እስራኤል ለወራት በሃማስ የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ የፈጸመችው ኦፕሪሽን ተአምራዊ ተብሏል። ይህ ዜጎችን የማስለቀቅ ዘመቻ የተሳካና የኮማንዶዎቿን ልዩ ብቃት ያሳየ ሆኖ ተነግሮለታል። ከዕግት የተረፉት የሰጡትይን ምስክርነት ቢቢሲ እንደወረደ ዘግቦታል።
“በሹክሹክታ ለመናገር ተገደደዋል” ይላሉ የአንድሬ ኮዝሎቭን አባት። አንድሬን ቅዳሜ ዕለት ከሐማስ እገታ ከተለቀቁት አራት ሰዎች አንዱ ነው።
አባቱ ማይክል የሩሲያ እና የእስራኤል ጥምር ዜግነት አላቸው። አንድሬ የእስራኤል “አልማዝ” ሲል የሰየመውን ታጋቾችን የማስለቀቅ ዘመቻ እሳቸው ደግሞ “ተአምር” ብለውታል።
አንድሬ ወላጆች ዩጂኒያ እና ማይክል ኮዝሎቭ የልጃቸውን መለቀቅ ሰሙበትን አጋጣሚ፣ ያለፉትን ስምንት ወራት ያሳለፉትን ሕይወት እና ሌላም ሌላም አንስተው ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አንድሬ እና አብሮት የታገተ ሌላ ሰው አንድ ክፍል ውስጥ እንዳሉ ነው የእስራኤል ጦር የደረሰው። ታጋቾቹ በፍርሃት ለመሸሽ ሲሞክሩ ወታደሮቹ ላይ የተገጠመው ካሜራ አጋጣሚውን ቀርጾታል።
በእስራኤሉ ወታደሮች የተለቀቀው ምሥል የሚያሳየው አንድሬ የ27 ዓመቱ እና ሌላ ታጋች፣ አዳኞቻቸው ወደ ታሰሩበት ክፍል ከገቡ በኋላ በፍርሃት እጃቸውን ወደ ላይ ሲይዙ ከትራስ ጀርባ ተደብቀው ነበር።
እናቱ ኡጂኒያ እንደሚሉት ከሆነ አንድሬ እና ሌሎችም ታጋቾች ከፍተኛ ለወራት ያልተገባ መረጃ ሲጫንባቸው ከርመዋል። የእስራኤል ወታደሮች ሲደርሱ ዕቅዱ “መግደል ይሁን የማዳን” ግልጽ እንዳልሆነላቸው የተናገሩትም ለዚህ ነው።

ስለታጋቾቹ እስራኤል ደንታም የላትም ከማለት ባለፈ በአገሪቱ ባለሥልጠናት እንደ ችግር እስከመቆጠር መድረሳቸው ተደጋግሞ ተነግሯቸዋል። በዚህ ምክንያት ያሉበት ከታወቀ ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጭምር ነው የተነገራቸው።
ማይክል በበኩላቸው ልጃቸው እና ሌሎች ታጋቾች ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው እንዲያወሩ ተነግሯቸዋል። ምክንያት ተባሉት ደግሞ “ልዩ የስለላ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በዕብራይስጥ የሚናገሩትን ይሰማል” በሚል ነው።
“ይህ በጣም ጥልቅ የሆነ የሥነ ልቦና ጉዳት አድርሶበት የሚሉትን እንዲያምን አስገድዶታል” ይላሉ ኮዝሎቭ።
“ከእገታ ነጻ መውጣቱን እስኪያውቅ ድረስ ቀልጦ ነበር።”
አንድሬ ከጋዛዋ ኑሴይራት ካምፕ ከእገታ ነጻ ከወጡ አራት ሰዎች አንዱ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ኖአ አርጋማኒ፣ አልሞግ ሜየር ጃን እና ሽሎሚ ዚቭ ሚባሉ ሲሆኑ፣ ሁሉም መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ከተካሄደ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ የታገቱ ናቸው።
አንድሬ ከእገታው ከ18 ወራት በፊት ነበር ከሩሲያ ወደ እስራኤል ያቀናው። እስራኤል ውስጥም የፀጥታ ኃይል አባል በመሆን ያገለግል ነበር።
