የወንጀል ህግ አንዱ አላማ እና ግብ ወንጀል እንዳይፈጸም መከላክል ሲሆን ይህም ስለ ወንጀል ድርጊቶች እና ስለ ሚያስከትሉት ቅጣቶች አስቀድሞ በማሳወቅ ተፈጽመው በተገኙ ጊዜም ለሌላው ትምህርት እንዲሆን አሰተማሪ የሆነ ቅጣትን በመቅጣል አለማውን የሚያሰካ በመሆኑ የሚጣለውም ቅጣት ወጥነት፤ ትክክለኝነት፤ ተገማችነት፤ ምክንያታዊነት እና ፍታዊነት ያለው መሆን አለበት፡፡ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ በ1996 የወጣው የወንጀል ህግ ቅጣትን ያሚያቀሉና የሚያከብዱ ምክንያቶችን ፤ሁኔታዎችን፤ አይነቶችን እና ፍርድ ቤትም ቅጣትን ሲጥል ግምት ውስጥ ማስገባት ስላለበት ሁኔታዎች ፤እንደ ቅጣት ማቅለያ እና መክበጃም ምክንያቶች ሊያዙ የሚገባ ምክንያቶችን እና ቅጣት በሚጥልበት ወቅት እንዴት ማስላት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በዚህ ጹሁፍ በወንጀል ህጉ ላይ ያተዘረዘሩትን የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ምክንያቶችን በዝርዝር የምናይ ይሆናል፡፡
የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ምክንያቶች
በ1996 የወጣው የኢ.ፊ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ምክንያቶችን ጠቅላላ እና ልዩ የቅጣት የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ ምክንያቶች በማለት በሁለት ያሚከፍል ሲሆን እነዚህም፡-
1ኛ ጠቅላላ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች
የወንጀል ህጉ አንቀጽ 82/1 ከ ሀ እስከ ሠ ባለው ስር የተለያዩ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ የቅጣት መቅለያ ምክንያቶችን በዝርዝር የሚያስቀምጥ ሲሆን እነዚህም ሁኔታዎች የጥፋተኛውን ግላዊ ሆኔታ ፤የትምርት ደረጃ ፤የተጎጂውን አስተዋጾ፤ ወንጀሉን እንዲፈጽም ያስገደዱትን ምክንያቶች እና ሌሎች ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በአምስት መቅላላ የቅጣት ማቅለያ ሁኔታዎች በመክፈል አስቀምጧ እነዚህም፡-
ሀ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን እስካደረገበት ጊዜ ድረስ የዞትር ጠባዩ መልካም እንደ ሆነ እና ያጠፋውም በእውቀት ማነስ፤ ባለማወቅ ፤ በየዋህነት ወይም ባልታሰበ በድንገተኛ አጋጣሚ ሲሆን፡፡
ለ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው በተከበረ እና በግል ጥቅም ላይ ባልተመሰረተ ፍላጎት ሲሆን ውይም
ከፍ ባለ ሀይማኖታዊ፤ ሞራላዊ ወይም ማህበራዊ እምነት ተነሳስቶ እንደሆነ
ሐ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈጸመው ከፍተኛ ቁሳዊ እጦት ወይም የሂሊና ስቃይ ደርሶበት እንደሆነ
ከፍ ያለ አደጋ የሚያመጣ ነገር የተቃጣበት መስሎት እንደሆነ
መሰረት ያለው ፍረሃት አድሮበት እንደሆነ ወይም
ሊታዘዝለት በሚገባው ወይም በስልጣኑ ስር በሚያስተዳድረው ሰው ተጽኖ ምክንያት እንደሆ፡፡
መ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን የፈጸመው የተበደለው ሰው ጸባይ ከብርቱ ፈተና ላይ ጥሎት በከባድ ጸብ ቀስቃሽነት በአጸያፍ ስድብ ምክንያት ደም ከሚያ ፈላ ንዴት ፤ስቃይ ብስጭት ላይ ጥሎት እንደ ሆነ ወይም
ከፍ ያለ አስገዳጅነት ባለው ስሜትን በሚለውጥ ሁኔታ ወይም ምክንያት ባለው የመንፈስ ሁከት ላይ ሆኖ እንደ ሆነ
ሠ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን ካደረገ በኋላ የእውነት የተጸጸተ መሆኑ በተለይም በደል ላደረሰበት ሰው አስፈላጊውን እርዳታ ያደረገ እንደሆነ
