የአትሌቲክሱ ድላችን በመላው አለም ከምንታወቅባቸው ቁልፍ እሴቶቻችን መሀል ትልቁ መገለጫ የሆነ ብሔራዊ ክብራችን ነው።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ያዘጋጁት እና በመጪው ክረምት ፓሪስ ኦሎምፒክ ለሚወዳደሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አትሌቶች በኢትዮጵያ አየር ኃይል የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል የልምምድ ፕሮግራም የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ በበጎ ጎኑ ስሟን ከሚያስጠሩ ቁልፍ እሴቶቻችን መሀል የአትሌቲክሱ ድላችን በዋነኝነት የሚገለፅ ብሔራዊ ክብራችን መሆኑን ጠቁመዋል።
በየውድድር መስኩ አትሌቶቻችን ለሰንደቅ አለማችን ክብር በብርቱ መፋለማቸውን ያወሱት ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በተለይም ከትግራይ የመጡ አትሌቶች ባለፉት ጥቅት አመታት ያንን ሁሉ ወጀብ እና አሉታዊ ወሬዎችን ተቋቁመው ሀገራቸውን በማሰጠራታቸው ታላቅ የሆነ ምስጋና እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
እስከ ልምምዳችሁ ፍፃሜ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ያስታወቁት ዋና አዛዡ “ሰማዩ የእኛ ነው” እንደሚባለው የአየር ኃይል ሎጎ አትሌቶቹም “ሜዳሊያው የኛ ነው” በሚል ሎጎ ልምምዳቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርግስ ኦሎምፒክ የሀገር ክብር እና ሰንደቅ አላማ በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ የሚታይበት የስፖርቶች ሁሉ ቁንጮ መሆኑን እና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ይህን ታሳቢ ባደረገ የስነ ልቦና መንፈስ ራሳቸውን ብቁ አድርገው ለውድድሩ መዘጋጀት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በበኩላቸው የፓሪስ ኦሎምፒክ ተወዳዳሪ አትሌቶች መላው ኢትዮጵያዊያን በጉጉት የሚጠብቁትን ይህን ታላቅ ውድድር ለማሸነፍ ከሁሉም በፊት ስፖርቱ በሚጠይቀው የቡድን መንፈስ እስከ ውድድሩ መዳረሻ ልምምዳቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመው የኢትዮጵያ አየር ኃይልም የመሮጫ ሜዳን ጨምሮ በሁሉም በኩል አጋርነቱን በተግባር ስላሳየን እናመሰግናለን ብለዋል።
ቀጣይ ልምምዳቸውን ጠንክረው በመስራት በፓሪስ ኦሎምፒክ ውጤታማ ለመሆን እንደሚዘጋጁ አትሌቶችን በመወከል የተናገሩት አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጉዳፍ ፀጋይ እና ረዳት ኮሚሽነር ሁሴን ሼቦ ናቸው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት