የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፦
- ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የ2ኛ ዙር የከተሞች የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የተፈረመውን የብድር ሥምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በብድር የተገኘው 207 ሚሊየን 200 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሲኾን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የሳኒቴሽን እና ሃይጂን አገልግሎት ተግባራትን ለማሻሻል እና የዘርፉን የማስፈጸም አቅም ለማጠናከር የሚውል ነው፡፡
ብድሩ ወለድ የማይታሰብበት፣ 0.75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት ኾኖ ስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ብድሩ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መኾኑን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
- በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የንብረት ታክስ በከተሞች ነዋሪ በኾነው ሕዝብ መካከል ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ለማስፈን፤ የመንግሥት አገልግሎቶችን በተሻለ ጥራት እና በዘመናዊ ዘዴ ማቅረብ ለማስቻል እና የከተማ መሠረተ ልማት ማሻሻያዎችን በቀጣይነት ለመተግበር የሚወጣውን የኢንቨስትመንት ወጪ በንብረት ዋጋ ማደግ ምክንያት በሚጣል ታክስ አማካኝነት ለመሰብሰብ የሚያስችል ነው፡፡ አዋጁ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ተፈጻሚነት የሚኖረው ሲኾን፤ ክልሎችም ይህንን አዋጅ መሠረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ሕግ እንዲያወጡ ያስችላል። በዚሁ መሠረት ይህንን ለማስፈጸም የሚረዳ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
- በ3ኛ ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሪፎርም እና የካፒታል ማሳደጊያ ዕቅድ ላይ ነው፡፡ የባንኩን የሃብት ጥራት ለማሻሻል እና በአስተማማኝ መልኩ የካፒታል መጠኑን በማሳደግ ለኢኮኖሚው ዕድገት እና ልማት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ዘላቂነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርግ ለማስቻል የሚረዱ የውሳኔ ሃሳቦች ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡ እነዚህም የባንኩን አስተዳደራዊ ውጤታማነት ማጎልበት፤ የሒሳብ መግለጫዎቹን ጠንካራ እና ተቀባይነት ባለው መልኩ እንዲዋቀር ማድረግ እና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚረዳ የመንግሥት የፋይናንስ አቅርቦት ማሻሻል የሚሉ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ በማሻሻያ እቅዱ ላይ ተወያይቶ ወደቀጣይ ተግባር እንዲገባ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
- ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ባለፉት 16 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው አዋጅ ሁሉንም የልማት ተዋናዮች ያሳተፈ የብልጽግና ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና መርኾች አንጻር፣ ከአቻ ማዕከላዊ ባንኮች መልካም ተሞክሮ፣ ከገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነት እንዲሁም በፋይናንስ ራስን ከመቻል አንጻር ክፍተቶች ያሉበት በመኾኑ፤ ባለፉት ዓመታት በሀገር ውስጥም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጦች በመኖራቸው፤ የባንኩን ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት የማስፈን፣ ዋጋን የማረጋጋት እና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የማድረግ ተልዕኮ ለማሳካት አዋጁን ማሻሻል እንደሚገባ ስለታመነበት ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን ታክለው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
- በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ስለባንክ ሥራ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ፣ የአደረጃጀት፣ የአሠራር እና የመንግሥት ፖሊሲ ለውጦች በመኖራቸው፤ ሀገራችን ለረጅም ጊዜ ዝግ አድርጋው የነበረውን የባንክ ሥራን ለውጭ ሀገራት ክፍት ማድረጓን ተከትሎ ይህንን ለመምራት፣ የፍቃድ አሰጣጥን ለመወሰን እና ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግ እና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶች ታክለውበት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
- በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የአካባቢ እና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የልማት ፕሮጀክቶች ከመተግበራቸው በፊት የአካባቢ እና ማኅበረሰብ ተጽእኖ ግምገማ እና ጥናት እንዲካሄድባቸው በማድረግ ተጽእኖዎቹን አስቀድሞ በመተንበይ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ መተግበር ስላለባቸው ሥራዎች የሚደነግግ እና የአካባቢ ጥበቃ ቁጥጥር አሠራርን በተቀናጀ መልኩ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ወጥ የኾነ ሀገራዊ የአካባቢ እና ማኅበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