እናቱ ዩጄንያ መቀመቻቸውን ሴንት ፒተርስበርግ ሩሲያ ቢያደርጉም ልጃቸው ከታገተ በኋላ እየተመላለሱ ታጋቾች እንዲለቀቁ በሚጠይቁ ሰልፎች እና ከባለሥልጣናት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ተሳትፈዋል። ወደ ቴል አቪቭ ሊመለሱ ሲዘጋጁ ነው ከእስራኤል ባለሥልጣናት ተደውሎ ስለልጃቸው መልካሙ ዜና የተበሰረላቸው።
“መጥፎ ዜና መስሎኝ ‘አይሆንም!’ ብዬ መጮህ ጀመርኩ። ስልኬን ስወረውረው ከጠረጴዛው ስር ገባ” ሲሉ ቅጽበቱን ያስታውሳሉ።
“’የምሥራች ነው የያዝነው’ እያሉ ሲጮሁ ድምጻቸው ከጠረጴዛው ስር ይሰማኛል።”
“ጠረጴዛው ስር ተስቤ ገባሁ እና ‘ምን እያላችሁ ነው?’ አልኳቸው።”
“የምሥራች ነው ያለን። አንድሬ ተለቋል። እንግሊዘኛዬ እንደነገሩ ነው። የነገሩኝን እንዲደግሙልኝ ጠኳቸው።”
አባት እና እናት ልጃቸውን በቪዲዮ ለማናገር ሲዘጋጁ ስጋት ነበራቸው። ምን መስሎ ይሆን የሚለው ስጋታቸው ግን ራሱን ሆኖ ስላገኙት ወደ እፎይታ ተቀየረ።
“ሳቀ፣ ቀለደ። ከጋዛ ከወጣ ከሦስት ሰዓታት በኋላ ይቀልድ ጀምሯል” ብለዋል እናቱ።
“እስር ቤት ውስጥ ታስሮ ነበረው ልጃችን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ እራሱን እስራኤል ግዛት ውስጥ አገኘው” ሲሉ አክለዋል።
ልጃቸው ስለ’ተአምራዊው’ ታጋቾችን የማዳን ዘመቻ የተነገራቸውን በዝርዝር መንገር አልፈቀዱም። ሦስቱ ወንድ ታጋቾች በኑሴይራት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ከሚገኝ ከአንድ መኖሪያ ቤት በሚታደጉበት ወቅት ከሐማስ ታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
በኋላም ታጋቾቹን እና የተጎዱ የልዩ ኃይል አባላትን ለማስወጣት የሚጠቀሙበት የጭነት መኪና ተበላሽቶ በቆመበት በታጠቁ ሰዎች ተከበቡ። የእስራኤል አየር ኃይል ደርሶ በፈፀመው ከባድ የቦምብ ጥቃት ጦሩ ጊዜ አግኝቶ ለማምለጥ በቃ።
የጋዛ ጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ይህ ከ270 የሚበልጡ ፍልስጤማውያን ሕይወታቸው ያለፈበት አጋጣሚ በርካታ ሰዎች ከሞቱባቸው ቀናት አንዱ ሆኗል ብለዋል።
የእስራኤል ጦር የሟቾችን ቁጥር ከ100 በታች ነው ብሏል። ሐማስ ሕዝብ በሚበዛበት ቦታ ታጋቾችን እየደበቀ ለዚህ ጉዳት መድረስ ምክንያት ሆኗል ሲልም ተጠያቂ አድርጎታል።
“ለሁለት ወራት እጅ እና እግሩ ተጠፍሮ ታስሮ ነበር” ይላሉ እናቱ በሚቆራረጥ ድምጻቸው።
አባት ደግሞ “አዋርደው ደበደቧቸው” ይላሉ።
“ሁልጊዜ በሥነ ልቦና ጫና ውስጥ ነበሩ። ‘እናትህ ለእረፍት ወደ ግሪክ መሄዷን አውቀናል። አይተናል። ሚስትህ ከሌላ ሰው ጋር እየተገናኘች ነው’ ተብለዋል” ይላሉ እናቱ ዩጂኒያ።
ታጋቾቹን የማስለቀቁ ዜና በመላው እስራኤል አስደሳች ምላሽ አስገኝቷል።

“ሰዎች ከመኪናቸው እየወጡ አንድሬን ሰላም ይሉታል። የአራቱ ታጋቾች መፈታት ለመላው እስራኤል ደስታ መፍጠሩ አስገርሞኛል” ብለዋል እናቱ።
እስራኤል ከስምንት ወራት በፊት አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎችን በገደለባት የሐማስ ጥቃት አሁንም እንደተናጠች ነው። ተይዘው ወደ ጋዛ ከተወሰዱት ከ240 በላይ ታጋቾች መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት በኅዳር ወር ለአንድ ሳምንት በዘለቀው የተኩስ አቁም ስምምነት ተለቀዋል።