ጥፋቱን በመገንዘብ ለፍትህ አካላት እርሱን የቀረበ እንደ ሆነ
የወንጀሉ ጥፋት ላደረሰው ጉዳት በተቻለው መጠን በመካስ መጸጸቱን በተግባር አሳይቶ እነደ ሆነ ወይም
ተከሶ ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ በክስ ማመልከቻ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ዝርዝር በሙሉ ያመነ እንደ ሆነ በማቅለያነት ይያዝለታል በማለት የህጉ ድንጋጌ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡
ነገር ግን ከላይ የተዘረዘሩት ሁኔታዎች
በህጉ ልዩ ክፍል ውስጥ በተለየ ድንጋጌ እነዚህ ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች በማቅለያነት በተመለከቱ ጊዜ ፍ/ቤቱ በድጋሜ እዚህን ምክንያቶች ቅጣቱን ለማቅለል በድጋሜ ሊጠቀምባቸው አይችልም፡፡
2ኛ ልዩ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች
ዝምድና እና የጠበቀ ወዳጅነት
ይህ የቅጣት ማቅለያ በብዛት ጥፋተኛው በቀጥታ ወንጀል ላይ ሳይሳተፍ ነገር ግን ፤የቅርብ የስጋ ዘመዱን ወይም የቅርብ የጋብቻ ዘመዱን ወይም በተለየ ጥብቅ በሆነ ወዳጅነት የተሳሰረውን ሰውን ወንጀል ፈጽሞ እሱን ለቅጣት ፤ለውርደት ወይም ለከባድ አደጋ ላለማጋለጥ በማሰብ
ወንጀል መደረጉን እና ወንጀለኛውን እያወቀ ለፍርድ ባለስልጣን ያማስታወቅ ግዴታውን ያለፈጸመው እንደሆነ
መስጠት የሚገባውን እርዳታ ያልሰጠው እንደሆነ
ሀሰተኛ መግለጫ፤ ምስክርነት ወይም መረጃ የሰጠው እንደሆነ
ወንጀለኛው ከክስ ወይም ከቅጣት አፈጻጻም እንዲያመልጥ በመርዳት የወንጀል ህግን የሚቃረን ተግባር ያደረገ ሲሆን ነው፡፡
ፍርድ ቤቱም ዝምድና መኖሩን እና ምክንያቱ በቂ መሆኑን በማረጋጋጥ በመሰለው ቅጣቱን ያሚያቀል ሲሆን ዝምድናው ጥብቅ ሲሆን እና የተፈጸመው ወንጀልና የደረሰው ጉዳት አነስተኛ ሲሆን ወንጀለኛውን በማስጠንቀቂያ፤ በወቀሳ ወይም በነጻ ሊያልፈው እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡
ነገር ግን ጥፋተኛው የፈጸመው ወንጀል
በአገር ላይ በህግ መንግስቱ እና ህግ መንግስታዊ ስረዓቱ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች አለማሳወቅ ሲሆን
በመከላከያ ሰራዊት እና በወታደራዊ ግዴታዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አለማሳወቅ ሲሆን እና
የመሸሸግ ወንጀል ሲሆኑ
ዝምድና እና የጠበቀ ወዳጅነት መኖሩ እንደ ልዩ ቅጣት ማቅለያ ምክንያት እንደማይያዝለት በግልጽ ህጉ ደንግጎ ይገኛል፡፡
3ኛ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች
የወንጀል ህጉ አንቀጽ 84/1 ከ ሀ እስከ ሠ ባለው ስር የተለያዩ ሁኔታቶችን መነሻ በማድረግ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶችን በዝርዝር ያሚያስቀምጥ ሲሆን እነዚህም ሁኔታዎች የጥፋተኛውን ግላዊ ጸባይ፤ አመል፤ ሀላፊነት፤ ስልጣን፤ ወንጀል አፈጻጸም ሁኔታ፤ አደገኝነት እና የተጎጂውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአምስት መቅላላ የቅጣት ማክበጃ ሁኔታዎች በመክፈል የሚያስቀምጥ ሲሆን እነዚህም፡-
ሀ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው
-በከሐዲነት ወይም
- በወስላተነት ፤ወራዳነት ወይም
- መጥፎ አመልን በሚያሳይ ምቀኝነት ጥላቻ ስግብግብነት
-መጥፎ ነገርን ለመስራት ወይም ስውን ለመጉዳት ፍጹም ፍቃደኛ በመሆን ፤ወይም
-በተለየ ክፋት ወይም ጨካኝነት እንደ ሆነ
