ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው የብፁዕ አቡነ ልቃስን የአውደምህረት ንግግር ከቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና አስተምህሮት ውጭ የሆነ ፣ ቅዱስ ሲኖዶስንም ሆነ ቤተክርስቲያንን የማይወክል ነው ሲል ውሳኔ አሳለፈ።
ንግግራቸው ቤተክርስቲያንን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑና በቤተክርስቲያንና መንግሥት መካከል የነበረውን ግንኙነት እንዳሻከረው ተመላክቷል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ፥ ብጹዕ አቡነ ሉቃስ የምስራቅ አውስትራሊያ እና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ፅ/ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀጳጳስ ታህሳስ 19 / 2016 ዓ/ም በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት በሜሪላንድ ከተማ ሐመረብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ ወቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በዓለ ንግስ ላይ ታቦተ ህጉ በቆመበት እንዲሁም ምእመናን በተሰበሰቡበት ቤተክርስቲያንን የማይመጥንና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ብሎም የአባትነትን ክብር ዝቅ በሚያደርግ ሁኔታ አንድን ጠቅላይ ሚኒስትር “ግድሉ ፣ ግንባሩን የሚል ጠፋ፣ ዘርህ ይጥፋ” በማለት መናገራቸውን ገልጿል።
ይህ አቡነ ሉቃስ ንግግር ቤተክርስቲያኒቱን የማይወክል፣ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ የሆነ፣ ቅዱስ ሲኖዶስን የማይወክል፣ ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የአባቶች ክብር ዝቅ የሚያደርግ፣ የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ዝቅ የሚያደርግ፣ ከህገ ኦሪትም ሆነ ከቃለ ወንጌል ያፈነገጠ ንግግር እንደሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ገልጿል።
የብፁዕ አቡነ ሉቃስን ጨምሮ አንዳንድ አባቶች በተለያየ ቦታ የሚያስተለልፏቸው መልዕክቶች ቤተክርስቲያንን ለትችት እየዳረገ እንዲሁም ዋጋ እያስከፈለ ነው ተብሏል። በቀጣይ የመግለጫ አሰጣጥ እና የትምህርተ ወንጌል አሰጣጥ ገዢ ህገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለጥቅምት 2017 ዓ/ም ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል።
ከዛሬ ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ አህጉረ ስክበት ስህተት እንዳይፈጸም ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርጉ ያን ሳያደረጉ ቀርተው የተሳሳቱ እና ከቀኖና ቤተክርስቲያን ያፈነገጡ ትምህርቶች አውደምህረት ላይ ቢተላለፉ በኃላፊነት እንደሚያስጠይቅ ጥብቅ መመሪያ እንዲተላለፍ ተወስኗል።