በዕለቱ ታግተው ከተወሰዱት ውስጥ 116 ታጋቾች አሁን በጋዛ እንደሚቀሩ እስራኤል ተናግራለች። ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ጨምሮ በሕይወት ላይኖሩ እንደሚችሉም ደምድማለች።
ከቅዳሜው የነፍስ አድን ዘመቻ በፊት ታግተው ጋዛ ከደረሱት መካከል ሦስት እስራኤላውያን ብቻ በወታደራዊ ዘመቻ ተለቀዋል። የቅዳሜው ስኬት ደግሞ ለአገሪቱ በለጠ ብርታት ሆኗታል።
ባለፉት ስምንት ወራት በርካታ ታጋች ዘመዶችን የተዋወቀችው ዩጂንያ ምን ያህል ዕድለኛ እንደሆኑ የሚገልጹ በርካታ ምክንያቶች አሏቸው። በቴል አቪቭ ዙሪያ እና የአንድሬ መኖሪያ በሆነችው በማዕከላዊ እስራኤል እስካሁን የታገቱ ሰዎችን ምሥሎች የያዙ ፖስተሮች ተለጥፈዋል።
“እነዚህን ምሥሎች መመልከት በጣም ያሳዝናል። በየቦታው ተለጥፈዋል። አሁን ፊታቸውን እያየሁ የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማኝ ይመስለኛል። ምክንያቱም በደንብ ስለምንግባባ እና በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ ስለምንነጋገር ይህ ተአምር ነው እንላለን!”
ልጃቸው መከራ ቢደርስበትም ወላጆቹ ግን ከሌሎች የእስራኤል ታጋቾች በተሻለ ሁኔታ ውስጥ መያዙን የነገሩትን ጠባቂዎቹን ወደማመን ያዘነብላሉ። ምክንያቱም ሌሎቹ ብርሃን በሌላቸው ከመሬት በታች ባሉ ዋሻዎች ውስጥ ታጉረዋልና ነው።
“እስካሁን ስለታገቱት ሰዎች ያለማቋረጥ እናስባለን። በእርግጠኝነት ልንታደጋቸው ይገባል” ሲሉ ማይክል ተናግረዋል።
ስለታጋቾቹ መቀስቀሳቸውን ባያቋርጡም አሁን ጉልበታቸውን ሰብስበው አንድሬ ሕይወቱን እንዲያስተካክል ለመርዳት እየሞከሩ ነው።
ከ245 ቀናት እገታ በኋላ አንድሬ ትኩረቱን ያመለጡትን ነገሮች ስለማወቅ ሆኗል። የእስራኤል መንግሥት ታጋቾቹን እንዲያስለቀቅ ስለሚጠይቁት ግዙፍ ሰልፎችም ተነግሮታል።
“በብዙ ነገሮች ይገረማል። የማያውቀው ዜና ደግሞ አንዳንዴ እንቅልፍ እንዳይተኛ ያግደዋል” ይላሉ እናቱ።
“ጽሑፎችን አንብቦ ደግሞ ‘ይህ እውነት ነው? የእውነት ነው ሆነው?’ ሲል ይጠይቃል” ብለዋል።
Read the original story on BBC
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሂዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ መገደሉ ተሰምቷል። እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ላይ ጥቃት ነው የሂዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ ታሌብ አብደላህ የተግደለው፡፡
ታሌብ አብደላህ የእስራኤል ጦር ትናንት ምሽት በደቡባዊ ሊባኖስ ጆዩያ በተሰኘ አካባቢ በፈጸመው የአየር ጥቃት ነው የተገደለው፡፡ በቅጽል ስሙ አቡ ታሌብ ተብሎ የሚጠራው ታሌብ አብደላህ በደቡብ ሊባኖስ ቀጣና የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አዛዥ እንደነበር ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
ከአዛዡ በተጨማሪም ሶስት የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አባላት በጥቃቱ መገደላቸው ነው የተገለጸው፡፡ ታሌብ አብደላህ የተባለው ከፍተኛ የቡድኑ አዛዥ መገደሉን ሂዝቦላህ ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል፡፡