ለ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው ስልጣኑን ተግባሩን ወይም የተጣለበትን እምነት ወይም ሀላፊነት ያለአግባብ በመገልገል እንደሆነ
ሐ/ ወንጀለኛው በቀድሞ ጥፋተኝነቱ ፤ወንጀልን ማድረግ ሙያው ወይም ልምድ አድርጎ መያዙ፤ወይም
የወንጀሉ አፈጻጸም ዘዴ፤ጊዜ ፤ቦታና የአፈጻጸሙ አኳኋን፤በተለይም
-በሌሊት ወይም በሽብር ወይም በሁከት ለአደጋ ሽፋን ወይም በጦር መሳሪያ ወይም በሌላ አደገኛ መሳሪያ ወንጀሉን በማድረግ የተለየ አደገኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ እንደ ሆነ
መ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው ወንጀል ለመፈጸም በተደረገ ስምምነት መሰረት ሲሆን ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን ሲሆን
ወንጀል ለመፈጸም ከተቋቋመ ቡድን ጋር በመስማማት ወይም አባል በመሆን ይልቁንም እንደ ወንጀል ቡድን ሹም፤አደራጅ ወይም መሪ በመሆን እንደሆነ
ሠ/ ወንጀለኛው ወንጀሉን ያደረገው በዕድሜው፤ በጤንነቱ፤ በኑሮው ወይም በስራው ሁኔታ ልዩ ጥበቃ በሚያሻው ሰው ላይ በተለይም ለመከላከል አቅም በሌለው ፤መንፈሰ ደካማ ፤በሽተኛ ወይም የአካል ጉዳተኛ፤እስረኛ ሲሆን
በቅርብ ዘመዱ ላይ ወይም የበላዩ ወይም የበታቹ በሆነ ሰው ላይ ሲሆን
በህግ በተቋቋመ ባለስልጣን ወይም የስራ ግዴታውን በማከናወን ላይ በሚገኝ በአንድ የህዝብ አገልጋይ በሆነ ሰራተኛ ላይ ሲሆን ነው በማለት በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡
ነገር ግን
እነዚህ ሁኔታዎች በህጉ ልዩ ክፍል ለወንጀል ማቋቋሚያ ወይም ለቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች እንደሚሆኑ በተደነገገ ጊዜ የወንጀል ቅጣት ለማክበድ ሲል ፍ/ቤቱ ይህንኑ ሁኔታ ዳድም ምክንያት ሊያደርግ እንደማይችል ህጉ ይደነግጋል ፡፡
4ኛ ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች
የወንጀሎች መደራረብ እና ደጋጋሚነት
የወንጀል ህጉ በአንቀጽ 60 ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመዋል የሚባሉት
ሁለት ወይም ከሁለት ሚበልጡ አንድ አይነት ወይም የተለያዩ ወንጀሎችን አከታትሎ ሲፈጸም
በአንድ ድርጊት በአንድ ጊዜ ሁለት ወይም ከሁለት ባላይ የሆኑ ህግ ድንጋጌዎችን በመጣስ
በአንድ ድርጊት ልዩ ልዩ ግዙፋዊ ውጤት የሚያስከትሉ ወንጀሎችን በመፈጸም ጣምራ ወንጀሎችን መድረግ
በአንድ የወንጀል ድርጊት ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ አንድ አይነት ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ እንደ ልዩ ቅጣት መከበጃ ምክንያቶች የወስዳሉ፡፡
የወንጀል ህጉ አንቀጽ 67 አንድ ሰው ደጋጋሚ ነው ሚባለው የተወሰነበትን የእስራት ቅጣት በሙሉ ወይም በከፊል ከፈጸመበት ወይም ይህ ቅጣት በይቅርታ ከቀረለት ቀን ጀምሮ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ መነሻ ቅጣቱ ስድስት ወር የሆነ ቀላል እስራት ሊያስቀጣ የሚችል አዲስ ወንጀል አስቦ የፈጸመ እንደሆነ እንደ ልዩ የቅጣት ማክበጃ ምክንያት የሚያዝ ያሆናል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በህጉ ላይ ከተዘረዘሩት ውጪ ሌሎች ጠቅላላ የቅጣት ማቅለያ እና መክበጃ ምክንያቶች ሲገኙ እና ይሄንኑ ፍርድ ቤቱ የሚቀበል ሲሆን ለምን እንደተቀበለው በምግለጽ መያዝ እንደሚችል ህጉ ደንግጎ ይገኛል፡፡
በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