ክሪፕቶአርድሮኘ ምንድን ነው የሚለውን ለማወቅ መጀመሪያ ክሪስቶከረንሲ ምንድን ነው የሚለውን ግልጽ በማድረግ መጀመር ያስፈልጋል። ክሪፕቶከረንሲ ዲጂታል ገንዘብ ወይም ምናባዊ ገንዘብ በሚል ልንጠራው እንችላለን። የማይዳሰስ፣ የማይታይ፣ የማይጨበጥ እና አካል ገልጦ የማይከሰት ዋጋ ያለው የገንዘብ ዓይነት ነው።
ምናባዊ ገንዘብ በድረ ገጽ አማካኝነት ሰዎች ምንም ማዕከላዊ የባንክ ሥርዓት ሳይኖር ልውውጥ የሚያደርጉበት እና ለግብይት አገልግሎት የሚውል ነው።
አሁን ላይ ከ20 ሺህ በላይ የምናባዊ ገንዘብ ዓይነቶች ያሉ ሲኾን በምንዛሬ ደረጃ ቁንጮ ላይ የሚቀመጠው ቢትኮይን የሚባለው የክሪፕቶ ከረንሲ ነው።
በዓለማችን ይህን ገንዘብ በፋይናንስ እና በግብይት ሥርዓታቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሀገራት እና ሥመጥር ኩባንያዎች አሉ። ለአብነት ማይክሮሶፍት፣ ስታርባክስ እና ፔፓል ተጠቃሾች ናቸው።
ክሪፕቶ ከረንሲን ሰዎች ሊያገኙ የሚችሉባቸው መንገዶች አሉ። በዋናነት በምናባዊው የገንዘብ ልውውጥ ላይ ያለውን ትራንዛክሽን በመቆጣጠር እና በማሳላጥ ማግኘት ይቻላል። ይህ መንገድ ማይኒንግ ይባላል።
የከበሩ ማዕድናትን ቆፍረን እንደምናወጣው ሁሉ በማይኒንግም ውስብስብ ቴክኒካዊ ተግባራትን በትራንዛክሽን ሂደት ውስጥ በመተግበር የሚገኝ ነው።
በተጨማሪም ሰዎች ዲጂታል የገንዘብ ቦርሳ ወይም ዲጂታል ዋሌት በመክፈት እና ከባንክ አካውንታቸው ውስጥ ያለውን ሕጋዊ እና ምናባዊ ያልኾነ ገንዘብ በመጠቀም መግዛትም ይችላሉ።
ሌላኛው መንገድ በአርዕስታችን ላይ የገለጽነው ኤርድሮኘ ነው። ኤርድሮኘ ማለት አዲስ ምናባዊ ገንዘብ ሲፈጠር ያንን ለማስተዋወቅ በሚል ከመለቀቁ በፊት ሰዎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ የሚሰጣቸው ዲጂታል ሳንቲም ነው።
ይህ ሳንቲም ወይም ገንዘብ ወደ ሰዎች ምናባዊ የገንዘብ ቦርሳ መግባት የሚችለው የዲጅታል ገንዘብ ፕሮጀክቱ ባለቤቶች በሚያስቀምጧቸው መስፈርቶች መሠረት ነው።
እነዚህ መስፈርቶች የተከፈቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመወዳጀት፣ ሰብስክራይብ በማድረግ እና የሚለቀቁ የማስታወቂያ ቪዲዮዎችን በመመልከት ሊኾን ይችላል።
ኤርድሮፖች ስታንዳርድ፣ ሆልደር፣ ቦውንቲ እና ኤክስክሉሲብ የሚባሉ ዓይነቶች አሉት ። እነዚህ የኤርድሮፖች ለተጠቃሚዎቸቸው በሚደርሱበት መንገድ ነው የሚለያዩት።
ስታንዳርድ የሚባለው ኤርድሮኘ ሰዎች የዋሌት አድራሻቸውን እና መሠረታዊ የግል መረጃዎችን በማቅረብ የፕሮጀክቱ ባለቤቶች ለተጠቃሚዎቻቸው የሚያጋሩበት ነው። ሆልደር ኤርድሮኘን ካየን ደግሞ ተጠቃሚዎች መጀመሪያ በዲጂታል ዋሌታቸው ውስጥ ገንዘብ መኖሩ ተረጋግጦ የሚጨመርላቸው የኤርድሮኘ ዓይነት ነው።
ቦውንቲ ኤርድሮፕ የምናባዊ ገንዘብ ባለቤቶች የሚፈጥራቸውን የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በመወዳጀት፣ የጽሑፍ እና የቪዲዮ መረጃዎችን በመመልከት እና ወዳጅነትን በማሳየት በምትኩ የሚለቀቅ ነፃ ምናባዊ ገንዘብ ነው።
ሌላኛው ደግሞ የምናባዊ ገንዘብ ፕሮጀክቱ ባለቤቶች በሚያቀርቡት ግብዣ ለሚመረጡ ሰዎች የሚበረከት ሲኾን ኤግዚከውቲቭ ኤርድሮፕ ይባላል።
የፕሮጀክቱ ባለቤቶች ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚከተሏቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። እነዚህም ኤርድሮፖችን ለመስጠት የወጡ መስፈርቶችን ማሳወቅ፣ ተጠቃሚዎች የዲጅታል ዋሌት አድራሻቸውን ማቅረብ፣ የተሳታፊዎችን ተገቢነት እና ማንነት ማረጋገጥ እና ከዛም በፕሮጀክቱ ደንብ እና ሕግ መሠረት ወደ ዲጂታል በርሳ ገቢ ማድረግ ናቸው።
ኤርድሮፕን በመጠቀምም ኾነ በሌላ መንገድ የተገኘን ምናባዊ ገንዘብ መጠቀም የሚፈቃዱ ሀገራት ቢኖሩም በተለያዩ ምክንያቶች የሚከለክሉ ሀገራትም አሉ። በይፋ ካልፈቀዱት ሀገራት መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያም አንዷ ናት።
ምናባዊ ገንዘብ እንዲከለከል ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ በመንግሥት እና በባንክ ሥርዓት እውቅና አልፎ የሚፈጸም ልውውጥ ያለው ባለመኾኑ ለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑ፣ በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመስል የሚያስችሉ ሁኔታዎች ስላሉት፣ ለወንጀል እና ሽብር ተግባራት ድጋፍ ለማድረግ የሚውል በመኾኑ እና ሌሎችም ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ከምንም በላይ ግን ከቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ ለመጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ቢኖር እንኳ ሀገራት የሕግ እና የቴክኖሎጂ ዝግጅት ሊኖራቸው ይገባል።
(አሚኮ)