚህ አዋጅ መሠረት መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከብር 100 ሺህ በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው 32ኛ መደበኛ ስብሰባ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል የደህንነት ስጋት ከመሆኑ በተጨማሪ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጸኝነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የሚያደርግ በመሆኑ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።
ENA news